ድንበር አካባቢ የተከሰተው ግጭት "የሱዳን መንግሥት የታችኛው እርከን ችግር ነው"- ኢትዮጵያ

የሱዳን መከላከያ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ የተከሰተው ግጭት በስፍራው ባለ የሱዳን መንግሥት መዋቅር ውስጥ በተከሰተ ችግር ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።

በድንበር አካባቢ ስለተከሰተው ጉዳይ በቢቢሲ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ "የተወሰኑ የሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የአርሶ አደሩን ንብረት ለመውሰድ ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት ለመከላከል የተደረገ ክስተት ነው" ሲሉ ግጭቱን ገልፀውታል።

ማክሰኞ ታህሣሥ 6/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የሱዳን ወታደሮች በድንበር አካባቢ ቅኝት አድርገው ሲመለሱ "ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው አድፍጠው በነበሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል" ሲሉ የሱዳን መገናኛ ብዙሃንን በመጥቀስ ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

ማምሻውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትዊተር ገጻቸው ላይ መንግሥት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ ከሚሊሻ ጋር የተፈጠረውን ክስተት በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልፀዋል።

አምባሳደር ዲና ስለክስተቱ ጨምረው እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ "የአርሶ አደር ማሳ ውስጥ ገብተው አንዳንድ ነገሮችን የመውሰድ፣ ወደዚያ የማስፋፋትና ከሕግ አግባብ ውጪ የመሄድ ሁኔታ ስለታየ ይህንን ነገር መመለስ ስለሚያስፈልግ እርምጃ ተወስዷል" ብለዋል።

ግጭቱን ተከትሎ የሱዳን መገናኛ ብዙሃን በጥቃቱ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጨምሮ አራት የሱዳን ወታደሮች መሞታቸውን ዘግበዋል።

የሱዳን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጦሩ ጎን መሆኑን እና ድጋፍ እንደሚያደርግ የዘገቡት መገናኛ ብዙሃኑ፤ የሱዳን ታጣቂ ኃይሎች የአገሪቱን ዳር ድንበር የመጠበቅ እና ማንኛውንም ጥቃት የመከላከል አቅም እንዳለው እምነታቸውን ገልጸዋል ብለዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት በጉዳዩ ላይ በመንግሥት ደረጃ ግንኙነት ማድረጋቸውን ገልፀው፤ ግጭቱን "ይህ የሱዳን መንግሥት ፍላጎት አይደለም" ብለዋል።

እንደ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ጥቃቱን በፈፀሙት ታጣቂዎች ላይ የሱዳን ሠራዊት እርምጃ እንደሚወስድ የተገለጸ ሲሆን፤ የሱዳን ብሔራዊ ዜና ወኪል የሆነው ሱና፤ መከላከያ ኃይሉ "የሱዳንን ድንበር ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ወታደር እንደሚመደብ" መግለፁን ዘግቧል።

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ የተሳካ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለፁት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይህ ችግር "የሱዳን መንግሥት የታችኛው እርከን ችግር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት በአጭር ጊዜ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ አመራሮች ለመነጋገር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ እሁድ እለት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበራቸው አጭር ቆይታ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የድንበር ጉዳይ ነው።

ሱዳን ትሪቡን ረቡዕ ዕለት፤ በሱዳን መከላከያ እና በኢትዮጵያ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደነበር ዘግቦ ግጭቱ የተካሄደው በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ስደተኞችን በሚቀበል ጣብያ አቅራብያ ነበር ብሏል።

ግጭቱ በምሥራቅ ሱዳን አል ቀዳሪፍ ግዛት ቁራይሻ መንደር፣ ዋድ አሩድ ከተማ አቅራብያ መከሰቱን አክሎ ዘግቧል።

አምባሳደር ዲና ግጭቱ የተፈጠረው የመንግሥት ትኩረት ሌላ ቦታ ላይ መሆኑን ከግምት በማስገባት ነው ካሉ በኋላ፤ ከዚህ ቀደምም ድንበሩ አካባቢ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያም ወደ ሱዳን እንቅስቃሴ እንደነበር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር አካባቢዎቻቸው ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ መፍትሄ የሚሰጥ የጋራ የድንበር ኮሚሽን ያላቸው ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባና በካርቱም እተገናኙ ሲመካከሩ መቆየታቸው ይታወቃል።