ኮሮናቫይረስ፡ ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅና እራስን ለይቶ መቆየት ምንድንናቸው?

ብቻዋን የተቀመጠች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እጅን በአግባቡ ከመታጠብና ከማጽዳት በተጨማሪ ከሰዎች ጋር ያለንን የቀረበ ንክኪ ማስወገድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ወሳኝ እርምጃ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥና በሌሎችም አገራት ውስጥ ሁሉም ሰው እጅግ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከሰዎች ጋር እጅግ ተጠጋግቶና ንክኪን ማስወገድ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚደረጉ ጉዞዎችን አለማድረግ በጥብቅ እየተመከረ ነው።

ይህም ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅ በሚል በስፋት መልዕክቶች እየተላለፉ ነው። በእርግጥ ስንቶቻችን ይህንን በሽታውን ለመከላከል የሚያስችለውን ዋነኛ አማራጭ እየተገበርነው? በዙሪያችንስ ምን እየታዘብን ነው?

ምንም እንኳን የጤና ባለሙያዎችና የመንግሥት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ቢመክሩም በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ የሚሰፍሩ ጽሁፎችና እየተሰራጩ ያሉ ምስሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በርካቶች ማኅበራዊ እርቀትን በመጠበቅ በኩል ቸልተኝነት እንዳለ የሚያመልከቱ ናቸው።

በተጨማሪም ከኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክቶች ጋር የሚመሳሰሉ ከጉንፋን ጋር የሚያያዙ ምልክቶች ከታዩብን ደግሞ የህመሙ ምንነት እስኪለይ ስረስ ማኅበራዊ እርቀታችንን ከመጠበቅ ባሻገር ወደ ሌሎች በሽታውን ላለማጋባት እራሳችንን ለይተን ማቆየት ይጠበቅብናል።

በተለይ ከጉንፋን ጋር የሚዛመዱ ምልክቶች ለምሳሌም ትኩሳት፣ ማስነጠስና ደረቅ ሳል ካለብን ለቤተሰቦቻችንና በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ደኅንነት ስንል በቤታችን ውስጥ እራሳችንን ከሌሎች ለይተን ማቆየት ያስፈልገናል።

እነዚህ የኮሮናቫይረስን መስፋፋት ለመግታት ወሳኝ የሆኑት ሁለቱ እርምጃዎች ማላትም ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅና እራስን ለይቶ ማቆየትን በተመለከተ ልናውቅ የሚገቡን ነገሮች ምንድን ናቸው?

ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅ ማለት ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖርን አላስፈላጊ ቅርርብና ንክኪን ማስወገድ ማለት ነው።

ይህም ማለት በርካታ ሰዎች ሊገኙባቸው በሚችሉ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ መቀነስ ወይም ማስቀረት ነው።

ሁሉም ሰው በተለይ ደግሞ ከ70 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች፣ ነፍሰጡር ሴቶችና ከጉንፋን ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን መቀራረብ በማስወገድ እርቀታቸውን እንዲጠብቁ ይመከራል።

እንዴት አድርገን እርቀታችንን እንጠብቃለን?

  • የሚቻል ከሆነ ሥራችንን ከቤታችን ሆነን ማከናወን
  • አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎችን ማስቀረት
  • ቡና ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛዎችና ብዙ ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች እራስን ማራቅ
  • በተቻለ መጠን ከጓደኞችና ከቤተሰብ ጋር የሚደረግ መሰባሰብን ማስቀረት

ከማኅበራዊ ግንኙነት በምንርቅበት ጊዜ ምን ማድግ እንችላለን?

  • ከሌሎች ሰዎች በሁለት ሜትር መራቅ ከቻልን ከቤት ወጥተን በእግር መንሸራሸርና ዱብዱብ ማለት
  • የበሸታው ምልክት ከሌለባችሁ ለአረጋዊያን የቤተሰብ አባላትና ለጎረቤቶቻችሁ ድጋፍ ማድረግ
  • ወደ መደብሮች በመሄድ አስፈላጊ ሸቀጦችን መግዛት
ማኅበራዊ እርቀትን ስለመጠበቅ ስዕላዊ መግለቻ

እራስን ለይቶ መቆየት ማለት ምን ማለት ነው?

እራስን ለይቶ መቆየት ማለት ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካልሆነ በስተቀር በቤት ውስጥ ሆኖ መቆየት ማለት ነው። ይህም ሲባል በየትኛውም ሰዓት ወደ ሥራ፣ ትምህት ቤትና በርካታ ሰው ወደ ሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች አለመሄድ ማለት ነው።

የሚቻል ከሆነም ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት ከቤት አለመውጣትን ያካትታል። ካልሆነ ግን ከቤት በሚወጣበት ጊዜ ከሰዎች ጋር የሚኖረንን መቀራረብና ንክኪ ለመቀነስ የተቻለንን ያህል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

እራስን ለይቶ መቆየት ያለበት ማነው?

