ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 መዛመትን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ እመርታ ያሳዩ ስድስት ምርቶች

ሬቭ ቡና

የኮሮና ቫይረስ መዛመት እያሻቀበ ባለበት በአሁኑ ወቅት በንግዱ አለም ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳርፏል፤ ንግዶች አሽቆልቁለዋል፣ አንዳንዶችም ላያንሰራሩ ወድቀዋል። የአንዱ እርግማን ለአንዱ ምርቃን እንዲሉ የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ተከትሎ ንግዳቸው በከፍተኛ ሁኔታ እመርታ ያሳዩም ዘርፎች አሉ።

" አብዛኛውን ጊዜ በገና ወቅት ስራ ይበዛብናል" የሚለው በበይነመረብ (ኢንተርኔት) ላይ የቡና ሽያጭ አቅርቦት ባለቤት የሆነው ግለሰብ በአሁኑ ወቅት ሽያጫቸው በእጥፍ እንደጨመረ አልደበቀም።

እንዲሁም የተለያዩ ስፖርታዊ ቁሳቁሶችን የሚያቀርብ አንድ ድርጅትም በሸማቾች ፍላጎት እንደተጨናነቁ አሳውቋል። " ያለንን የጠረጴዛ ቴኒስ ሸጠን ጨርሰናል፤ አዲሱ የመፀዳጃ ወረቀት( ሶፍት) ነው ማለት ይቻላል" በማለት በቀልድ መልኩ ተናግሯል።

ቤተሰቦች በአንድ ቤት ውስጥ ታፍነው ከቤት መውጣት በማይችሉበት ሁኔታ ምን ማድረግ ይችላሉ፤ አዕምሯቸውን እንዲሁም አካላቸውን የሚያነቃቃ ነገር ይፈልጋሉ።

በዚህ ወቅት ሽያጫቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀቡ ያሉ ምርቶች የትኞቹ ናቸው?

ሳይክሎችና ስፖርታዊ ቁሳቁሶች

አካላዊ እንቅስቃሴም ለማድረግም ሆነ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ ሳይክሎች ተመራጭ ሆነዋል።

"ብዙዎች ነፃ ሆኜ መጓዝን እፈልጋለሁ ብለው ሲያስቡ ሳይክሎችን ይመርጣሉ" በማለት ብሮምተን የተባለው የሳይክል ኩባንያ ስራ አስፈፃሚ ዊል በትለር አዳምስ ይናገራሉ።

በተለይም በእንግሊዝ ባሉ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ጋር ሲወዳደር አስራ አምስት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ታዋቂው የለንደን ሳይክል መጠገኛም እንደቀድሞው ስራ አልጎደለበትም፤ ያረጁ ሳይክሎችን የህዝብ መመላለሻ ትራንሰፖርቶችን እንዲያስወግዱ በማለት ለደንበኞቻቸው ይጠግናሉ።

ሪቴይለን ሃልፎርድስ የተባለው ድርጅትም በሳይክል ሽያጭ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳስመዘገበ ሪፖርት አድርጓል "ከቤታቸው መውጣት የማይችሉ ሰዎችም ቤታቸው ውስጥ ሆነው አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይፈልጋሉ" ብሏል።

የፑል ጠረጴዛ
የምስሉ መግለጫ, በቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ ስፖርታዊ ቁሳቁሶች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው

ሚንቴል የተባለው በገበያ አቅርቦት ላይ ምርምር የሚሰራውን ድርጅት ኃላፊ ቶቢ ክላርክ በበኩሉ ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ ስፖርታዊ ቁሳቁሶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን፤ ወደ ስፖርት ቤቶች መሄድ ስለማይችሉም እሱን ለማካካስ በመፈለግ ይመስላል" ብሏል።

የቤትና የውጭ መጫወቻዎች

የተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታ አይነቶችን የሚያቀርበው አንዲ ቤሬስፎርድ እንደሚለው ከነበራቸው የክምችት ክፍል የጠረጴዛ ቴኒስ ሙሉ በሙሉ እንደተሸጠና ለዚህ ሳምንት ታዞ የነበረው ተሸጦ እንዳለቀ ነው።

