[ምልከታ] ፡ ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር አለመግባባት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ
    • ፀሐፊ, በአሌክስ ደ ዋል*
    • የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ተንታኝ

በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ለዘመናት በቆየው ውዝግብ ምክንያት በሁለቱ አገራት ሠራዊቶች መካከል የሚደረግ ግልጽ ወታደራዊ ግጭት ከዚህ በፊት እምብዛም አጋጥሞ ባያውቅም በቅርቡ በድንበር አካባቢ የታየው ሁኔታ ግን ነገሮች እየተቀየሩ መሆናቸውን ያመለክታል።

ለዚህ ችግር ቀዳሚ ምክንያት የሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ግዛት ከሆነው ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰነውና የሱዳን የዳቦ ቅርጫት ተብሎ በሚጠራው የገዳሪፍ ግዛት ውስጥ በሚገኘው አል ፋሻጋ አካባቢ የግዛት ይገባኛል ነው።

ሁለቱን አገራት የሚለየው ድንበር መልክአ ምድራዊ አቀማመጦችን በመጥቀስ ከሚገለጸው ውጪ በመሬት ላይ በግልጽ ተለይቶ የተካለለ አይደለም።

የቅኝ ግዛት ስምምነቶች

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ድንበሮች በጣሙን አወዛጋቢ ናቸው። ከአስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በኦጋዴን የተነሳ ጦርነት አድርገዋል።

እንዲሁም ከ20 ዓመታት በፊት ደግሞ በትንሿ ባድመ ይገባኝል ምክንያት ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር።

በጦርነቱ 80 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮች መሞታቸው የሚነገር ሲሆን በዚህም ምክንያት በሁለቱ አገራት ፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል። በተለይ ደግሞ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለኤርትራ ከወሰናቸው ግዛቶች ኢትዮጵያ ለመውጣት ፈቃደኛ ባለመሆኗ አለመግባባቱ ለዓመታት ቆይቷል።

እነዚህ ቦታዎች በዚህ ዓመት በትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች መልሰው ተቆጠጥረዋቸዋል።

ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያና ሱዳን ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን 744 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ድንበራቸውን ለይቶ ለማመላከት የሚያስችል ንግግርን መልሰው ጀመሩ።

በዚህ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆነው አካባቢ ፋሽጋ የሚባለው ነበር። በ1902 እና በ1907 (እአአ) የነበረው የቅኝ ግዛት ስምምነት መሰረት ዓለም አቀፉ ድንበር ወደ ምሥራቅ ይዘልቃል።

በዚህም ሳቢያ መሬቱ ወደ ሱዳን የሚካተት ይሆናል። ነገር ግን ቦታው ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ሲሆን የግብርና ሥራ በማከናወንም የሚጠበቅባቸውን ግብር ለኢትዮጵያ መንግሥት ሲከፍሉ ቆይተዋል።

የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት አወዛጋቢውን ቦታ ይዘው እንደሚቆዩ አሳውቀዋል

'ድብቅ ስምምነት'

ሁለቱ አገራት ሲደረጉ በነበረው የድንበር ድርድር አማካይነት በ2008 (እአአ) ላይ ከመግባባት ደረሱ። በዚህም ኢትዮጵያ ለሕጋዊው ድንበር ዕውቅና ስትሰጥ ሱዳን ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ በስፍራው ያለችግር ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀደች።

ይህም አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በድንበር አካባቢ ያሉ የነዋሪዎችን ህይወት ሳያደናቅፍ ኢትዮጵያ ግልጽ የድንበር መለያ እንዲኖር እስክትጠይቅ ድረስ ቀጥሎ ነበር።

በሁለቱ አገራት መካከል ከስምምነት የተደረሰበትን የዚህ የድርድር ልዑክ የተመራው የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣን በሆኑት በአባይ ፀሐዬ ነበር።

ህወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት ስልጣን ሲወገድ የአማራ ብሔር መሪዎች ከሱዳን ጋር የተደረሰው ስምምነት በአግባቡ ሳያውቁት የተደረገ ድብቅ ውል ነው ሲሉ ተቃውመውታል።

በአሁኑ ጊዜ በፋሽጋ አካባቢ ለተከሰተው ግጭት ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ምክንያት ያቀርባሉ። ነገር ግን የተከሰተው የሚያከራክር አይደለም፤ በዚህም የሱዳን ሠራዊት ኢትዮጵያዉያኑን ከሚኖሩባቸው መንደሮች ለቀው እንዲወጡ አድርጓል።

በቅርቡ ጂቡቲ ውስጥ በተካሄደው ቀጠናዊ የኢጋድ ጉባኤ ላይ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጉዳዩን ከኢትዮጵያው አቻቸው ዐብይ አህመድ ጋር አንስተው ተወያይተዋል።

