እሽኮኮ ተብሎ ማስታወቂያ ከመስራት ወደ ቴሌቭዥን፡ የውብሸት ወርቃለማሁ የማስታወቂያ ሕይወት

የፎቶው ባለመብት, FANA BROADCASTING CORPORATE
ውብሸት ወርቃለማሁ በማስታወቂያ ሥራ፣ በቴአትር ጽሑፍ፣ በትወና እንዲሁም በሌሎችም የኪነ ጥበብ ዘርፎች ገናና ስም አትርፈዋል። በርካቶች ጋሽ ውብሸት ሲሉ በአክብሮትና በፍቅር ይጠሯቸዋል።
'አቢሲኒያ የትጉሀን መናኸሪያ'. . . ጋሽ ውብሸት በአስገምጋሚ ድምፃቸው ከሚታወሱባቸው ማስታወቂያዎች መካከል ይጠቀሳል።
የማስታወቂያ ዘርፍን በማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን በማዘመን እንዲሁም የበርካቶች እንጀራ በማድረግም ፈር ቀዳጅ ናቸው።
የሙያ አጋራቸው እንዲሁም ወዳጃቸው አያልነህ ሙላት፤ "ውብሸት ወደ ማስታወቂያ የገባው ገና ቄስ ትምህርት ቤት ሳይገባ ነበር" ይላሉ።
አቶ ውብሸት ልጅ ሳሉ በትውልድ ቀያቸው 'በባህላዊ መንገድ' ማስታወቂያ ይነግሩ ነበር። አንድ የታወቀ ትልቅ ሰውን 'እሽኮኮ በለኝ' አሉና ሰውየው ትከሻ ላይ ሆነው ይሄን ያህል ጤፍ መጥቷል፣ ይሄን ያህል በቆሎ ተገኝቷል፣ አትክልትም መጥቶላችኋልና እዚህ ቦታ ግዙ እያሉ ያስተዋውቁ ነበር።
"ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ መጻፍ ሲጀምር ሙክት፣ በግ፣ የት እንዳለ ቀለም በጥብጦ ፣ እየጻፈ ትልልቅ ዛፍ ላይ እየሰቀለ ማስታወቂያ ይሰራ ነበር' ሲሉ አያልነህ ያወሳሉ።
ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የተቀጠሩት ብሔራዊ ሎተሪ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔራዊ ሎተሪን ማስታወቂያ ሲሠሩ፤ አህያ ላይ ገለባ የሞላው ማዳበሪያ ጭነው፣ ብር ለጥፈውበት ነበር።
ከቸርችል ጎዳና ወደ ታች እየወረዱ 'ሎተሪ ብትገዙ ይህን ያህል ብር ታገኛላችሁ' እያሉ ያስተዋውቁ ነበር።
አያልነህ እንደሚሉት፤ ይህን ማስታወቂያ ያየው ፊሊፕስ አቶ ውብሸትን የቀጠራቸው ወዲያው ነበር። ከዚያ በኋላ እጅግ በርካታ ማስታወቂያዎች ሠርተዋል።
"የማስታወቂያ ሙያ እንዲታወቅ ያደረገ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ ነው" ሲሉም ይገልጿቸዋል።
ጋሽ ውብሸት ከአብነት ትምህርት ቤት ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ መደበኛ ትምህርት ጀመሩ። ከትምህርት ቤት እንደወጡ መዋያቸው አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ነበር።
የትወና እና የጸሐፌ ተውኔትነት ሕይወታቸውን 'ሀ' ብለው የጀመሩት በዚያው ቴአትር ቤት እንደሆነም አያልነህ ያስታውሳሉ።
