ኮሮናቫይረስ፡ ሁለት ሰዎች ከኮቪድ-19 መዳናቸው ተገለፀ

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, FBC

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ 21 ሰዎች መካከል ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው መዳናቸው ተገለጸ።

ወረርሽኙ በአገሪቱ ውስጥ መከሰቱ ታውቆ ይፋ ከተደረገ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የህሙማኑ ቁጥሩ 21 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም ሁለት ሰዎች የሚሰጠውን ህክምና በአግባቡ ተከታትለው ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ የዳኑ መሆኑ ተገልጾ፤ ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጠቅሰዋል።

በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ህክምናና ለይቶ ማቆያ ማዕከል የሚሰሩ ሕክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ሰው በቫይረሱ መያዙ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ እረፍት የለሽ ሳምንት ማሳለፋቸውን በሐኪም የፌስቡክ ገጽ ላይ አስፍረው፤ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተሽሏቸው ማየታቸው ተስፋ እንደሚሰጣቸውና ይህም " ከምን ጊዜውም የበለጠ ጠንክረን ለመስራት ተነሳስተናል" ማለታቸው ተዘግቧል።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት

የሚፈልጉት ይዘት የለም

በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ ለተገኘባቸው ሰዎች በተዘጋጀው የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ 17 ህሙማን ሲኖሩ አንድ ታማሚ በጽኑ ህሙማን ከፍል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።

እስካሁን በሚመለከታቸው አካላት በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመዘገቡት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ህሙማን መካከል ኢትዮጵያዊያን 14፣ ጃፓናዊያን 4፣ አንዲት እንግሊዛዊት፣ አንድ ኦስትሪያዊና አንድ ሞሪሸሳዊ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርምረው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናዊያን ወደ አገራቸው የሄዱ ሲሆን ሁለት ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ድነዋል።

ስለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ በሽታው እንደተገኘባቸው የተገለጸው ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 21 ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 17 ነው።

እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል በጽኑ ከታመሙ አንድ የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ በስተቀር በበሽታው ምክንያት የሞተ ሰው እንደሌለ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኮሮና