በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ ባለው ችግር ጉዳት መድረሱ ተነገረ

ካርታ

ሰሞኑን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታየበት ባለው ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ በነዋሪዎች ጉዳት ሲደርስ በርካቶች ደግሞ መፈናቀላቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለቢበሲ እንዳስታወቁት በግጭቱ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ሁለቱ መሞታቸውን ጠቅሰው ከ1700 በላይ ሰዎች ከድንበሩ አካባቢ መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ እስከ 200 የሚጠጉ አርሶ አደሮች ለዘመናት ያፈሩት ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት በሱዳን ወታደሮች ወድሞባቸዋል ብለዋል።

የሱዳኑ የማስታወቂያ ሚንስትር የአገራቸው ወታደሮች በሁለቱ አገራት አዋሳኝ የድንበር አካባቢ በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ተይዞ የቆየ ካሉት መሬት ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠራቸውን ባለፈው ቅዳሜ ዕለት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

"ማንኛውም ችግር በውይይት ይፈታል ብለን እናምናለን" ብለዋል የማስታወቂያ ሚንስትሩ ፋይሳል ሳሊህ። "ነገር ግን ሠራዊታችን መሬታችንን ለማስመለስ ኃላፊነቱን ይወጣል። በዚህም በአሁኑ ጊዜ ከ60 አስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሱዳን መሬትን መልሶ ይዟል" በማለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በአወዛጋቢው የድንበር አካባቢ ያለው የምዕራብ ጎንደር አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የሱዳን ሠራዊት በድንበር አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ከጥቅምት ወር ማብቂያ ጀምሮ ነበር።

"ምንም እንኳን የሱዳኖች እንቅስቃሴ ጥቅምት 27 ጀምሮ የንብረት ጉዳትን ቢያደርስም በሰው ላይ ጉዳት ስላላደረሰ ነገሮችን ሳናሰፋና ሳናጋንን ለመያዝ ሞክረን ነበር" ብለዋል አስተዳዳሪው።

ሆኖም የሱዳን ወታደሮች አንዳንድ ቦታዎችን መያዝ በመጀመራቸው ይህንንም ተግባር ማቆም እንዳለባቸው መነጋገራቸውን የሚጠቅሱት አቶ ደሳለኝ፤ "በኅዳር 3 እና 4 በነበሩት ቀናት አዳዲስ ቦታዎችን በመያዝ የአርሶ አደር ካምፖችን ማቃጠል እና ጉዳት ማድረስ እስከ ትላንትና ድረስም ቀጥሏል" ሲሉ ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎንደር አስተዳዳሪው እንደሚሉት የሱዳን ወታደሮች በአካባቢው ለተከታታይ ቀናት በወሰዱት እርምጃ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውና ንብረት መውደሙን አመልክተዋል።

"የአርሶ አደሩ የተለያዩ ንብረቶች፣ ማሽኖች፣ መጋዘኖች እና እህል በማቃጠል ቀሪውን ደግሞ ሰብስበው ወስደዋል" በማለት ጨምረውም "የማሽላና የጥጥ ምርቶችን እየሰበሰቡ ወደ ቀጠናቸው አጓጉዘዋል" በማለት ሌሎች ንብረቶችን ማቃጠላቸውን ተናግረዋል።

በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ "ሠላም በር በምትባል መለስተኛ ቀበሌ ከ400 አስከ 500 የሚደርስ አርሶ አደር የሚኖርባት መንደራቸውን ለቀው እንዲወጡ ሆነዋል። በዚህም ወደ 1750 የሚሆኑ ቤተሰቦች ለመፈናቀል ታዳርገዋል" ሲሉ አስረድተዋል።

በድንበር አካባቢው ግጭት እንደነበረ ለሮይተርስ የተናገሩት የሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር፤ ወታደሮቻቸው የመከላከል እርምጃ መውሰዳቸውን አመልክተው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ግጭቶች ጋብ ማለታቸውን ተናግረው ነበር።

ሳሊህ ጨምረውም "የሱዳን የደኅንነት ሪፖርት እንዳረጋገጠው ሠራዊቱ የገጠማቸው ኃይሎች ከአደረጃጀት፣ ከስልጠናና ከትጥቅ አንጻር መደበኛ ኃይል እንጂ ሚሊሻ አይደለም" በማለት ግጭቱ ከየትኛው ኃይል ጋር እንደሆነ አመልክተዋል።

በድንበሩ አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ያጋጥሙና በቀላሉ መፍትሔ ያገኙ እንደነበር የተናገሩት የምዕራብ ጎንደር ዞን እተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ የአሁኑ ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የአሁኑ የተደራጀ ሜካናይዝድ ሠራዊት በማሰለፍ በርከት ባለ ከባድ መሣሪያ ታገዞ የተካሄደ ጥቃት ነው። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ደርሰውባቸው ወደማያውቁ አዳዲስ ቀጠናዎችን ጭምር ለመያዝ አላማ ያደረገ ነው" ብለዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ወደ ግጭት አንዳይገባ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሚገልጹት የምዕራብ ጎንደር አስተዳዳሪ "ሕዝቡ እራሱን ለመከላከል ቢችልም ሁሉም ነገር ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንደሚከናወን እያስረዳን ነው። ነገር ግን ይህ ሁኔታ በመንግሥት መፍትሔ ካላገኘ ነገሮች ሲበዙ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳያመሩ ስጋት አለ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ አገራት በጉዳዩ ላይ በመንግሥት ደረጃ ግንኙነት ማድረጋቸውን ገልፀው፤ ግጭቱን "የሱዳን መንግሥት ፍላጎት አይደለም" በማለት በስፍራው ባለ የሱዳን መንግሥት መዋቅር ውስጥ በተከሰተ ችግር ምክንያት የተከሰተ መሆኑን አመልክተዋል።

በድንበር አካባቢ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን ባለፈው ሳምንት ወደ ሱዳን በመሄድ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መወያያታቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት አካባቢ ያልተቋጨ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ያለ ሲሆን፤ በተለያዩ ጊዜም በድንበር አካባቢ ግጭቶች እንደሚከሰቱ ሲዘገብ ቆይቷል።

የሁለቱ አገራት መንግሥታትም ለረዥም ጊዜ ለቆየው ለዚህ የድንበር ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት በሚል የጋራ የድንበር ኮሚሽን አዋቅረው ተከታታይ ውይይቶችን ቢያደርጉም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ እስካሁን ዘልቋል።