ትግራይ ፡ ወደ ሱዳን የተሰደደችው ጋዜጠኛ አጭር ማስታወሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ወደ ሱዳን የተሰደደችው የድምጸ ወያነ ጋዜጠኛ ታሪኳን ለቢቢሲ ትግርኛ እንዲህ አጋርታለች።
ስሜ ስምረት* ይባላል። ጋዜጠኛ ነኝ። ተወልጄ ያደኩት በምዕራብ ትግራይ፣ በሑመራ ከተማ ነው።
እስካለፈው ወር ድረስ የድምጽ ወያነ ራዲዮ ጋዜጠኛ ነበርኩ።
ያደኩት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው። ባደኩበት ከተማ ሁሉም ዓይነት ሰው ይኖራል። ትግራዋይ፣ ኦሮሞና አማራ ብቻም ሳይሆን የሱዳንና የናይጄሪያ ዜጎችም አብረውን ይኖራሉ፤ ለዚያውም በሰላምና በፍቅር።
አንዱ ለሌላኛው አክብሮትና መዋደድ ኖሮት በጋራ ነበር የምንኖረው።
ሑመራ የበረሃ ገነት ናት ማለት ይቻላል። ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት። በተለይ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች።
በዚህም የተነሳ በበጋው ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአማራ ክልልና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሥራ ይመጣሉ። ስለዚህ ሁመራ ሁልጊዜም ሕይወት ያላት ውብ ከተማ ነበረች።
ጥቅምት 08/2013 ዓ.ም የዓመት ፍቃድ ወስጄ ከምሠራበት መቀለ ወደ ትውልድ አገሬ ሑመራ ተጓዝኩ። ከቤተሰቦቼና ከአብሮ አደጎቼ ጋር ቆንጆ ጊዜን አሳልፌ ወደ ሥራ ለመመለስ ነበር አካሄዴ።
እንዳሰብኩትም ቆንጆ ጊዜን በሑመራ በማሳለፍ ላይ ነበርኩ፤ ከቤተሰቤና ከጓደኞቼ ጋር ደስ የሚል ጊዜ ነበረን። ይህ የሆነው ግን ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን በከተማዋ ድንገት የሆነ ፍርሃት እና ውጥረት ማሽተት ጀመርን። እውነትም በማዕከላዊው መንግሥትና በህወሓት መካከል ውጥረት እየነገሰ ነበር።
የሆነ ቀን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ለጋዜጠኞች መግለጫ እየሰጡ ነበር።
መግለጫውን በክልሉ ቴሌቪዥን ተከታተልኩት። "ሁሉም ነገር አብቅቶለታል" ሲሉ ሰማኋቸው። "የትግራይ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግ አለበት፤ ጦርነቱ አይቀሬ ነው…" አሉ።
ዶ/ር ደብረጺዮን ብዙውን ጊዜ በመግለጫዎቻቸው እንደዚያ ይላሉ። "ለጦርነት ተዘጋጁ" የምትለው ቃል ከአፋቸው አትጠፋም። ሆኖም ግን በዚህ ወቅት የሰጡት መግለጫ ከሌላው ጊዜ ተለየብኝ።
ስለዚህ መቀለ የሚገኙ ጓደኞቼ ጋር ደወልኩኝ። "አስፈሪ ነገር እየመጣ ይሆን? ነገ ምን ሊመጣብን ይሆን?" እያልን አወራን።
በሚደንቅ ሁኔታ ያንኑ ቀን ሌሊት፣ ተኩስ ተሰማ።
አስታውሳለሁ ያን ምሽት በዶ/ር ደብረጺዮን መግለጫ ተደናግጬ ነበር ወደ መኝታ የሄድኩት። ለዚህም ይመስላል ሌሊት 8 ሰዓት ላይ ባንኜ ተነሳሁ። ስልኬን ስበረብር በጣም ብዙ የጽሑፍ መልዕክቶችን አገኘሁ። መቀለ ከሚገኙ ጓደኞቼ የተላኩ ነበሩ።
ምንድነው ይሄ ሁሉ መልዕክት ብዬ ለአንዳንዶቹ ለመመለስ ስሞክር ኔትወርክ መቋረጡን ተረዳሁ። ታላቅ ወንድሜን እየሆነ ያለውን ነገር እንዲያስረዳኝ ጠየቅኩት።
"አታስቢ፤ የጦር ልምምድ እየተደረገ ይሆናል፤ አሁን አርፈሽ ተኚ" አለኝ።
ነገር ግን በቀጣዩ ቀን የተሰማው ነገር ሌላ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ አዘዙ፤ ይህም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነበር።
