ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኒው ዮርክ ከተማን ለይቶ የመዝጋት ሃሳባቸውን አነሱ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኒው ዮርክ ከተማን ለይቶ የመዝጋት ሃሳብን ነቀፉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኒው ዮርክ ገዢ ከተማዋን በመለየት በሽታውን ለመቆጣጠር የቀረበው ሃሳብ የማይተማን እንደሆነ በመግለጽ "አስፈላጊ አይደለም" አሉ።

ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት የመጨረሻው ውሳኔ የሚሰጠው በዋይት ሃውስ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል ምክረ ሃሳብ መሰረት መሆኑን አመልክተዋል።

ቀደም ሲል ፕሬዝዳንቱ ኒው ዮርክን፣ ኒው ጀርሲንና ኮኔክትከትን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል በከፊል ዝግ ይደረጋሉ ማለታቸው ይታወሳል።

በኒው ዮርክ ብቻ ከ52 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ታማማሚዎች ይገኛሉ።

ይህም አሜሪካ ካላት የቫይረሱ ህሙማን መካከል ግማሾቹን ማለት ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት ከለይቶ ማቆያ ይልቅ በእነዚህ ግዛተቶች ጠንካራ የጉዞ ምክር ቢደረግ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሬዝዳንቱን ምክረ ሃሳብ ተከትሎም የበሽታ መከላከል ማዕከል በጣም አስፈላጊ ካልሆነ ለ14 ቀናት ምንም ጉዞ ባታደርጉ ይመረጣል በማለት በሦስቱ ግዛቶች የሚገኙ ነዋሪዎችን መክሯል።

ባለፈው ቅድሜ ከጋዜጠኞች በቀረበላቸው ጥያቄ "ኒው ዮርክን ሙሉ በሙሉ ለመለየት አቅጃለሁ፤ ምክንያቱም የቫይረሱ ከፍጠኛ ስርጭት የሚገኘው ኒው ዮርክ በመሆኑ" ብለው ነበር።

የኒው ዮርክ ገዥ አንድሪው ኮሞ ግን ይህ ምክረ ሃሳብ "አስደንጋጭ" እና "ጸረ አሜሪካዊያን ነው" ብለዋል። ከየትኛውም አካባቢ ጋር ኒው ዮርክ እንዳትገናኝ ማድረግ ሙሉ በሙሉ ግዛቷን መዝጋት ማለት ነው ያሉት ገዥው ኒው ዮርክ ራሷ ቀደም ብላ እርምጃዎችን መውሰዷን ገልጸዋል።

ሰዎች በብዛት እንዳይሰባሰቡና ከቤት እንዳይወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ገልጸው ኒው ዮርክን ሙሉ በሙሉ መዝጋት በሚለው ግን የማይስመማሙበት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። ምክንያታቸው ደግሞ በዚህ ደረጃ ኒው ዮርክ ሙሉ በሙሉ ከተዘጋች በአሜሪካ ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ውድቀት ያመጣል። ከውድቀቱ ለማገገምም ወራትን ሳይሆን ዓመታትን ሊጠይቅ እንደሚችል ገልጸዋል።

ኒው ዮርክ ውስጥ በሚቀጥሉት ከ14 እስከ 21 ቀናት ወረርሽኙ ሊከፋ እንደሚችል አስተዳዳሪው አስጠንቅቀዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ 30 ሺህ ለመተንፈሻ የሚያግዙ መሣሪያዎች ለኒው ዮርክ ብቻ የሚያስፈልጉ ሲሆን ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ የአንዱ ዋጋም እስከ 45 ሺህ ዶላር መድረሱ ታውቋል።

የወረርሽኙ በመስፋፋት በኒው ዮርክ አራት ተጨማሪ ጊዜያዊ ሆስፒታሎች እንዲገነቡ የቀረበውን ሃሳብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማጽደቃቸውንም የኒው ዮርክ ገዥው አንድሪው ኮሞ ገልጸዋል።

ኮሮና