የኮሮናቫይረስ በሽታ ምክልቶች የሆኑት ትኩሳት፣ የማይቆም ሳልና የመተንፈስ ችግር ያጋጠመው እንዲሁም ምልክቶቹ ከታዩበት ሰው ጋር በአንድ ቤት የሚኖር ማንኛውም ሰው እራሱን ለይቶ ማቆየት ይኖርበታል።

  • ብቻውን የሚኖር ሰው ምልክቶቹ ከታዩበት ቀን ጀምሮ ለሰባት ቀናት ከቤቱ ሳይወጣ መቆየት አለበት
  • እራሳችን ወይም አብሮን የሚኖር ሰው ላይ ምልክቶች ከታዩ መላው ቤተሰብ ለ14 ቀናት እራሱን ለይቶ መቆየት አለበት
  • በ14 ቀናቱ ውስጥ ተጨማሪ ምልክቶች ማሳየት የጀመረ ሰው ካለ ከመጀመሪያ ተጨማሪ ሰባት ቀናትን እራሱን ለይቶ ማቆየት አለበት

ምልክቶቹ የታየበት ሰው በቤቱ ውስጥ ካሉት ሌሎች ሰዎች ተለይቶ መስኮት ባለውና አየር በደንብ በሚያገኝ ክፍል ውስጥ ተለይቶ መቆየት አለበት።

ሌሎችስ እነማን ናቸው እራሳቸውን ለይተው መቆየት ያለባቸው?

ቀደም ያለና ከባድ የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በቫይረሱ ከመያዝ ለመጠበቅ በልዩ ለይቶ የማቆያና የቅድም ጥንቃቄ እርምጃዎች ስር ለ12 ሳምንታት ተለይተው እንዲቆዩ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህም ሰዎች የሚከተሉት ያካትታል፡

  • የኬሞቴራፒና የጨረር ህክምና ላይ ያሉ የካንሰር ህሙማን
  • የአካል ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ሰዎች
  • በካበድ በሽታ የተያዙ ወይም የኩላሊት እጥበት የሚደረግላቸው ሰዎች
  • ከባድ የአስም ህመምና ሌላም ከባድ ህመም ያለባቸው ሰዎች

እራሳችንን ለይተን በምንቆይበት ጊዜ በቀላሉ ለጉዳት የተጋለጡ ሰዎች አብረውን የሚኖሩ ከሆነ ምን ማድረግ አለብን?

በእድሜ የገፉ ሰዎች፣ ነፍሰጡር ሴቶችና ሌላ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች አብረውን የሚኖሩ ከሆነ፤ እራሳችንን ለይተን በምንቆይበት ጊዜ ከእነዚህ ሰዎች ቢያንስ በሁለት ሜትር መራቅ አለብን።

ማእድ ቤትንና ሌሎች በጋራ በምንቆይባቸው ክፍሎች ውስጥ አብረን የምናሳልፈው ጊዜ የተወሰነ እንዲሆን ማድረግና በክፍሎቹ ውስጥ አየር እንደ ልብ እንዲገባ ማድረግ ይኖርብናል። የሚቻል ከሆነም እነዚህ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ተለይተው ምግባቸውን በክፍላቸው ውስጥ እንዲመገቡ ማድረግ።

የምንጠቀምባቸው ፎጣዎችን መለየት ከተጠቀሙ በኋላ ለንክኪ የተጋለጡ የመታጠቢያ ቤት መገልገያዎችን ማጽዳትና ንጽህናቸውን በአግባቡ መጠበቅ። የሚቻል ከሆነም የተለየ መጸዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ ማድረግ።

እራሳቸውን ለይተው በመቆየት ላይ ካሉ ሰዎች ጋር የሚኖሩ ሰዎች በተለይ በየትኛውም አጋጣሚ ንክኪ ካላቸው ወይም እቃዎችን ከነኩ በኋላ አዘውትረው እጃቸውን ለ20 ሰከንዶች በሳሙናና በውሃ መታጠብ ይኖርባቸዋል።

ለጽዳት የተጠቀምንባቸውን ሶፍትን የመሳሰሉ ቆሻሻዎችን በድርብ የፕላስቲክ መያዣ ውስጥ ለ72 ሰዓታት ለይቶ በጥንቃቄ በማስቀመጥ ከዚያም ከሌሎች ቆሻሻዎች ጋር እንዲወገድ ማድረግ ያስፈልጋል።

ስለዚህም ከኮሮናቫይረስ እራሳችንንና ሌሎችን ለመጠበቅ የግድ ካልሆነ በስተቀር በቤታችን ውስጥ መቆየት ወሳኝ እርምጃ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን በየትኛውም ቦታና አጋጣሚ መገኘት ካለብን ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረን እርቀት ከሁለት ሜትር ያነሰ እንዳይሆን ማድረግ አለብን። ይህም ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅ ማለት ይሆናል።

በተጨማሪም የበሽታው ምልክቶች በእራሳችንም ሆነ ከእኛ ጋር የቅርብ ንክኪ ባላቸው ሰዎች ላይ ከታየ ከሰባት እስከ 14 ቀናት እራሳችን ከሌሎች ሰዎች ለይተን በቤት ውስጥ በማቆየት የበሽታው ሁኔታ እስኪለይ ድረስ መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህም እራስን ለይቶ ማቆየት እርምጃ ነው።

ከዚህ ባሻገር ስለበሽታውና ስላለንበት ለቅርብ ሰዎቻችን ማሳወቅ እንዲሁም ድጋፍ ለማድረግ በተዘጋጁ የነጻ የስልክ መስመሮች 8335 ወይም 952 ላይ በመደወል ምክርና ድጋፍ ማግኘት ይቻላል።

ኮሮና