ደራሲ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር "ደፋር ጸሐፊ ነበር"

ደራሲ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር

የፎቶው ባለመብት, FAMILY

የደራሲ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፅሟል።

ሕዳር 24 ቀን 2012 ዓ. ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጸሐፊው፤ ሥርዓተ ቀብራቸው ዛሬ ህዳር 25 ቀን 2012 ዓ. ም. መቀለ በሚገኘው በአዲሽምድህን ማሪያም ቤተክርሲቲያን ይፈጸማል።

መምህር ካሕሳይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ፕሮግራም ወጎችን በማቅረብ ይታወቃሉ።

በሦስት ቅጽ ከተጻፈው "ኀብረ ብዕር" የተሰኘው መጽሐፍ በተጨማሪ "ብፁአን እነማን ናቸው?"፣ "ምንኩስና በኢትዮጵያ"፣ "ባህል እና ክርስትያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ" እና "ምስጢረ ፊደል ወትርጓሜሁ፤ የፊደል ምስጢር ከነትርጉሙ" የተሰኙ መጻሕፍትም ጽፈዋል።

"ኀብረ ብዕር" የወጎች፣ የግጥሞች፣ የሽለላ እና የቦታ ሥያሜዎች ስብስብ ነው።

በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም፣ ወጎች በማቅረብ የሚታወቁት ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እንዲሁም የወግ ጸሐፊ ካሕሳይ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሚታተመው "ዜና ቤተክርስትያን" ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅም ነበሩ።

ደራሲና ጋዜጠኛ ካሕሳይ፤ በመምህርነት እንዲሁም በርዕሰ መምህርነት ሠርተዋል።

በ "ሠርቶ አደር" ጋዜጣ የሐረር ሪፖርተር የነበሩ ሲሆን፤ ከደርግ መውደቅ በኋላ በሐረርጌ ክፍለ አገር በትምህርት መገናኛ ድርጅት በፕሮግራም አዘጋጅነት፣ በአፍሪካ ቀንድ መጽሔት የምሥራቅ ኢትዮጵያ ዘጋቢም ነበሩ።

"ዜና ቤተክርስትያን" በተባለው ጋዜጣ በምክትል አዘጋጅነት የሠሩትም እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ነበር።

ካሕሳይ ገ/እግዚአብሔር፤ ባደረባቸው ሕመም በጦር ኃይሎች፣ በቤተ ዛታ፣ እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ህክምናቸውን ቢከታተሉም፤ ስላልተሻላቸው ከነሐሴ መግቢያ ጀምሮ ቤታቸው ከአልጋ ላይ መዋላቸውን የሚቀርቧቸው ሰዎች ገልጸዋል።

ደራሲ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ካሕሳይ፤ የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።

"ካሕሳይ ደፋር ጸሐፊ ነው"

ደራሲ ጌታቸው በለጠ ከካሕሳይ ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ ይተዋወቃሉ። ከድርሰት ሥራ ባሻገር "አዲስ ዘመን" እና "የዛሬይቱ ኢትዮጵያ" ጋዜጦች ላይ በብዕር ስም በሚጻጻፉበት ዘመን ይተዋወቁ እንደነበር ጌታቸው ያስታውሳል።

"ትልቁ የካሕሳይ ጥንካሬ ሁለገብ መሆኑ ነው። በጋዜጠኛነቱም፣ በኢትዮጵያ ባህላዊ ጉዳዮች ላይ፤ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ባህል ላይ፤ ከሀይማኖት ጋር በተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮችም ደፍረው ከሚጽፉ ጸሐፊዎች መካከል ነው" ሲል ይገልጻቸዋል።

ጌታቸው እንደሚለው፤ ደራሲ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ካሕሳይ የሚያምኑበትን ነገር ደፍረው ከመናገር፣ የማይስማሙበትን ከመሞገት ወደኋላ አይሉም። እንደምሳሌ የሚጠቅሱት፤ በኢትዮጵያ የምንኩስና ታሪክ ውስጥ ያነሷቸውን ጠንካራ ሀሳቦች ነው።

ደራሲያን ማኅበረሰባዊ ጫና፣ ኃይማኖታዊ ጫና እና ፖለቲካዊ ጫናም እንዳለባቸው ጠቅሶ፤ ካሕሳይ ይህንን ማለፋቸው "ከሁኔታዎች በላይ ለህሊናው እና ለሙያው ታማኝ እንደሆነ ያሳያል" ሲል ያስረዳል።

"የትኛውንም ጉዳይ ከብሔርም ሆነ ከሀይማኖት ጋር ሳይፈርጁ እውነት ብቻ ይዘው ይሄዳሉ"

ሙዓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔርን፤ በብዕር ስም ለኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ጠዋት ፕሮግራም ጅግጅጋ ሆነው ሲያቀርቡ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚያስታውሳቸው ገልጾ፤ በኋላም ወደ ቤተ ክህነት መጥተው በቅርበት አብረው መሥራታቸውን ይናገራል።