ያኔ ከቀደምቶቹና ታላላቆቹ እነ ኢዩኤል ዩሐንስ፣ አውላቸው ደጀኔ፣ ጸጋዬ ገብረመድሕን፣ ወጋየሁ ንጋቱ. . . ጋር አብረው ይሠሩ ነበር።
ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፤ ጋሽ ውብሸት የተዋጣላቸው ተዋናይና ጸሐፊ እንደነበሩ ይናገራሉ።
"ሲተውን መምሰል ሳይሆን መሆን የሚችል ሰው ነበር። ንጉሠ ነገሥቱን ሆኖ ሲጫወት ራሳቸው ንጉሠ ነገሥት [ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ] በጣም ተገርመው ነበር። እንደኔ ለመሆን የሞከርከው በጣም ጥሩ ነው ብለውት ነበር። ውብሸት የሚጽፈው እንደዛሬው ይዘት በሌለው ኮሜዲ ሰውን አስቆ ለመለያየት ሳይሆን፤ መሠረታዊነት የኮሜዲን ሥርዓት ጠብቆ ነው።"ይላሉ
ውብሸት እና አያልነህ አጋፔ ቅዱስ ሚካኤል የተባለ የበጎ አድራጎት ማኅበር አባል ናቸው። ላለፉት 20 ዓመታት ለአቅመ ደካማ ቤተክርስቲያኖች ድጋፍ ያደረገው ይህ የጽዋ ማኅበር የሚመራው በአቶ ውብሸት ነበር።
"በየወሩ እንገናኝ ነበር። ማኀበሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ያስቻለው ውብሸት ነው። ለአገሩ ያለው ፍቅር፣ በኢትዮጵያዊነቱ ያለው ኩራት ልነግርሽ አልችልም. . . "
አቶ ውብሸት በወሎ ረሀብ፣ በድሬዳዋ ጎርፍ ወቅትም ገንዘብ በማሰባሰብ እና ከቀይ መስቀል ጋር በመሥራትም ይታወሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media Agency
"ማስታወቂያን 'ሀ' ብሎ ያስተማረኝ ጋሽ ውብሸት ነው" ሙሉዓለም ታደሠ
ሙሉዓለም ታደሠ ብሔራዊ ቴአትር የተቀጠረችው በ1984 ዓ. ም. ነበር። ያኔ ተዋናይት ለመሆን ቴአትር ቤቱን ስትቀላቀል፤ አቶ ውብሸት ግን ለማስታወቂያ ሠሪነት ጭምርም አጯት።
ወቅቱን "የሕይወት አቅጣጫዬ የተቀየበረበት ነው" ስትል ትገልጸዋለች።
ጋሽ ውብሸት ማስታወቂያ ሲሠሩ ታውቃቸው ነበር። በከብት ወይም በሰው ትከሻ ላይ ቆመው 'ስማ፤ የሰማህ ላልሰማ አሰማ'፤ ይህ ሰንጋ ጥሩ ነው' ብለው ማስታወቂያ ይሠሩ እንደነበርም ታስታውሳለች።
በድምፅ የምታውቀውን አንጋፋ ሰው በአካል ስታይ "የበለጠ ገዝፎ ታየኝ" ትላለች።
በወቅቱ እንኳን ስለ ማስታወቂያ ይቅርና ስለ ቴአትርም እምብዛም እውቀት እንዳልነበራት ሙሉዓለም ታስታውሳለች። ውብሸትን "ማስታወቂያን 'ሀ' ብሎ ያስተማረኝ የሙያ አባቴ ነው" የምትለውም ለዚሁ ነው።
በቴአትር ቤቱ ተቀጥራ ገና በአንድም ቴአትር ላይ ሳትተውን ውብሸት የብሔራዊ ሎተሪ ማስታወቂያ እንድትሠራ ጋበዟት።
ሙሉዓለም የምትተውነው ሙሽራ ሆና ነበር። ሁሌም አጠገባቸው ያለን ሰው ፈገግ ማሰኘት የማይሳናቸው ጋሽ ውብሸት ማስታወቂያውን ሲያዘጋጁ ሙሉዓለምን እያሳሳቋት እንደነበር ታወሳለች።
