ጣሊያን ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተሰማ

በደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና በአውሮፓ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል። ቢቢሲ አማርኛ በኢትዮጵያ እና በተቀረው ዓለም ከቫይረሱ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን እና መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እያደረጉ ስለሚገኙት ጥረት መረጃዎችን በፍጥነት እናደርሳችኋላን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያስፈልገው ማን ነው?

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያስፈልገው ማን ነው?

    የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የፊት መሸፈኛ ጭምብል ያን ያክል አስፈላጊ ነው? ለመሆኑ ጭምብል ማድረግ ያለበትስ ማንና መቼ ነው? በለንደን የህክምና ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆኑት ዶ/ር ሹንሜይ ዩንግ ጭምብል መቼ አስፈላጊ እንደሆነና እነማን መጠቀም እንዳለባቸው ያስረዳሉ።

  2. የአሜሪካ ኤምባሲ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎቼ ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው አለ

    የአሜሪካ ኤምባሲ አርማ

    የፎቶው ባለመብት, US Embassy

    አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለዜጎቹ ባወጣው የደኅንንት መስጠንቀቂያ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከኮቪድ-19 [ከኮሮናቫይረስ] ክስተት ጋር በተያያዘ ጸረ የውጪ ዜጋ የሆኑ ስሜቶች እየተንጸባረቁ መሆኑን አመልክቷል።

    ከበሽታው ጋር የውጪ ዜጎችን በማያያዝ አዋራጅ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም አጸያፊ ቃላት በዜጎቹ ላይ መሰንዘሩን ሪፖርት እንደተደረገ ኤምባሲው ተጠቁሟል።

    ይህ ጥቃት በአሜሪካዊያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራት ዜጎች ላይ ጭምር እያጋጠመ መሆኑን በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ማሳወቃቸውን ከኤምባሲው ያወጣው ማስጠንቀቂያ ጠቁሟል።

    በተጨማሪም በክስተቱ ዙሪያ የቀረቡ አቤቱታዎች በድንጋይ መመታትን፣ የታክሲ አገልግሎት መነፈግን፣ ምራቅ መትፋትን፣ ማባረርና በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ብሎ መውቀስን እንደሚጨምር አመልክቷል።

    በዚህም ሳቢያ ኤምባሲው ዜጎቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል።

  3. የኮሮናቫይረስ ስርጭትን የሚያመላክት አሁናዊ መረጃ

    ካርታ
  4. ፌስቡክ በናይጄሪያ ከኮረናቫይረስ ጋር ተያይዘው የሚሰራጩ ሐሰተኛ ዜናዎችን ሊቆጣጠር ነው

    ፌስቡክ ለናይጄሪያውያን ስለኮሮናቫይረስ የሚያስተምሩ የተለያዩ መልዕክቶችን ያሰራጫል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፌስቡክ ለናይጄሪያውያን ስለኮሮናቫይረስ የሚያስተምሩ የተለያዩ መልዕክቶችን ያሰራጫል

    ፌስቡክ ከኮረናቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚሰራጩ ሐሰተኛ ዜናዎችን የሚያረጋግጥ የሙከራ ፕሮግራም በናይጄሪያ ሊያካሂድ ነው።

    ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋም ፌስቡክ፣ ተመራማሪዎች ሐሰተኛ ዘገባዎችን በተመለከተ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንዲረዳቸው ዋትስአፕ ይጠቀማሉ ብሏል።

    ይህ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም የናይጄሪያ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ከኮረናቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚያስተላልፏቸውን መልዕክቶች በገፁ ላይ ለማስተዋወቅ አቅዷል።

    የመረጃዎችን እውነተኛነት የሚያጣራው ተቋም፣ አፍሪካቼክ፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን በዩርባ፣ኢግቦ እና ሐወሳ ቋንቋዎች ያጣራል።