ስለድንበሩ ጉዳይ ድርድር ለማድረግ ቢስማሙም ሁለቱም የየራሳቸውን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸውን ማኅበረሰቦች ሱዳን እንደትክስ ስትጠይቅ፤ ሱዳን በበኩሏ ነገሮች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ትፈልጋለች።

በበርካታ የድንበር ውዝግቦች ውስጥ እንደሚያጋጥመው ሁሉም ወገን የተለያየ የታሪክ፣ የሕግና ለዘመናት የቆዩ ስምምነቶችን እንዴት መተርጎም እንዳለባቸው የየራሱ ትንታኔ አለው። ነገር ግን ይህ የሁለት ጉዳዮች ማሳያ ምልክት ነው፤ ይህም ከጠቅላይ ሚኒስርት ዐብይ የፖሊሲ ለውጥ ጋር የሚያያዝ ነው።

የአማራ ክልል ኃይሎች በሁመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአማራ ክልል ኃይሎች በሁመራ

ግዛት ይገባኛል

በፋሽጋ አካባቢ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን የአማራ ብሔር አባላት ናቸው። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ትልቁ ከሆነው የኦሮሞ ብሔር በኩል የነበራቸው ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ትኩረት ያደረጉበት ማኅበረሰብ ነው። አማራ በአገሪቱ ሁለተኛው ትልቁ ብሔር ሲሆን በአገሪቱ የመሪነት ስፍራም ታሪካዊ ስፍራ አለው።

ከወር በፊት የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል በህወሓት ኃይሎች ላይ ድል መቀዳጀቱን ተከትሎ የአማራ ክልል የግዛት ይገባኛል ጥያቄን እያነሳ ነው።

የህወሓት ኃይሎች ሽንፈት ሲገጥማቸውና የአማራ ክልል ሚሊሻ ጥያቄ የተነሳባቸውን አካባቢዎች ሲቆጣጠር የራሱን ባንዲራ በመስቀል "ወደ አማራ ክልል እንኳን ደህና መጡ" የሚሉ የመንገድ ምልክቶችን አስቀምጧል። ቦታዎቹ በአማራ ክልል ጥያቄ የሚቀርብባቸው ሲሆን ወደ ትግራይ ክልል የተጠቃለሉት ህወሓት ስልጣን በያዘበት ጊዜ ነበር።

ምንም እንኳን ጉዳዩ የውስጣዊ የድንበር ጉዳይ ሳይሆን ከጎረቤት አገር ጋር ያለ የግዛት ጉዳይ ቢሆንም፤ የፋሽጋው ግጭትም ተመሳሳይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄን የተከተለ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የውጭ ግንኙነት የፖሊሲ ለውጥ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዳይፈታ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ምክንያት ሆኗል። ለ60 ዓመታት የኢትዮጵያ ስትራተጂካዊ ዓላማ ግብጽን መግታት ላይ ያተኮረ ነበር። ነገር ግን ከዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወዳጅነት እጃቸውን ዘርግተዋል።

ኢትዮጵያና ግብጽ የአባይ ወንዝን የህልውናቸው ጥያቄ አድርገው ይመለከቱታል።

ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን ተቀመጡ ስምምነቶችን መሠረት አድርጋ በላይኛው የተፋሰሱ አገራት ውስጥ የሚገነቡ ግድቦች በውሃ ድርሻዋ ላይ የተጋረጡ አደጋዎች እንደሆኑ ትመለከታቸዋለች።

ኢትዮጵያ ደግሞ የአባይ ወንዝን ለምታደርገው የኢኮኖሚ ልማት በጣሙን አስፋላጊ ለሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛ ምንጭ አድርጋ ትመለከተዋለች።

በግዙፉ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ውዝግብ የተነሳውም በዚህ ሳቢያ ነው።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚያካሂደው የውሃ ዲፕሎማሲ ዋነኛው መሰረቱ በቀሪዎቹ የአባይ ወንዝ የላይኛው ተፋሰስ የአፍሪካ አገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው የትብብር መዋቅር ነበር።

ዓላማውም በርካታ አገራትን ያካተተ በአባይ ወንዝ የውሃ ክፍፍል ላይ አጠቃላይ ስምምነት መድረስ ነበር። በዚህ መድረክ ላይም ግብጽ በቁጥር ተበልጣ የበላይነትን ማግኘት አልቻለችም።

ህዳሴው ግድብም ጎርፍን በመቆጣጠር፣ የመስኖ ልማቷን በመጨመርና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት እንደሚያስችላት በመረዳት፤ ሱዳንም ከቀሪዎቹ የአፍሪካ አገራት ወገን ተሰልፋ ነበር።

