ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ እስከ ሠኔ ድረስ ከኮሮና ታገገምላች አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፌደራል የኮሮናቫይረስ መመሪያ መሰረት የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚያስችሉት አካላዊ እርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉ እርምጃዎች እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ እንደሚቆዩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ቀደም ሲል ፕሬዝዳንቱ እነዚህ እርምጃዎች በፈረንጆቹ ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በሚከበረው የፋሲካ በዓል ሰሞን ሊላሉ እንደሚችሉ ገልጸው ነበር።
ነገር ግን አሁን ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት "በሁለት ሳምንት ውስጥ በበሽታው ምክንያት የሚያጋጥመው ሞት ከፍተኛው ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችልበት እድል አለ" ብለዋል።
ትራምፕ ትናንት ዋይት ሐውስ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግብረ ኃይል ሥራዎችን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ አካላዊ እርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉት በሽታውን የመከላከያ መንገዶች "በአሸናፊነት ለመውጣት ዘዴ ነው" ብለዋል።
አክለውም አሜሪካ ሠኔ ወር ላይ "ከበሽታው ለማገገም ጉዞ ላይ ትሆናለች" ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በአሜሪካ ውስጥ በሁለት ሳማንት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጠር ከፍተኛው መጠን ላይ ይደርሳል ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ድል ከመገኘቱ በፊት ድልን ከማወጅ የከፋ ነገር የለም፤ ይህም ከሁሉ የባሰ ሽንፈት ነው" ብለዋል።
ተንታኞች እንዳሉት ግን ፕሬዝዳንቱ ስለከፍተኛው የወረርሽኙ "የሞት መጠንን" የጠቀሱበት ሁኔታ በአገሪቱ የሚከሰተውን አጠቃላይ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን አሃዝ ለማመልከት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ ሆስፒታሎች በታማሚዎች ሊጥለቀለቁ ይችላሉ የሚለው የበርካቶች ስጋት ትራምፕን ሳያሳስባቸው አልቀረም።
ቀደም ሲልም የዋይት ሐውስ የህክምና አማካሪ የሆኑት ዶክተር አንተኒ ፋውቺ ቫይረሱ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ አሜሪካዊያንን ሊገድል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።
ዶክተሩ ጨምረውም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች በኮሮናቫይረስ ሊያዙበት የሚችል ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ውስጥ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ከ140,000 ሺህ በላይ ህሙማን ይገኛሉ።
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በተጠናቀረው አሃዝ መሰረት እስከ ትናንት እሁድ ምሽት ድረስም 2,493 ሰዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
አሜሪካ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ብዛት ቀደም ብሎ በሽታው ተከስቶባቸው ከነበሩት ከቻይናና ጣሊያን መብለጧን ባለፈው ሳምንት የወጡ የበሽታው መስፋፋት ዘገባዎች አመልክተዋል።