    ይህ የድርጅቱ እርምጃ ከተወሰኑ የአፍሪካ አገራት ጋር ሐሰተኛ መረጃን በፌስቡክና በኢንስታግራም ለመዋጋት የደረሰው ስምምነት አካል ነው ተብሏል።

    ኮሮናን እንፈውሳለን የሚሉ ሐሰተኛ ማስታወቂያዎችን እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማስታወቂያዎችም ይታገዳሉ ተብሏል።

  5. ሰበር, በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ሆነ

    የቫይረሱን ስርጭት የሚያመላክት ካርታ

    የፎቶው ባለመብት, John Hopkins

    የምስሉ መግለጫ, የቫይረሱን ስርጭት የሚያመላክት ካርታ

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዞች እንደሚጠቁሙት በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 201 ሺህ 436 ደርሷል።

    የሞቱ ሰዎች ቁጥር 8,006 ሲሆን በበሽታው ተይዘው የተፈወሱ ደግሞ 82,032 መሆኑን አሳውቋል።

    ቻይና፣ ጣሊያን እና ኢራን በርካታ በቫይረሱ የተያዙ እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች የሚገኙባቸው አገራት ናቸው።

  6. በኬኒያ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሰባት ደረሰ

    ኬኒያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው አገራት የሚመጡ የውጪ ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ከልክላለች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኬኒያ በዛሬው ዕለት ሦስት በቫይረሱ የተያሱ ሰዎችን ማግነቷን ገለፀች።

    ይህ በአጠቃላይ በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ሰባት አድርሶታል።

    የጤና ሚኒስትር የሆኑት ሙታኢ ካግዌ እንዳሉት ሁሉም ሕሙማን ከባህር ማዶ ወደ ኬኒያ የመጡ ናቸው ብለዋል።

    አሁን የተገኙት ሰዎች ከስፔን በዱባይ በኩል የመጡ ጥንዶች እንደሆኑ ተነግሯል።

    ሌላኛው ሕሙም ብሩንዲያዊ ሲሆኑ ከዱባይ መምጣታቸው ተነግሯል። መንግሥት ከእነዚህ ሶስት ሰዎች ጋር የተገናኙትን በሙሉ ክትትል እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

    ኬኒያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው አገራት የሚመጡ የውጪ ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ከልክላለች።

  7. ሰበር, ጣሊያን ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያውያን በኮሮናቫይረስ ተይዘው መሞታቸው ተሰማ

    የህክምና ሰራተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አውሮፓ ውስጥ በኮሮናቫይረስ [ኮቪድ-19] ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል ቀዳሚዋ በሆነችው ጣሊያን ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ አረጋገጠ።

    ኢትዮጵያዊያኑ እዚያው ጣሊያን ውስጥ በበሽታው ተይዘው ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ያናገራቸው የውጪ ጉዳይ ምንጮች አረጋግጠዋል።

    በወረርሽኙ የሞቱት ሁለቱም ሰዎች ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የነበረ ወንድና ሴት ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የታወቀ ሲሆን አንደኛው ለረጅም ዓመታት ጣሊያን ውስጥ የኖሩ መሆናቸውም ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።

    ሁለተኛዋ ሟች መቼ ወደ ጣሊያን እንደሄዱ በትክክል ባይገለጽም ቤተሰብ ለመጎብኘት ወደ ጣሊያን በመሄድ እዚያው የቆዩ እናት እንደሆኑ ታውቋል። ሁለቱም ሟቾች ህመሙ ከታየባቸው በኋላ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል ሲያደርጉ እንደቆዩና በመጨረሻም ለህልፈት መብቃታቸው ተገልጿል።

    የእዚህን ዜና ዝርዝር ዜና ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡

  8. የቬጋስ ማቋመሪያ ቤቶችም የኮሮናቫይረስ ሰለባ ሆነዋል

    ቬጋስ ኔዛዳ

    የአሜሪካ ዋነኛ የቁማር ከተማ በሆነችው በኔቬዳዋ ላስ ቬጋስ የሚገኙት የቁማር ቤቶች በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት ምክንያ ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ዝግ ይደረጋሉ።

