ኪነ ጥበብ፡ አንጋፋው የጥበብ ሰው ተስፋዬ ገሰሰ በሚያውቋቸው አንደበት

የፎቶው ባለመብት, Tesfaye Gessesse facebook
መተከዣ ፣ ዕቃው፣ የሺ፣ አባትና ልጆች፣ ላቀችና ደስታ፣ ተሐድሶ የተሰኙ ተውኔቶችን ደርሰዋል።
የሼክስፒር ድርሰት የሆነውን ሐምሌትና ትያትርን ጨምሮ በርካታ ተውኔቶች ላይ በመተወን እና በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅተዋል።
የዑመር ኻያምን ልቦለዳዊ የሕይወት ታሪክና ሩብ አያቴ የትርጉም ሥራ ለአንባቢያን አድርሰዋል።
'ሽልንጌን' ጨምሮ በርካታ የአጭር ልቦለድ ሥራዎችን ለአንባቢያን አበርክተዋል።
በተለያዩ ፊልሞችና ድራማዎች ላይ ተውነዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር እና ጥበባት ኮሌጅ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል።
የብሔራዊ ትያትር ቤት ዳሬክተር በመሆንም ሰርተዋል። ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ ትልቅ አሻራ ካሳረፉ አንጋፋ የጥበብ ሰዎች አንዱ ናቸው። ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ።
እኝህ አንጋፋ የጥበብ ሰው በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተሰማው ትናንት ነበር። በርካቶች ተስፋዬ ገሰሰን "ራሳቸውን ሆነው ለጥበቡ ዘርፍ የበኩላቸውን አበርክተው ያለፉ ሰው" ሲሉ ይገልጿቸዋል።
"በግለሰቦችም ሆነ በአገርም ላይ ብዙ ውጤቶች ያፈራ ሰው ነው"
አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ከተስፋዬ ገሰሰ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ናቸው። ለአስርት ዓመታትም በጥበቡ ዘርፍ አብረው ደፋ ቀና ብለዋል።
ሁለቱ ተስፋዬ ትውውቃቸው የሚጀምረው በ1965 ዓ.ም ነበር። እርሳቸው አገር ፍቅር ትያትር ክበብ ሲመሰርቱ፤ ተስፋዬ ገሰሰ ደግሞ የትያትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ነበሩ።
"ተስፋዬ ገሰሰ ልዩና ጨዋ ሰው ነበር" የሚሉት ተስፋዬ አበበ፤ "በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበብ መምህር ሆኖ ወደፊት ተተኪ የሆኑ ተዋንያንን ፈጥሯል" ይላሉ።
በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ የትያትር አዳራሽ 'ተስፋዬ ገሰሰ የኪነ ጥበባት ማዕከል' ተብሎ ተሰይሞላቸዋል።
"ተስፋዬ ገሰሰ በግለሰቦችም ሆነ በአገር ላይ ብዙ ውጤቶች ያፈራ ሰው ነው" ይላሉ። ለዚህም 'ጋሻ ዳምጤ' የተሰኘውን ሙዚቃዊ ተውኔት ለአብነት ያነሳሉ።
'ጋሻ ዳምጤ' በሳንሱር የተከለከለና የወሎ ረሃብን የሚያሳይ ሙዚቃዊ ድራማ ነው። በዚህ ተውኔት ላይ የተስፋዬ የትወና ብቃት የሚገርም እንደነበር ያስታውሳሉ። "ተዋንያኑም በደስታ ተነስተው ይቀበሏቸው ነበር" ይላሉ- በሙያቸውም ሆነ በጥበበኞች ዘንድ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበሩ ሲገልፁ።
'ጋሻ ዳምጤ' የተሰኘው ሙዚቃዊ ተውኔት ሙዚቃው በተስፋዬ አበበ የተሰራ ሲሆን ዳይሬክት የተደረገው በተስፋዬ ገሰሰ ነበር።
የጥበቡ ሰው ተስፋዬ ገሰሰ ለኪነ ጥበብ ዘርፉ እንደየ ዘመኑ ዋጋ ከፍለዋል።
በደርግ ዘመነ መንግሥት 'ዕቃው' የሚል ተውኔት ጽፈው ለእስራት ተዳርገው እንደነበር አርቲስት ተስፋዬ ያስታውሳሉ።
በዚያው ዘመን 'ደማችን ትግላችን' የሚል ሙዚቃዊ ድራማ ላይ በትወና እና በዝግጅት ሰርተዋል። በዚህም በዝምታ አልታለፉም ነበር። ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር።