'ዛሬ ባል የሌላት ሙሽራ ደግሼ ልድር ነው' እያሉ ይቀልዱ እንደነበር ታስታውሳለች። ማስታወቂያውን ለመቅረጽ ወደ መናፈሻ ሲሄዱ (ሙሉዓለም ቬሎ እንደለበሰች) ትራፊክ ፖሊስ መኪኖችን አስቁሞ ሲያዩ፤ 'ሙሽራ ክቡር ነው፤ እባክህ አሳልፈን' ብለው ማለፋቸውም አትዘነጋም።
በማስታወቂያው ላይ ሙሽራዋ እንደ ሎተሪ ሆና 'እድል የደረሰው ይውሰደኝ' ትል ነበር። ማስታወቂያው ሦስት ጊዜ እንደተላለፈ ግን ከቤተ ክህነት ከባድ ወቀሳ ስለገጠመው እንዲቋረጥ ተወሰነ።
ሁለተኛው የሎተሪ ማስታወቂያ ሙሉዓለም ሎተሪ እንደደረሳት ሰው ሆና በጠዋት ተነስታ ዘለግ ላለ ደቂቃ ስትስቅ ያሳያል። ያኔ መንገድ ላይ 'ሳቅ ሳቅ ይለኛል' 'ሳቂልኝ' ትባል እንደነበር ታስታውሳለች።
ከዛ በኋላ የአምቦ ማስታወቂያ [ግብዣ ያለ አምቦ ውሀ] እና የፊሊፕስ ማስታወቂያ እንዲሁም ሌሎችም በርካታ ሥራዎች ተከተሉ።
"ድራማዊ የሆኑ ማስታወቂያዎችን በመሥራት ለኔና ለሠራዊት ፍቅሬ መነሻችን ጋሽ ውብሸት ነው" ትላለች ሙሉዓለም።
ውብሸትን ሁሌም ከምታስታውስበት ነገር አንዱ ጀማሪ ማስታወቂያ ሠሪዎች የሚሰጡትን አስተያየት ለማድመጥ ዝግጁ በመሆናቸው ነው።
"እንደ ታላቅነቱ አይደለም። በትህትና ዝቅ ብሎ ይቀርበናል። ምንም የማናውቀው ሰዎች እሱን እንከራከረዋለን። ሲከራከሩት ደግሞ ደስ ይለዋል"
ሙሉዓለም ብሔራዊ ቴአትር የተቀጠረችው ከተስፋዬ ገብረሃና፣ ከሰለሞን ሙላት እና ከቴዎድሮስ ተስፋዬ ጋር ነበር። ያኔ ደመወዛቸው 230 ብር ነበር። ውብሸት 'ማስታወቂያ ጥበብ ነው፤ ከዛ ባሻገር ራሳችሁን፣ ኑሯችሁን ትደግፉበታላችሁ' ብለው ወደ ሙያው እንዳስገቧት ታስታውሳለች።
ከዛ በኋላ ለዓመታት በዘርፉ ገናና ከሆኑ ባለሙያዎች እንዷ ሆና ዘልቃለች። አቶ ውብሸትንም እንዲህ ትገልጻቸዋለች።
"በጣም አገሩን ይወዳል፤ ዓለምን ዞሯል፤ በየሄደበት ደግሞ ኢትዮጵያን ያስተዋውቅ ነበር። ጎርፍም ሌላም ችግር ቢከሰት ቀድሞ ደራሽ ነው። እኛ የሙያ ልጆቹ አንድ ነገር ቢደርስብን የምንደውለው እሱ ጋር ነው። ደከመኝ ሰለቸኝ ከአፉ አይወጣም።"
"ጋሽ ውብሸት [ገና ሳያውቀኝ] አበባ ይዞልኝ ቢሮዬ መጥቷል"ሳምሶን ማሞ
የማስታወቂያ ባለሙያው ሳምሶን ማሞ ከ25 ዓመታት በፊት የማስታወቂያ ድርጅቱን ሲከፍት ያልጠበቀው እንግዳ ቢሮውን አንኳኳ። ውብሸት ወርቃለማሁ እቅፍ አበባ ይዘው 'እንኳን ደስ አለህ' ሊሉት ቢሮው ተገኝተው ነበር።
"ያኔ ጋሽ ውብሸት ሊያውቀኝ አይችልም። እኔ ገና ልጅ ጋዜጠኛ ነበርኩ። ጋሽ ውብሸት እኔጋ ሊመጣ ይችላል ብዬ በህልሜም አላስብም። እንኳን ደስ አላችሁ ብሎ ለኔና ለባለቤቴ አበባ ይዞልን መጣ። በአሁን ሰዓት በጋሽ ውብሸት ደረጃ እንደዚህ የሚያደርግ ሰው አለ ብለሽ ታስቢያለሽ? አንዳንድ ሰው ገበያዬን ነጠቀ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ጋሽ ውብሸት ግን እንደዛ አይነት ሰው አይደለም።"