    የላስ ቬጋስ ቁማር ማጫወቻ ቤቶች የሚታወቁት 24 ሰዓታት ለደንበኞቻቸው ክፍት በመሆን ነው።

    ለመጨረሻ ጊዜ በላስ ቬጋስ የሚገኙት ማቋመሪያ ቤቶች ዝግ የተደረጉት እአአ 1963 የጆን ኤፍ ኬኔዲ ሥርዓተ ቀብር በተካሄደበት ቀን ነበር።

    ምግብ ቤቶች ምግብ ለተጠቃሚዎች ባሉበት እንዲያደርሱ ወይም አዘው ይዘው የሚሄዱ ደንበኞቻቸውን ብቻ እንዲያስተናግዱ ተፈቅዶላቸዋል።

  9. ፈረንሳይ ከቤት ውጪ የሚገኝን ሰው በገንዘብ መቅጣት ጀመረች

    ኤፍል ማማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፈረንሳይ ሁሉም ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ ያስተላለፈችውን ጥብቅ ትዕዛዝ መተግበር ከጀመረች ሁለተኛ ቀኗን ይዛለች።

    ሕጉን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

    ሌ ሞንድ የተሰኘው የፈረንደሳይ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎች መቀጮ ከዛሬ ጀምሮ ከ38 ዩሮ ወደ 135 ዩሮ ከፍ ተደርጓል።

    ያለ አጥጋቢ ምክንያት በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ቢገኙ 138 ዩሮ እንዲቀጡ ይደረጋል።

  10. የሠራዊቱ አባላት ላልተወሰነ ጊዜ ከካምፕ ውጭ ያለ ሥራ መንቀሳቀስ የለባቸውም ተባለ

    የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopia News Agency

    የምስሉ መግለጫ, የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ

    የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ ሠራዊቱ ራሱን ከኮሮናቫይረስ እንዲጠብቅ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል።

    የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው የሠራዊቱ አባላት ላልተወሰነ ጊዜ ከካምፕ ውጭ ያለ ሥራ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

    በሽታውንም ለመከላከል በሁሉም ካምፖች በቂ የሆነ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እንደሚደረግ ኢታማዦር ሹሙ ተናግረዋል።

  11. ፍርድ ቤቶች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በከፊል ሊዘጉ ነው, ፍርድ ቤቶቹ ለ14 ቀን ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ተገልጿል

    የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከኮረናቫይረስ ጋር በተያያዘ በከፊል እንደሚዘጉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ አስታወቁ።

    ፍርድ ቤቶቹ ከመጋቢት 10 ጀምሮ ለ14 ቀናት ዝግ የሚሆኑ ሲሆን አዳዲስ መዝገቦችም አይከፈቱም ብለዋል።

    ከአገር ደህንነትና ፀጥታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብቻ እየተመዘኑ በተረኛ ችሎት ይታያሉ ማለታቸውም ተዘግቧል።

    ፍርድ ቤቶቹ ዝግ በሚሆኑባቸው ወቅት ቀጠሮ የነበራቸው ባለጉዳዮች ከመጋቢት 24 በኋላ ጉዳያቸው እንደሚታይ ጨምረው አስታውቀዋል።

  12. አንድም የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ያልተገኘባት ዚምባብዌ ብሔራዊ አደጋ አወጀች

    የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን የነፃነት በዓል ከበራ ወደ ሌላ ጊዜ አስተላልፈዋል

    የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተገናኘ ብሔራዊ አደጋ አወጁ።

    በአገሪቱ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ግን አለመኖሩ ተገልጿል።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም አገሪቱ በቅርቡ ልታከብር የነበረውን የነጻነት ቀን በዓል ለሌላ ጊዜ ያስተላለፉ ሲሆን ከአንድ መቶ ሰው በላይ መሰብሰብንም አግደዋል።