"አገራዊና ሕዝባዊ የሆኑ ሥራዎች ላይ በድፍረት እየገባ፤ ጥበብን በድፍረት እየተወጣ የነበረ ሰው ነበር" ይላሉ አርቲስት ተስፋዬ።
እርሳቸው እንደሚሉት ተስፋዬ ገሰሰ በግድ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው የሰሯቸው ሥራዎች አልነበሩም። አንዳንድ ነገሮች ከበላይ አካል ሲመጡም 'ይህን አልሰራም!' የማለት አቅም የነበራቸው ሰው እንደነበሩ ይመሰክራሉ።
በወቅቱ ከነበረው ጫና ጋር ተያይዞ ገጣሚና ፀሐፈ ተውኔት አያልነህም አንድ አጋጣሚን እንዲህ ሲሉ ያስታውሳሉ።
"በደርግ ዘመነ መንግሥት የሱዳን መሪ ኢትዮጵያ መጥተው ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሙዚቃ ለማየት ትያትር ቤት ገብተው ሳለ፣ ማን እንዳደረገው ሳይታወቅ መብራት ጠፋ። የዚያን ጊዜ 'ሆነ ተብሎ ነው የተደረገው' በሚል ወቀሳ ቀርቦባቸው ነበር። በዚህ ምክንያትም በወቅቱ የነበሩት የባህል ሚኒስትር ከሥልጣናቸው ተነስተዋል"

የፎቶው ባለመብት, Tesfaye Gessesse facebook
"በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለዲግሪ ተዋናይ ነበር"
በንጉሱ ዘመን አፄ ኃይለሥላሴ ተስፋዬ ገሰሰን አንድ ተውኔት ሲሰራ አይተውት በሥራው በመደሰታቸው የትምህርት ዕድል ሰጥተውት ነበር። ከዚያም ወደ አሜሪካ አገር አቅንቶ ትያትር አጥንቶ ተመልሷል።
"በኢትዮጵያ የኪነ ጥበባት ታሪክም የመጀመሪያው ባለዲግሪ ተዋናይ ተስፋዬ ገሰሰ ነው" ይላሉ አርቲስት ተስፋዬ።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፊልሞች ላይ በርካታ ሥራዎችን ሲሰሩ እንደነበር በመጥቀስም "እርጅና እንኳን አልበገረውም። በጥበብ የተገዛ፣ በጥበብ የኖረ እና በጥበቡ መስዋዕትነት የከፈለ ሰው ነው" ይላሉ።
አርቲስት ተስፋዬ፤ የተስፋዬ ገሰሰ የገፀ ባሕርይ አለዋወጥ፣ የሥነ ቃላት አጠቃቀማቸው ልዩ ነበር ይላሉ።
"ዑመር ኻያምን ማንም እንደሱ አድርጎ አይተውነውም፤ ዑመር ኻያም ማን ነው? የሚለውን ብዙዎቻችን የምናውቀው በተስፋዬ ገሰሰ ነው" ሲሉም አድናቆታቸውን ይገልፃሉ።
ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት ብዙዎች ናቸው።
ገጣሚና ፀሐፈ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር የተዋወቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ነበር።
እርሳቸውም "የጥበብን ፍቅር 'ሀሁ' ብሎ ያስተማረኝ ተስፋዬ ነው" ይላሉ።
የጥበብን ከፍታ ያዩትም ያኔ ተስፋዬ ገሰሰ በብሔራዊ ትያትር 'ሐምሌትን' ሲጫዎት እንደነበር ይናገራሉ። ይህም በሕይወት ዘመናቸው ትልቅ ተፅእኖ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
ደራሲ እንዳለጌታ ከበደም የሕልፈታቸውን ዜና ከተሰማ በኋላ በፌስቡክ ገጹ ተስፋዬን " በባህርይውም በሥራውም ተለይቶ የወጣ ሰው ነበር፤ በሥራዎቹ መድረክ የቤተመቅደስ ያህል ክቡር እንደሆነ ኖሮ አሳይቶናል" ሲል ገልጿቸዋል።
"አርቲስቶች ቋሚ ደመወዝ እንዲኖራቸው ያስፈቀድነው ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር ሆነን ነው"
ፀሐፈ ተውኔት አያልነህ ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር በርካታ ሥራዎችን የሰሩት ተስፋዬ የብሔራዊ ቲያትር ቤት ዳሬክተር በነበሩነት ጊዜ ነበር። ከእነዚህ መካከል የአርቲስቶች የደመወዝ ጉዳይ ነበር።
