ትኩረት የተነፈገው የባህር ዳር መለያ ባህላዊ ጥበብ

የፎቶው ባለመብት, BBC
የጣና ሃይቅ ዳርቻዋ የባህር ዳር ከተማ በስፋት ከምትታወቅባቸው ነገሮች መካከል ከቆዳ የሚሰሩት ባህላዊ ቁሶች ይገኙበታል። ከተለያዩ የእንስሳት ቆዳ የሚሠሩት እንደ መቀመጫ፣ አገልግል እና ከበሮ ያሉ ባህላዊ መገልገያዎች የበርካቶችን ቀልብ የሚስቡ የጥብበ ሥራዎች ናቸው።
እኒህን መሰል ባህላዊ ቁሶች ከእንስሳት ቆዳ በመስራት ቤተሰብ ከሚያስተዳድሩ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ገብረመድህን አሞኘ አንዱ ነው። ገብረመድህን ለበርካታ ዓመታት የቆዳ ውጤቶቹን ሰርቶ እየሸጠ የቤተሰቡን የዕለት ፍላጎት ከመሸፈን ውጪ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዳላስገኘለት ይናገራል።
ይሁን እንጂ ገብረመድህን እንደሚለው ከሆነ ለእነዚህ ባህላዊ ጥበባት ትኩረት ቢሰጥ ከእንድ ቤተሰብ አልፈው ለሃገርም ከፍተኛ ገቢ ያስገኛሉ ይላል።

የቆዳ ውጤት የሆኑ ባህላዊ የጥበብ ሥራዎች በውጪ ጎብኚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዳላቸው የሚናገራው ገብረመድህን እንደማሳያም በባህላዊ መንገድ በቆዳ ሽፋን የሚሰራው መቀመጫ ምን ያክል በውጪ ሃገር ዜጎች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነ ሲያስረዳ ''ቱሪስቶች በጣም ነው የሚወዱት። ገዝተው ይዘው መሄድ ይፈልጋሉ፤ ግን ከባድ ስለሆነ መውሰድ አይችሉም። አማራጭ ስለሌላቸው ፎቶ ተነስተውበት ነው የሚሄዱት'' ይላል።
ለሥራው ግብዓት የሚሆነውን ቆዳ ከአርሶ አደሩ እንደሚገዛ ከዚያም ቆዳውን ቆራርጦ የተለያዩ ባህላዊ መገልገያዎችን እንደሚሰራ፤ ሥራውም እጅግ አድካሚ እና ጊዜ የሚወስድ መሆኑንም ይናገራል።
ገብረመድህን እንደሚለው ከሆነ እኚህ መሰል እቃዎች በውጪ ሃገር ጎብኚዎች ዘንድ ተወዳጅ ስለሆኑ ወደ ውጪ ሃገር ተልከው ቢሸጡ ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሪ ለሃገር ሊያስገኙ እንደሚችሉ ዕምነት አለው።
ይህ እንዲሆን ግን መንግሥት ለጥበብ ሥራው ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት የፈጠራ ችሎታን ማዳበር እና በእጅ ብቻ ሳይሆን በማሽኖች በመታገዝ ሥራው ቢከናወን ሁሉም ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ይናገራል።

ሌው የቆዳ ውጤቶችን በመስራት እና በመሸጥ ለ12 ዓመታት በሥራው ላይ የቆየው ሃብታሙ ሙጬም እንደ ገብረመድህን ሁሉ ለጥበብ ሥራው በቂ ትኩረት ስላልተሰጠ ማግኘት የሚገባንን ጥቅም እያገኘን አይደለም ይላል።
ባህር ዳርን በእነዚህ የጥበብ ሥራዎች እንደምትታወቅ የሚያስረዳው ሃብታሙ በአዳዲስ ፈጠራዎች ደንበኞቻቸውን ለመማረክ የተለያየ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ፤ ይሁን እንጂ ይህ ነው የሚባል ለውጥ በስራው ላይ እንዳላየ ይናገራል።
አቶ አወቀ መንግሥት የባህላዊ የቆዳ ውጤቶች ዕቃዎች አምራች ማህበር ሊቀመንበር ነው። የጥበብ ሥራ ''የክልላችን፤ በተለይም ደግሞ የከተማችን መለያ ሆኖ ሳለ በክልሉ መንግሥት በቂ ትኩረት አልተሰጠውም። ጎንደርም፣ ደሴም ቢሰራ እንኳ የባህር ዳር እቃ ተብሎ ነው የሚታወቀው ይሁን እንጂ ትኩረት አልተሰጠውም'' በማለት ይናገራል።
''ጎብኚዎች ከጢስ አባይ እና ከጣና ገዳማት ባላነሰ ሁኔታ የእኛን ሥራ ጎብኝተው ነው የሚሄዱት። ትኩረት ብቻ ሳይሆን የተነፈገን በቋሚነት ምርታችንን ለደንበኞች የምናቅርብበት ቦታ እንኳ አልተሰጠንም። ምርቶቻችንን እየሸጥን ያለነው አመቺ ባልሆነ ስፍራ ከብረት በተሰሩ ሱቆች ውስጥ ነው። ይህም ለደንበኞችችንም ሆነ ለምርቶቻችን አስቸጋሪ ሆኗል'' ይላል።

ወ/ሮ ብርቱካን ይታየው በባህር ዳር ከተማ የባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ የባህል እሴቶች እና የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ እንዳሉት የተባሉትን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተው "የንግድ ቦታው ለቱሪስቶች አመቺ የሆነ ቦታ እንዲሰጣቸው ለከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤት ጥያቄ እናቀርባለን" ብለዋል።
ጨምረውም ምርታቸው እንዲሻሻልና ገቢያቸውን ለማስፋት የሚያስችል ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያግዝ ስልጠና በተወሰነ ደረጃ የተሰጣቸው ቢሆንም ተጠናከሮ እንዲቀጥልና በዘርፉ እንቅስቃሴ ላይ እድገትን የሚያመጣ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ እነደሆነ ወ/ብርቱካን ተናግረዋል።
በዚህ ሁኔታ የሚመረቱት እነዚህ ባህላዊ መገልገያዎች የባህር ዳር መለያ በመሆን ወደ ከተማዋ የገባውን የሃገር ውስጥም ሆነ የውጪ እንግዳን ቀልብ በመሳብ ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እያበረከተ ቢሆንም በርካታ ችግሮች ስላለበት የሚፈለገውን ያህል እድገት አላሳየም።
ነገር ግን ዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘት ከቻለ ለበርካቶች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር ከተማዋ መታወቂያ በመሆን በገቢ በኩልም ቀላል ያማይባል ገንዘብን ሊያስገኝ እንደሚችል በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች በእርግጠኝነት ይናገራሉ።