ሳምሶን 'ፊሊፕስ የጥሩ እቃ ስም. . .' የሚለውን በሙሉቀን መለሰ ዘፈን የታጀበ ማስታወቂያ ከልጅነቱ ጀምሮ አጥንቶታል። በርካታ የውብሸት ሥራዎችንም ያደንቃል።
ሳምሶን እንደሚለው፤ የማስታወቂያ ሙያ እንዲጀመር ብቻ ሳይሆን እንዲጎለብት በማድረግም የአቶ ውብሸት ሚና ቀላል አይደለም። "ባልሰለጠነ ዘመን ቀድሞ የሰለጠነ እና ራሱን የፈጠረ" ሲልም ይገልጻቸዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ300 በላይ የማስታወቂያ ድርጅቶች ለመፈጠራቸው ምከንያቱ ጋሽ ውብሸት እንደሆነ ያስረዳል።
ከሁለት አሰርታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የአንድ ደቂቃ ማስታወቂያ ለማስተላለፍ 100 ብር ይከፈል ነበር (ዛሬ ከ15 እስከ 20 ሺህ ያስከፍላል)። በዘመኑ በቴሌቭዥን ማስታወቂያ የሚሠራለት ምርትና አገልግሎት ማንም የማይፈልገው እንደሆነ ይታመን ነበር።
"ማስታወቂያ ማስነገር እንደ ሀጢያት፣ ምርቱም እንደ ርካሽ ይቆጠር ነበር። ይህንን ብቻውን ነው የታገለው። ዛሬ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን የመሳሰሉት ከ100 ብር ተነስተው በአንድ ደቂቃ እስከ 25 ሺህ ብር እየተከፈለ፣ በዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እስከመሰብሰብ ደርሰዋል" ይላል ሳምሶን።
አቶ ውብሸት የዓለም አቀፍ አስተዋዋቂዎች (ኢንተርናሽናል አድቨርታይዚንግ አሶሴሽን) አባል ሲሆኑ፤ በምዕራቡ አገራት ስለ ማስታወቂያ ሥራ ስልጠናዎችም ወስደዋል።
በ82 ዓመታቸው የገበያ ድርሻቸው ሳይቀንስ፣ በድምፃቸው ማስታወቂያ በመሥራት መግፋታቸው ሳምሶንን ያስገርመዋል። "እኔ በ82 ዓመቴ ይህንን የማደርግ አይመስለኝም" ይላል።
አያልነህ፣ ሙሉዓለምና ሳምሶን ስለ ጋሽ ውብሸት የሚናገሩት ተመሳሳይ ነገር አለ። ይህም አገር ወዳድ፣ ሀይማኖተኛ፣ አስታራቂ፣ በየትኛውም ቦታ (ባለሥልጣኖች የታደሟቸውና ከባድ የሚባል ርዕሰ ጉዳይ የተነሳባቸውን ጨምሮ) ቀልድ ጣል ማድረጋቸው ነው።
ያለፈው ቅዳሜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አንጋፋው ውብሸት ወርቃለማሁ ዛሬ በመስቀል አደባባይ ሽኝት እንደሚደረግላቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ አስተባባሪ አያልነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