ግብጽ ግን በቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ላይ የተቀመጠውን አብዛኛውን የአባይ ወንዝን ውሃ ለማግኘት የሚያስችላትን ጥቅም ለማስከበር ቀጥተኛ የሁለትዮሽ ድርድር ፈልጋ ነበር።

በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስርት ዐብይ በሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ ሶቺ በሄዱበት ጊዜ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲሰ ጋር ተገናኝተው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ባልተገኙበት በዚህ ውይይት ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ላይ ከምትከተለው ስትራተጂ ውጪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዝዳንት አል ሲሲ የቀረበውን በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ አሜሪካ በአሸማጋይነት እንድትገባ የቀረበውን ሐሳብ ተቀበሉት። በዚህም ሂደት አሜሪካ ከግብጽ ጎን ቆመች።

ከኤርትራ ጋር የነበረውን ውጥረት ለማስወገድ የቻሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ ከግብጽ ጋርም ከስምምነት እንደሚደርሱ አስበው ነበር፤ ግን አልሆነም። እንዲያውም እራሳቸውን አጣብቂኝ ውስጥ አስገቡ።

በዋሽንግተኑ ድርድር ላይ የተጋበዘችው አገር ለዓመታት በአሜሪካ ሽብርተኞችን ከሚደገፉ መንግሥታት ዝርዝር ውስጥ ገብታ የገንዘብ ማዕቀብ ስር የቆየችውና ለአሜሪካ ተጽእኖ ተጋላጭ የሆነችው ሱዳን ነበረች። በድርድሩም ሱዳን ከግብጽ ጋር ተስማምታ ቆመች።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ አሜሪካ ያቀረበችው የስምምነት ሐሳብ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፤ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳቡን ውድቅ ለማድረፈግ ተገደዱ። ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው እርዳታ የተወሰነውን አገደች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንትም ግብጽ የህዳሴውን ግድብ "ልታፈነዳው" ትችላለች ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ግድቡ በሚገነባበት አካባቢ ማንኛውም በረራ እንዳይካሄድ አደረገች።

የጢስ አባይ ፏፏቴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አብዛኛው የአባይ ውሃ የሚመነጨው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ገባር ወንዞች ነው

ተቃዋሚዎችን መደገፍ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትግራይ ውስጥ ከተከሰተው ግጭትና በሱዳን ድንበር ካለው ውጥረት በተጨማሪ ከግብጽ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባት አይችሉም። ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ችግር በታሪክ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ውዝግብ መልሶ እንዲያንሰራራ አድርጎታል።

ከአርባ ዓመታት በፊት ሱዳን ህወሓትን ጨምሮ የብሔር ሸማቂ ቡድኖችን ስታስታጥቅ የኢትዮጵያው ወታደራዊ መንግሥት ደግሞ የሱዳን አማጺያንን ይረዳ ነበር። በአውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ ሱዳን ታጣቂ እስላማዊ ቡድኖችን ስትደግፍ ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳን ተቃዋሚዎችን ትረዳ ነበር።

በትጥቅ የተደገፉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ በሚያጋጥሙበት በዚህ ጊዜ፤ ሱዳን በቅርቡ የተሟላ ባይሆንም በዳርፉርና በኑቢያ ተራሮች ካሉ አማጽያን ጋር የሰላም ስምምነት ደርሳለች። በዚህ ሁኔታም አገራቱ ወደ ቆየው አንዳቸው የአንዳቸውን ሠላም ወደ ሚያናጋ ተግባር ሊመለሱ ይችላሉ።

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍተኛ ከሚባለው ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ካርቱም ሄደው አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የዲሞክራሲ መብት ጠያቂ ተቃዋሚዎችና የአገሪቱ ጀነራሎች የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰርቱ ድጋፍ ባደረጉበት ጊዜ ነው።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክም ውለታቸውን ለመመለስ በትግራይ ግጭት በተከሰተበት ጊዜ መፍትሄ ለማምጣት ለማሸማገል ሙከራ አድርገው ነበር። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይዋን በራሷ ትወጣዋለች በሚል ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ረሃብና አሰቃቂ ታሪክ ያላቸው ስደተኞች ከትግራይ ወደ ሱዳን እየሄዱ ባሉበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽምግልናውን ላለመቀበል የበለጠ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል።

ምናልባትም በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ ዙር ድንበር ተሻጋሪ ጠላትነት ሊቀሰቀስ የሚችልበት ስጋት ያለ ሲሆን ይህም የቀጠናውን ቀውስ ሊያባብሰው ይችላል።

Short presentational grey line

*አሌክስ ደ ዋል በአሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የፍሌቸር የሕግና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ነው።