"በዚህ ሳምንት 124 የጠረጴዛ ቴኒሶች ሸጫለሁ፤ በዚህ ወቅት አምና የሸጥኩት 15 ብቻ ነው"

በተለይም መንግሥት ትምህርት ቤቶች ይዘጉ የሚለውን እወጃ ተከትሎ ሽያጮች በከፍተኛ ሁኔታ ነው የጨመሩት።

ከጠረጴዛ ቴኒስ በተጨማሪ የፑል ጠረጴዛዎችም በሸማቾች በከፍተኛ ሁኔታ እንደተቸበቸቡ አንዲ ገልጿል።

ከነበረውም 500 የፑል ጠረጴዛ ግማሹን፣250፣ ሸጧል።

የቤት የእጅ ስራ መስሪያዎችና ለአትክልት ስፍራ የሚውሉ ዘሮች

ጀስት ሲድ የተባለ ድርጅት የተለያዩ አዝርዕት እንዲሁም አትክልት ዘሮችን ያቀርባል። ነገር ግን ከሰሞኑ ዘሮችን ማቅረብ እንደማይችል ድርጅቱን ወክሎ ፊል ጆንስ ተናግሯል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያቀረቡት ካሮት፣ ሰላጣና ቲማቲም የመሳሰሉ ዘሮች አቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ በገፍ በመጠያቃቸው ነው።

ጀስት ሲድ ብቻ አይደለም ሁለቱ ትልልቅ የዘር አምራች ኩባንያዎች ማርሻልስና ሰተንስም ስልካቸውን መመለስ አቁመዋል።

ለአንዳንድ ሸማቾች አትክልቶች ሊያጥሩ እንደሚችሉ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመግባት የሚገዙ ቢኖሩም፣ ለአብዛኛው ግን ዘሮችን የሚገዙት በትርፍ ጊዜያችን ምን እናድርግ በሚል እንደሆነ ፊል ይናገራል።

ብሮምፕተን የብስክሌት ፋብሪካ

ሌላኛው የዘር አከፋፋይ ፍራንቺ ሲድስም ድረገፁን ለአጭር ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ ያደረገ ሲሆን "ብዙዎች በፍራቻ በገፍ እየገዙም ነው" የሚል ምላሽም ሰጥቷል።

አትክልቶችን ከመትከል በተጨማሪ ብዙዎች በአንድ ቤት ውስጥ መታፈን ከሚያመጣው ድብርት ለመላቀቅ ወደ ሹራብ ስራ እንዲሁም ልብስ ስፌት እየተመለሱም ነው ተብሏል።

በለንደን ተቀማጭነቱን ያደረገ እንደ መደብርም የልብስ ስፌት ቁሳቁሶች ከባለፈው አመት ጋር ሲወዳደር በ380 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን እንዲሁም የእጅ ስራ መሳሪያዎች በ228 በመቶ ጭማሪም አሳይተዋል ተብሏል።

መፃህፍት

በአሁኑ ሰዓት ብዙዎች ከስራ ውጭ ቤታቸው ተቀምጠው ጊዜ በተትረፈረበት ሰዓት ወቅት መፃህፍትን በማንበብ ማሳለፍ አንዱ መንገድ ሆኗል። በተለይም የተለያዩ ሳይንሳዊ ልብወለድ ስራዎች በተለይም ስለ ወርርሽኝ የተፃፉት ተፈላጊነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ከአማዞን እንግሊዝ የተገኘን መረጃ ብናይ በዚህ ሳምንት በሽያጭ ደረጃ ሁለተኛ የሆነውን ብናይ 'The Eyes of Darkness' የተባለው መፅሀፍ ነው። ደራሲው ዲን ኩንትዝ ሲሆን የተፃፈበት ወቅትም እንደ ጎርጎሳውያኑ 1981 ነው። ውሃን- 400 ስለተባለ ቫይረስ የሚተርከው ይህ መፅሀፍ አሁን ስላለው ኮሮና ቫይረስ ትንቢት ነውም ተብሏል።