ቤተ ክህነት ውስጥ የ "ዜና ቤተክርስትያን" ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ሆነው እንዳገለገሉም ያስታውሳል።

ዲ/ን ዳንኤል፤ ካሕሳይ መጽሐፋቸውን በሚጽፉበት ወቅት ይመካከሩ እንደነበር አስታውሶ፤ "አሁን ባለንበት ዘመን፤ የኢትዮጵያን ትውፊቶች፣ በገበሬው ዘንድ ያሉትን በተለይ በአማራና በትግራይ አካባቢ የሚነገሩትን ጥንታዊ ትውፊቶችና በትውፊቶች ውስጥ ያሉትን እውቀቶች፤ የመምህር ካሕሳይን ያህል የሚያውቃቸው አለ ብሎ ማለት ያስቸግረኛል" ሲል ይናገራል።

በፎክሎርና ባህል ጥናት ላይ የተሰማሩ ምሁራን፤ የጥናት ዘዴውን ያውቁት ይሆናል የሚለው ዲያቆን ዳንኤል፤ ይዘቱን በእርሳቸው መጠንና ዝርዝር የሚያውቅ አለ ብሎ ለማለት እንደሚከብደው ጨምሮ ያስረዳል።

ካሕሳይ ላመኑበት ነገር ወደኋላ የማይሉ ናቸው የሚለው ዲ/ን ዳንኤል፤ የትኛውንም ጉዳይ ከብሔርም ሆነ ከሀይማኖት ጋርም ሳይፈርጁ እውነት ብቻ ይዘው እንደሚሄዱም ይናገራል።

መምህር ካሕሳይ በአንድ ወቅት ከመነኮሳት ጋር በተያያዘ የጻፉት መጽሐፍ፤ ከአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሰዎች ጋር እንዳጋጫቸው በማስታወስም፤ "መጽሐፋቸውን ለማስመረቅ አዳራሽ ሲከለከሉ ከአዳራሽ ውጪ መንገድ ላይ አስመርቀዋል" ይላል።

"ላመኑበት ነገር ቆራጥና የሀሳብ ሰው ናቸው" የሚለው ዲ/ን ዳንኤል፤ ሦስቱም የ "ኅብረ ብዕር" ቅጾች በያዟቸው እውቀቶች ብልጫ፤ ከሥራዎቻቸው ሁሉ ገዝፈው እንደሚታዩት ይናገራል።

ቃላዊና ትውፊታዊ መረጃዎችን በጽሑፍ በማስቀረታቸውና ያንን ትልልቅ እውቀት ለትውልድ በማሸጋገራቸው ሲታወሱ ቢኖሩ ደስ እንደሚለው ጨምሮ ገልጿል።

"በዕጽዋት ላይ ይመራመር ነበር"

ካሕሳይን ለዓመታት ከሚያውቋቸው መካከል አንዱ የሆኑት ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ፤ ካሕሳይን የሚገልጿቸው "እውነተኛ፤ ሀቀኛ፣ ለጋዜጠኝነት፣ ለመምህርነት፣ ለደራሲነት የሚገባ ሰው ነው" በማለት ነው።

ካሕሳይ ከሚያምኑበት ጉዳይ ውጪ የማይጽፉ፣ የማይናገሩ ሰው እንደነበሩም ያስታውሳሉ። "ቤተ ክህነት ውስጥ ሆኖ የሚያያቸውን ስህተቶች ሁሉ በመጽሐፍ ለንባብ ያበቃ ጎበዝ፣ ደፋር ጋዜጠኛ ነው" ሲሉም ንጉሤ ይገልጻሉ።

ከ40 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሬድዮ፣ በእሑድ መርሀ ግብር ካሕሳይ በጽሑፍ፣ ንጉሤ ደግሞ በድምጽ ይሳተፉ ነበር።

"ካሕሳይ ሳይንቲስትም ነው" የሚሉት ንጉሤ፤ በሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ዲፕሎማ ያላቸው ካሕሳይ፤ በእጽዋት ላይ ምርምር ያደርጉ እንደነበርም ያክላሉ።

ለሥነ ጽሑፍ ሥራ ሲዘዋወሩ በእጽዋት ላይ ጥናት ያደርጉ እንደነበር ይገልጻሉ። "እስካሁን እድሜው የረዘመው በእነዚህ እጽዋት አማካይነት የባህል መድኃኒቶችን እያዘጋጀ ስለሚጠቀም ነው" ሲሉም ይናገራሉ።

ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተወላጆች ጋር፤ ብሔርና ቋንቋን መሰረት ሳያደርጉ፤ በስምምነት መሥራት እንደሚችሉም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

"ሞቱ ለአገር ጉዳት ነው" ሲሉም ንጉሤ ተናግረዋል።