    ክልከላው የቤተ እምነቶችን ስብሰባ፣ ሠርግ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለ60 ቀናት እንዳይካሄዱ ይከለክላል።

    ፕሬዛዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ወደ አገሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎች ባይከለከሉም በቫይረሱ ከተጠቁ አገራት የሚመጡ ዜጎች ግን አይበረታቱም ብለዋል።

    ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ዚምባብዌያውያን ወደተለያዩ አገራት ጉዞ እንዳያደርጉ መክረዋል።

  13. በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ጨምሮ 116 ደረሰ

    በሰዎች እጅ ላይ ሳኒታይዘር ሲቀመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Gallo Images

    ደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ጨምሮ 116 መድረሱን አስታወቀች።

    አገሪቱ የቫይረረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ድንበሯንና ትምህርት ቤቶችንም ዘግታለች።

    በደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ቫይረሱ ያለበት ሰው የተገኘው ከአስራ አምስት ቀን በፊት የነበረ ሲሆን አሁን ግን ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ላይ ነው።

    በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙት አብዛኞቹ ከባህር ማዶ የገቡ መሆናቸው የተገለጠ ሲሆን በተለይ ከእንግሊዝ የገቡ ይበዛሉ ተብሏል።

    ቫይረሱ ካለባቸው ጋር በነበራቸው የቅርብ ንክኪ ብቻ የተያዙ 14 ሰዎች እንዳሉም ባለሰልጣናት ተናግረዋል።

    ከዛሬ እሮብ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን በቫይረሱ ከተጠቁ አገራት የሚመጡ የውጪ አገር ዜጎችንም እንዳይገቡ ተወስኗል።

  14. ሰዎች ስለኮሮና መረጃ እንዲያገኙ በኦሮሚያ የተዘጋው ኢንተርኔት እንዲከፈት ተጠየቀ

    ተንቀሳቃሽ ስልክ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኦሮሚያ የሃኪሞች ማህበር ነዋሪዎች ስለኮሮና መረጃ እንዲያገኙ በኦሮሚያ የተዘጋው ኢንተርኔት እንዲከፈት ጠየቁ።

    ማህበሩ ለጠቅላይ ሚንስትሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ ሰዎች ስለ ቫይረሱ ቀድመው ማወቃቸው በሽታው የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

    የማህበሩ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጂልቻ ዲሪቢ “በአሁኑ ሰዓት በበርካታ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት የለም። በዚህም ለህዝቡ ወቅታዊ እና ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ማድረስ አልተቻለም” ብለዋል።

    በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው ምዕራብ ሸዋ እና በአራቱ ወለጋ ዞኖች የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት የለም።

    የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ኢንተርኔት በተቋረጠባቸው አካባቢዎች የተለወጠ ነገር እንደሌለ መናገራቸው ይታወሳል።

  15. የልጅ ሚካኤል የጤና መልዕክት

    የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የተለያዩ አካላት የጤና መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።

    ድምፃዊ ልጅ ሚካኤል በኢንስታግራም ገፁ ላይ "በቆሸሸ እጃችን አንንካ ፊታችን" እያለ በማንጎራጎር መልዕክት አስተላልፏል።

    በኢንስታግራም ገፁ ላይ “ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በማንኛውም የስፖርት ዘርፍ ውስጥ ያላችሁ አትሌቶች፣ የህክምናና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም በጣም የምወዳችሁ አርቲስቶች ጓደኞቼ እናንተም ያላችሁን ይጠቅማል የምትሉትን ሙያዊ ምክርና እገዛ በማያስጨንቅና ዘና በሚያረግ መልኩ በቪዲዮ በመታገዝ ለሰዉ እንድታካፍሉ ” ሲል ጥሪውን አቅርቧል

    የ Instagram ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን Instagram ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ Instagram ይዘት መጨረሻ