የዘር ከረጢቶች

ሌላኛው በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጠ ያለው መፅሀፍ በታዋቂው ፈረንሳያዊ ደራሲ አልበርት ካሙዝ የተፃፈው 'The Plague' የተሰኘው ነው። የእንግሊዙ አሳታሚ ፔንግዩን እንደሚለው በየካቲት መጨረሻ ሳምንት ላይ የነበረው ሽያጭ በ150 ፐርሰንት የጨመረ ሲሆን፤ እንደገና ወደማተምም ስራ ተገብቷል። መፅሀፉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸበቸበ ያለው በፈረንሳይና በጣልያን ነው።

የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች

ከተለያዩ ትልልቅ መደብሮች (ሱፐር ማርኬቶች) የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ግምት የሚያወጣ የምግብ ክምችት በየሰው ቤት ይገኛል።

ይሄ ሁሉ ግን የት ይሄዳል? ማስቀመጫ ሊኖረው ይገባል።

በዚህም ምክንያት የተለያዩ መጠን ያላቸው ፍሪጆችም ሆነ ማቀዝቀዣዎችን በተለያዩ ድረገፆች እየተፈለጉ በመሸመት ላይ ናቸው።

ፍሪጆች ብቻ አይደሉም ላፕቶፖችም ተፈላጊ ከሆኑት ቁሳቁሶች መካከል ሲሆን በተጨማሪ የቢሮ ቁሳቁሶችም እንዲሁ። በቤታቸው ሆነው የሚሰሩ ሰዎች ሶፋ ላይ ተንሰራፍተው መስራት ስለማይመች የቢሮ እቃዎቻቸውን እያስመጡ ነው።

ዲክሰንስ ካርፎን የተባለው ድርጅት እንዳሳወቀው ቤት ውስጥ ሆነው ለመስራት የሚያመቹ ላፕቶፖች፣ ማተሚያዎች እንዲሁም ለቤት መዝናኛ የሚሆኑ ቴሌቪዥኖች የተለያዩ የመጫዎቻ አይነቶችና እንዲሁም ማቀዝቀዣዎች፣ የማእድ ቤት ቁሳቁሶች በ23ፐርሰንት ጭማሪ አሳይቷል።

ቡና

የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ተከትሎ ባሳየው የፍላጎት ማሻቀብ ምክንያት ሬቭ ኮፊ ተጨማሪ ሰራተኞችን ለመቅጠር ተገዷል።

"አስራ አንድ ሰራተኞች ብቻ ነበሩን፤ ያለው ፍላጎት በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት አምስት ሰራተኞች አስፈልገውናል" በማለት ቪኪ ሆጅ የድርጅቱ ኃላፊ ተናግራለች።

"ከዚህ ቀደም ብዙዎች ቡናችንን ይገዙት የነበረው ለቢሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ለቤታቸው ነው" በማለት ቪኪ ገልፃለች።

"ምናልባት ለምሳሌ አንድ ሰው ቡና ከቢሮ ቢያዝ አስር ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው ሆነው ያዛሉ" ትላለች

ምንም እንኳን አንዳንድ የንግዱ ዘርፎች ጥሩ እየሰሩ ቢሆንም ቀውሱ እስካልተፈታ ድረስ ነገሮች በዚህ አይቀጥሉም።

የተለያዩ ስፖርታዊ ቁሳቁሶችን የሚሸጠው አንዲ ተጨማሪ የጠረጴዛ ቴኒሶችን ትእዛዝ እንዳይቀበል ያደረገው ምክንያት በፈረንሳይ፣ በስፔንና ጣልያን ያሉ ፋብሪካዎች በመዘጋታቸው ነው።

በዚህ ሳምንት መጨረሻም ቤት ለመቆየት ሃሳብ ያለው አንዲ አርባ ሰራተኞችን ያስተዳድራል። አርባ ሰራተኞቹን እንዲሁ ዝም ብሎ ከመበተን መንግሥት ደመወዛቸውን እንዲከፍላቸው የመጠየቅ ሃሳብ አለው።

ቪኪም በስጋት ላይ ናት ያላቸው ቢዝነስ ጥቃቅንና አነስተኛ ከሚባሉት አንዱ ከመሆኑ አንፃር በቅርቡ ሊዘጋ ይችላልም ትላለች።

ኮሮና