አሜሪካ ከህዳሴ ግድብ አደራዳሪነት እንድትወጣ የሚጠይቀው የዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, TASEW MELAKEHIWOT
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙርያ የሚያደርጉትን ድርድር የአሜሪካ መንግሥት ቀደሞ በታዛቢነት አሁን ደግሞ በአደራዳሪነት መግባቱን በመቃወም በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
የሰልፉ አስተባባሪ እና የዲሲ ግብረ ኃይል ተወካይ አቶ ጣሰው መላከሕይወት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ዋነኛ ጥያቄያቸው አሜሪካ ከአደራዳሪነት እንድትወጣ ነው። አሜሪካ እንዲሁም የዓለም ባንክ ከአደራዳሪነት ወደ ታዛቢነት እንዲመለሱ እንደሚፈልጉም አክለዋል።
"ሰልፉን የጠራነው የአሜሪካ መንግሥት ቀደም ሲል በታዛቢነት አሁን ደግሞ በአደራዳሪነት ለመግባት ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለሆነ፤ ያንን ተጽዕኖ ከኢትዮጵያ እንዲያነሳ ለመጠየቅ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተጽዕኖ የሚመጣ ስምምነትን እንደማይቀበሉ ለማሳወቅና የኢትዮጵያ መንግሥትም የበርካቶች ህልውና የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን በተመለከተ በተጽዕኖ ስምምነት እንዳይፈርም ለመጠየቅ ሰልፉ እንዳስፈለገም አብራርተዋል።
አቶ ጣሰውን ያነጋገርናቸው ሰልፉ መካሄድ በጀመረበት ሰዓት ሲሆን፤ ወደ አንድ መቶ ሰዎች ገደማ እንደተገኙ ለቢቢሲ ገልጸው እየጨመረም ይመጣል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, TASEW MELAKEHIWOT
"አገር ውስጥ ባለው ፖለቲካ የተለያየ አቋም ቢኖረንም በአገር ህልውና ላይ በተመሰረተው በአባይ ጉዳይ በጋራ እንደምንቆም፣ በጋራ ድምጻችንን እንደምናሰማ የሚገልጹ መፈክሮች አሉን" ሲሉ አስተባባሪው ተናግረዋል።
መንግሥት በግድቡ ጉዳይ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲወያይና ያሚካሄደውን ነገር ለሕዝብ እንዲያሳውቅ የሚያሳስቡ መፈክሮች የሰላማዊ ሰልፉ አካል እንደሆኑም አቶ ጣሰው አክለዋል።
አሜሪካንም ትሁን ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዳያሳድሩ ለመጠየቅ ከሰልፍ ባሻገር በየአካባቢያቸው ያሉ የሕዝብ ተወካዮችንና የመንግሥት ተቋሞችን የመድረስ እቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ሰልፉን ያስተባበሩት ዲሲ ግብረ ኃይል፣ መደመር በተግባር፣ ኢትዮጵያን-አሜሪካን ሲቪል ካውንስል የተባሉ ስብስቦች እንዲሁም የመብት ተሟጋቾችም ጭምር ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, TASEW MELAKEHIWOT
ኢትዮጵያ በዋሽንግተን የመጨረሻ ቀጠሮ ተይዞለት በነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጣይ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ ለአሜሪካ ማሳወቋ ይታወሳል።