ጦርነቱ ከተጀመረ ከሳምንት በኋላ አንድ የታመመ ዘመዴን ለመጠየቅ ካህሳይ አበራ ሆስፒታል ሄድኩ። እዚያው እያለሁ ድንገት ከባድ ተኩስ መሰማት ተጀመረ። ተኩሱ ከጎረቤት ኤርትራ ድንበር በኩል የሚሰማ ነበር።
ሁሉም ሰው በድንጋጤ ተዋጠ። ነዋሪዎች ቶሎ ብለው መሸሽ ጀመሩ። በየገጠሩ ለመደበቅ ሩጫ ተጀመረ። የእኛ ቤት ከከተማው ራቅ ብሎ የሚገኝና ወደ ኤርትራ ድንበር የተጠጋ ነው። ስለዚህ ወደ እናቴ ቤት መሮጥ ጀመርኩ።
ሰዎች ግን እየጮኹ ሊመልሱኝ ሞከሩ። እየሮጥሽ ያለሽው ተኩስ ወደሚሰማበት አቅጣጫ ነው ሲሉ አስጠነቀቁኝ። ሩጫዬን ግን አልገታሁም፡፡ በዚያ ሰዓት ቶሎ ብዬ ከእናቴ ጋር መሆንን ነበር የፈለኩት።
ስደርስ እናቴ እንጀራ አቀረበቸልን። ከቤተሰቡ ጋር አብረን በላን። ከዚያም ወላጆቼ "አሁን መሄድ አለብሽ" አሉኝ።
ከዚያ ቶሎ ብለን በቅርብ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ገብተን ተጠለልን። በዚህ ሁሉ ጊዜ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
ምንም አንኳን አልፎ አልፎ መሳሪያዎቹ የከተማዋን እምብርት ቢመቱም ዋንኛ ዒላማቸው ግን በቅርብ የሚገኘው የትግራይ ልዩ ኃይል የነበረበትን ካምፕ ነበር።
ያን ቀን እስከ ማታ 4፡00 ሰዓት ድረስ ከቤተክርስቲያን ሳንወጣ ስንጸልይ ቆየን።
በሌላ አቅጣጫ ታላቅ ወንድሜ ከብቶቹንና እርሻውን እየጠበቀ ነበር። ማታ ላይ እኛንና ልጆቹን ሊያይ የተጠለልንበት ቤተ ክርስቲያን ድረስ መጣ።
ልክ እንደመጣ ግን አዲስ ሐሳብ አመጣ። ተነሺ ወደ ሱዳን እንሂድ አለኝ።
ለቤተሰብ እንኳ ሰላም ያገናኘን ሳልላቸው በሞተር አፈናጦ ወደ ድንበር ከተማዋ ዲማ ወሰደን። ምሽቱንም እዚያው ዲማ አሳለፍኩ።
ሑመራ፣ ኤርትራና ሱዳን እርስበርስ ሩቅ አይደሉም።
ስለዚህ የጦር መሣሪያ ድምጽ አልፎ አልፎ ይሰማን ነበር። በዚህ ጊዜ ስለ ቤተሰቦቼ መጨነቅ ጀመርኩ። ቤተሰቦቼ የሚኖሩበት ቤት ለኤርትራ ድንበር በጣም ቅርብ ነው።
ያ ብቻም ሳይሆን የትግራይ ልዩ ኃይል አንዳንዶቹ ካምፖች ከእኛ ቤት ጀርባ ይገኙ ነበር። ስለዚህ የቤተሰቦቼ ሁኔታ አስጨነቀኝ።
ነገር ግን ወደ ሱዳን፣ ሐምዳይት ከተማ ከመሸሽ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለኝ ተረዳሁ።
በመጀመርያው ቀን ሐምዳይት እንደገባሁ ያየሁት ነገር ቢኖር በጣም ብዙ ስደተኛ ወደዚህ መምጣቱንና የአስፈላጊ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን ነበር።
ሐምዳይት ከሑመራ ብዙም ሩቅ የሚባል አልነበረም። የሑመራና የሐምዳይት ነዋሪ ድንበር የለየው ዘመድ ያህል ነው።
እኔ ዛሬም ድረስ በካምፑ ውስጥ ነው የምገኘው። ጋዜጠኞችና ሌሎች ወኪሎች ሲመጡ እነሱን በማገዝ እሠራለሁ። እዚህ የሚገኙት ብዙዎቹ ስደተኞች በጦርነት ምክንያት ሰቆቃ ውስጥ ናቸው።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ገና የ5ዓመት ልጅ ነበርኩ። ነገር ግን ብዙዎቹ የጦርነት ስቃዮች ትዝ ይሉኛል።
ወላጆቼ ደግሞ ዕድሜያቸውን በሙሉ ጦርነት ውስጥ ነው ያሳለፉት። ነገር ግን ጦርነት መጣ ብለው ከጦርነት ቀጠና ወጥተው አልጠፉም። ሁልጊዜም የሚሉት እዚሁ ቤታችን ብንሞት እንመርጣለን ነው።
ዛሬ ሑመራ በጦርነቱ ምክንያት ሌላ ከተማ መስላለች። ብዙ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ቤቶች ፈራርሰዋል። ንብረት ተዘርፏል።