  16. በክላሲካል ሙዚቃ ታጅበው እጅዎን ይታጠቡ

    ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ በርካታ የጤና መልዕክት የያዙ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ይለቀቃሉ።

    እጃችንን በአግባቡ እንድንታጠብ የሚያስተምሩ ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ከእነዚህ መካከል ይገኙበታል።

    በፈጠራ ክህሎታቸው ላቅ ያሉ እና እያዝናኑ ተገቢውን መልዕክት የሚያስተላልፉ አይጠፉም።

    በኢራን የሚገኘው ኮሜዲያን ይህንን አጭር ቪዲዮ ሰርቶ መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ኢራን በኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃች አገር መሆኗ ይታወቃል።

    የ Instagram ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን Instagram ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ Instagram ይዘት መጨረሻ

  17. ቱኒዚያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሰዓት እላፊ አወጀች

    የቱኒዚያ መዲና ቱኒዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የቱኒዚያ መንግሥት ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ጣለ።

    የአገሪቱ ፕሬዝደንት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ከምሽቱ 12 እስከ ንጋቱ 12 ድረስ ከቤት መውጣት አይቻልም ብለዋል።

    በቱኒዚያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ 24 ሰዎች ይገኛሉ።

  18. በታንዛኒያ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮና ተያዙ

    ጆን ማጉፉሊ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ቃሲም ማጃሊዋ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ገለፁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አንዱ ግለሰብ በዛንዚባር ሌላኛው ደግሞ በዳሬሰላም የሚገኙ ናቸው።

    በአሁን ሰዓት በታንዛኒያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሶስት ደርሷል።

  19. ደቡብ አፍሪካ በአንድ ቀን በኮሮና የተያዙ በርካታ ሰዎችን አገኘች, ደቡብ አፍሪካ በአንድ ቀን በኮሮና የተያዙ 23 ሰዎችን አገኘች

    በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ምግብ ቤቶች ደንበኞቻቸው ወደ ምግብ ቤቱ ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱ እያደረጉ ነው።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ምግብ ቤቶች ደንበኞቻቸው ወደ ምግብ ቤቱ ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱ እያደረጉ ነው።

    ደቡብ አፍሪካ በአንድ ቀን ብቻ 23 በኮሮና የተያዙ ሰዎችን በማግኘት ከፍተኛውን ቁጥር አስመዘገበች።

    ከ23ቱ ሰዎች መካከል 4ቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው ተብሏል።

    አሁን በደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ 85 ሰዎች ይገኛሉ።

    የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስትር 8ቱ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙት እዛው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሌሎች ሕሙማን ጋር በነበራቸው ንክኪ መሆኑን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፖሳ ኮሮና በብዛት ከሚገኝባቸው አገራት ወደ ደቡብ አፍሪካ ይደረጉ የነበሩ በረራዎችን መሰረዛቸው እና ብሔራዊ አደጋ ማወጃቸው ይታወሳል።

  20. የአውሮፓ ሕብረት የአገራቱን ድንበር ሊዘጋ ነው

    የፈረንሳይ ጀርመን ድንበር አካባቢ ፍተሻ ሲደረግ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የአውሮፓ ህብረት ከአባላት አገራቱ ዜጎች ውጪ የሚመጡ ሰዎችን ለ30 ቀናት እንዳይገቡ ሊከለክል መሆኑ ተሰማ።

    ውሳኔው በ26ቱ የአውሮፓ አገራት እንዲሁም አይስላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድና ሌቺቴንስቴይን ያካትታል ተብሏል።

    ይህ ውሳኔ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች አይመለከታቸውም።

    በአውሮፓ ቫይረሱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን 8ሺህ ያህል ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መሞታቸው ተመዝግቧል።

    በተያያዘ ዜና ዩሮ 2020 የእግር ኳስ ጨዋታ በአንድ ዓመት መገፋቱ ይታወሳል።

    እንደ ዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት መረጃ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ 200ሺህ ሰዎች ያህል በቫይረሱ ተይዘዋል።