አቶ አያልነህ እንዳጫወቱን በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን አርቲስቶች ቋሚ ደመወዝ አልበራቸውም። በኮንትራት ክፍያ ነበር የሚሰሩት።
"ይህን አሰራር ለመለወጥ ጥናት አጥንተን ለመንግሥት በማቅረብ፤ አርቲስቶቹ ቋሚ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያስፈቀድነው ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር ነበር" ይላሉ።
የጥበብ ሥራዎችንም አብረው እንደሰሩ ይናገራሉ።
ከእነዚህ መካከል በናይጀሪያ ሌጎስ የጥቁር አፍሪካ ፌስቲቫል ላይ የቀረበው 'ትግላችን' የተሰኘው ሙዚቃዊ ድራማ አንዱ ነበር። ይህ ድራማ በናይጄሪያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ተዘዋውሮ እንደታየ አቶ አያልነህ ይናገራሉ።
ድራማው ኩባም ድረስ ተጋብዞ በወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለዕይታ በቅቷል። በዚያም ድራማ ላይ በአያልነህ ተጽፎ ተስፋዬ ገሰሰና ሃይማኖት አለሙ የተሳተፉበት የ20 ደቂቃ 'ትንሳኤ ሰንደቅ አላማ' የሚል ውዝዋዜ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በደርግ ዘመንም በብሔራዊ ትያትር የሚወጡት ሥራዎች የሚደነቁ እንደነበሩ አቶ አያልነህ አውስተዋል።
" 'ሻጥር በየፈርጁ'፣ 'መንታ እናት' ፣ የጋዜጠኛ ነጋሽ ገብረ ማሪያም ሥራዎች 'የአዛውንቶች ክበብ'፣ 'ሀሁ በስድስት ወር'፣ 'የከርሞ ሰው' ፣ 'ጠያቂ እና ሌሎችም በሰው ሕሊናው ውስጥ የማይጠፉ ወጣቱን ትውልድ ሊቀርፁ የሚችሉ ሥራዎች ይወጡ የነበሩት ተስፋዬ ገሰሰ የትያትር ቤቱ ዳሬክተር ከሆኑ በኋላ ነው" ይላሉ።
አቶ አያልነህ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በትያትር ቤት የሚቀርቡት ትያትሮች ትርጉም ነበሩ በማለትም፤ ይህ የተቀየረው በተስፋዬ ጥረት እንደነበር ይመሰክራሉ።
"ጋሽ ተስፋዬ ራሱን ሆኖ የኖረ ሰው ነው"
በርካቶች የጥበቡ ሰው ተስፋዬ ገሰሰን የግል ባህርይ፤ "ግልፅ ፣ ተጨዋች፣ ያመነበትን የሚናገር፣ ለማንም የማያሸረግድ፣ ራሱን ሆኖ የኖረ ነው" ሲሉ ይገልጿቸዋል።
አርቲስት ተስፋዬ አበበ "በጣም ልዩ ሰው ነው። በመድረኩም በውጭም አርቲስት ነው። ለፍንደቃ የተፈጠረ ሰው ነው። ምንም ነገር ቢሆን አይከፋውም። ሁሉንም ሰው አስደስቶ፣ አጫውቶ ማናገር ይፈልጋል። መድረክ ላይም ዳይሬክት የሚያደርገው ተዋንያንን ከገፀ ባህሪያቸው እንዳይወጡ እያሳሳቀ ነበር" በማለት ተናግረዋል።
ፀሐፈ ተውኔት አያልነህ በበኩላቸው " በትወናውና በአስተዳደሩ እውነተኛ የአርቲስት መንፈስ የያዘ ነው። ቂም አያውቅም፤'ተጣልተናል' ሲባል እንኳን 'መቼ?' ብሎ የሚጠይቅ ሰው ነው። ቅን ልቦና ያለው ነው። ሕዝባዊ አመለካከት ያለው፣ የሕዝብ ወገን የሆነ ሰው ነበር" ብለዋል።
ደራሲ እንዳለጌታም በፌስቡክ ገፁ እኝህን አንጋፋ የጥበብ ሰው በዘከረበት ፅሁፉ "ራሱን ሆኖ የኖረ ሰው" ሲል ገልጿቸዋል።
አንዳንዴ ደግሞ እንግዳ በሆነ ተግባር ሲሳተፍ እንግዳ ነገር ሲያደርግ እናየዋለን ይላል።
ለዚህም ከአብነቶቹ አንዱን ያነሳል።
በአንድ ወቅት ከተስፋዬ ጋር ለጨዋታ ተገናኝተው ሦስት ድራፍት እንዳዘዙና እና አንዱ ለማን እንደሆነ በጠየቃቸው ጊዜ በሞት ለተለየው ወዳጁ ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚያብሔር መሆኑን እንደገለፀለት በጽሁፉ አውስቷል።
የአንጋፋው ደራሲና ተዋናይ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

