ስልክ መሥራት እንደጀመረ ቤተሰቦቼን ደወልኩላቸው። ደህና እንደሆኑ ነገሩኝ። ሁላችንም ስለ ጦርነት መጥፎ ትዝታዎች እንዳሉን አውቃለሁ። በትግራይ ጦርነት የእያንዳንዱን በር አንኳኩቷል። ጦርነት አስቀያሚ ነገር ነው።
ራሴን በሐምዳይት መጠለያ ካምፕ ውስጥ አገኘዋለው ብዬ አልሜም አስቤም አላውቅም ነበር። ዘመዶቼ፣ ጓደኞቼ እና ሕዝቤ ሲሞቱ እመለከታለሁ ብዬ እስቤ አላውቅም። ሆኖም ይህን ለማየት በቃሁ። ይህን በዓይኔ የተመለከትኩትን ሰቆቃ እዘነጋዋሁ ብዬ አላስብም።
በፊት በፊት በሶሪያ ጦርነት ምክንያት ስለተፈናቀሉ ሰዎች ታሪክ እሰማ ነበር። ይህ በአገሬ ወይም በሌላ በማንኛውም አገር እንዲሆን አልመኝም። በጣም አዝኛለሁ።
በዚህ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ብዙዎቹ ሰላም ሆኖ ወደ ትውልድ ቀያቸው ለመመለስ ተስፋ ያደረጉ ናቸው።
ከዳንሻ የመጡ አዳዲስ ጓደኞችን እዚህ ካምፕ ውስጥ ተመልክቻለሁ። እነሱ በጦርነቱ ጊዜ በጣም የከፉ የሚሰቀጥጡ ነገሮችን ተመልክተዋል።
ጋዜጠኛ እንደመሆኔ መቅረጸ ድምጽ ነበረኝ፤ ማስታወሻ ደብተር ተለይቶኝ አያውቅም ነበር። በሕይወቴ የሚያጋጥሙኝን ነገሮች መሰነድ እወድ ነበር። በዜና ክፍል ነበር የምሠራው። ፎቶ ማንሳት ያስደስተኝ ነበር። ለዚህም ስል ሁልጊዜም ስልኬን ይዤ ነበር የምንቀሳቀሰው።
ነገር ግን ያኔ ተኩስ ሲጀመር ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመደበቅ የሮጥን ቀን ስልኬን ቤት ጥዬው ነበር የወጣሁት። ያው እመለሳለሁ በሚል ተስፋ…።
ከ10 ቀናት በኋላ ነበር ከወንድሜ ስልክ ያገኘሁት። በመጀመርያዎቹ ቀናት የነበሩትን ሁኔታዎች እንደ ጋዜጠኛ ሰንጄ አለመያዜ ይቆጨኛል። ነገር ግን አእምሮዬ ላይ ተቀርጾ ተቀምጧል።
ያኔ ዶ/ር ደብረጺዮን "በሁሉም ረገድ ለሚመጣው ነገር ተዘጋጁ" ሲል ምን ማለቱ እንደነበረ አልገባኝም ነበር። ከባንክ ራሱ ግንዘብ ማውጣት አላሰብኩም ነበር።
መቀለ እያለሁ ሁልጊዜ ጠዋት 11፡00 ሰዓት ነበር የምነቃው። ከዚያ ለአንድ ሰዓት ያህል እንቅስቃሴ አደርግ ነበር። በሳምንት ለ6 ቀናት ሥራ እገባ ነበር።
እሑድ፣ እሑድ ግን ሁልጊዜም ወደ ተለያዩ የትግራይ ተራሮች እሄድ ነበር። ከጦርነቱ በፊት ሕይወቴ ደስ የሚል ነበር።
አሁን እዚህ እንቅስቃሴ ማድረግም አልችልም። አሸዋማ ነው። አየሩም አይመችም። ቀኑን ሙሉ በካምፑ ውስጥ ቁጭ ብዬ አሳልፋለሁ። ቁጭ ስል እጨነቃለሁ፤ ቀኑን ሙሉ ጭንቀቴን እያዳመጥኩ ማስታመም ሆኗል ሥራዬ።
ትግራይን ለቅቄ እሄዳለው ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም። ለዚህም ነው ፓስፖርት እንኳ ኖሮኝ የማያውቀው።
ወደ አገሬ ተመልሼ ሕዝቤን ማገልግል ነው ምኞቼ። ወደ አገሬ ተመልሼ ጋዜጠኛነቱን መቀጠል ነው ህልሜ።
ከግጭቱ በፊት በርካታ ሕልም ነበረኝ። ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመሥራት እያሰብኩ ነበር። ቤት የመሥራት ሐሳቡም ነበረኝ። ሌሎችም አያሌ ህልሞች። ምን ዋጋ አለው ታዲያ…!
አሁንም ቢሆን ግን ወጣት ነኝ። ወደፊት ብዙ ተስፋዎች ይጠብቁኛል። ነገ የተስፋ ብርሃን ትፈነጥቅ ይሆናል። ሕልሜንም አሳካለሁ።
ማመን የምፈልገው አሁን የደረሰብኝ ነገር ለነገ ይበልጥ እንድዘጋጅ የሚያደርገኝ እንጂ የሚሰብረኝ እንዳልሆ ነው።
* ስሟ ለደኅንነቷ ሲባል ተቀይሯል








