አፍሪካ ቀንድ፡ አሜሪካ ሱዳን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ የማታነሳው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱዳን ምጣኔ ሀብታዊ 'ነፍስ ውጪ-ነፍስ ግቢ' ላይ ናት። የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚዋን አገርጅፎታል። ገንዘቧ የዚምባብዌ ዕጣ እንዳይገጥመው ተሰግቷል።
አባይ ካርቱም ከተማን እስከ ወገቧ ነክሯታል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት እንኳን አልተረፈም። ደግ ነው የሚባለው የሱዳን ሕዝብ ዕለታዊ ዳቦ ቅንጦት ሆኖበታል።
ይሄኔ ነው አሜሪካና እስራኤል ፈገግ ያሉት። አንድ ቁልፍ ነገር ለማሳካት ትክክለኛው ጊዜ እንደመጣ ገብቷቸዋል።
በጣላቶቿ የተከበበችው እስራኤል ከአረብ አገራት የምትፈልገው ብዙ ነገር አይደለም። እውቅና ማግኘት ብቻ። ሌላው ትርፍ ነው። የአየር ክልል መከፈት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ይህን ተከትለው የሚመጡ ናቸው።
ከዕውቅናው በኋላ አረቦቹ የቴክኖሎጂና የጦር መሣሪያ ደንበኞቿ ይሆናሉ።
የትራምፕ አስተዳደር ከአረቦቹ ጋር በምንም ነገር ሊደራደር ይችላል። በእስራኤል የመጣ ግን በዐይኑ መጣ ማለት ነው ይባላል።
ሱዳን ፈተና የገጠማትም ለዚሁ ነው። ዕድልም ገጥሟታል። ማይክ ፖምፔዮ በቅርቡ ወደ ካርቱም ብቅ ብለው ነበር።
"እኔ ምለው፤ ብንተጋገዝ አይሻልም?" አሉ።
"እንዴት አድርገን?" አለች ሱዳን።
እዚህ ጋ ነው ፍጥጫው የተጀመረው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማዕቀቡ ያን ያህል ከባድ ነው?
ሱዳን ላይ የተጣለባት የማዕቀብ አለት የዋዛ አይደለም።
ሽብርን በአገር ደረጃ ከሚደግፉ አገራት ተርታ ነው ጥቁር መዝገብ ላይ ወስዳ የጻፈቻት፤ አሜሪካ ሱዳንን።
ይህ ማዕቀብ ለሱዳን ቢነሳላት የዐይን ሞራዋ ተገፈፈ ማለት ነው። ዶላርን ማየት ቻለች ማለት ነው። ለሕዝቧ ዳቦ አደለች ማለት ነው።
ሱዳን እዚህ ቅርቃር ውስጥ ከገባች 30 ዓመት ሊሆናት ነው። አምባገነኑ አልበሽር ናቸው ከዚህ ማጥ ውስጥ የዶሏት። ነገሩ ውስብስብ ይመስላል።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1989 አልበሽር መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ። ካርቱምን የአሸባሪዎች መናኽሪያ ለማድረግ ወራት እንኳን አልወሰደባቸውም።
ጂሐዲስቶች ነጻ አገር አገኙ። በአሜካና በምዕራቡ ላይ ለመዝመት እንቅስቃሴያቸውን ከዚያ ማድረግ እንደጀመሩ ይነገራል።
አልቃኢዳና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ሱዳንን የጦር ቀጠናቸው አደረጓት። በአሜሪካ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በግብጽ፣ በኢትዮጵያ፣ በዩጋንዳና በኬንያና በታንዛኒያ እንዲሁም በየመን ለተፈጸሙ ጥቃቶች ግንኙነት ሲካሄድ የነበረው ከሱዳን እንደነበር የደኅንነት መረጃዎች አመላክተዋል።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1993 በኒውዮርክ መንትያ የንግድ ማዕከላት ሕንጻዎች የተፈጸመው የመጀመሪያው የቦንብ ጥቃት ነበር። ያን ጊዜ አሜሪካ ሱዳንን በደማቅ ብዕር በጥቁሩ የአሸባሪ አገራት ዝርዝር መዝገብ ላይ አሰፈረቻት።
እነሆ ከ30 ዓመታት በኋላም የዚያ ጥቁር የቀይ ቀለም አልደረቀም። ጥቁር መዝገቡም እንዳለ ነው። ሱዳን አሁን ሕልሟ ከዚህ ክፉ መዝገብ ስሟን መፋቅ ብቻ ነው።
ሱዳንና ሲአይኤ
የኒውዮርኩን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ከጀርባ የምትዘውራቸው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሱዳንን ፊት ነሷት።
አሜሪካ ስታዝን ቀድመው የሚያነቡ አንዳንድ የሱዳን አረብ ጎረቤት አገራት ከሱዳን ጋር ተኳረፉ። ጎረቤቶቿ ከኩርፍያም አልፈው የሱዳን መንግሥትን የሚገዳደሩ ሽምቅ ተዋጊዎችን ማስጠለል ጀመሩ።
ሱዳን ጫናው ሲበረታባት እ.አ.አ በ1996 ከኒውዮርኩ የመጀመሪያ የቦንብ ጥቃት ሦስት ዓመት በኋላ፤ ኦሳማ ቢን ላደንና ወዳጆቹን "ከይቅርታ ጋር ከግዛቴ ውጡልኝ" ብላ አሰናበተቻቸው።
ከዚህ በኋላ ትልቁ ክስተት 9/11 ተብሎ የሚታወቀው ከሃያ ዓመታት በፊት የተፈጸመው የሽብር ጥቃት ነው።
በዚህ የዓለምን ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በለወጠው ጥቃት አሜሪካ ሱዳንን ተጫነች። ሱዳንም ነገሩ ሳያስደነግጣት አልቀረም። ጥቁር እንግዳዋ የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ይህን ያህል ጉዳት ያደርሳል ብለው አላሰቡ ይሆናል። ሱዳኖች ለሲአይኤ ፍጹም ተባባሪ ሆነው ቆዩ።
በአልበሽር ዘመን የሱዳን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ከሲአይኤ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሠርቷል። ቢን ላደን ግን ያን ጊዜ ቶራ ቦራ መሽጎ ነበር።
ሱዳን ከዚያ ጥቃት ማግስት ጀምሮ ለአሜሪካ ያሳየችው ተባባሪነትና መሽቆጥቆጥ ከሽብር አገራት ተርታ ሊያወጣት ይገባ ነበር። ያ ግን አልሆነም።
አንዱ ምክንያት የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት አባላት (ሴናተሮች) ለሱዳን በጎ አመለካከት ማሳደር ስላልቻሉ ነበር።
ሴናተሮቹ የአልበሽር አስተዳደር በዳርፉር የሰው ልጆች ላይ የፈጸመውን ግፍ ቸል ብለው ማለፍ አልፈለጉም። ስለዚህ ሱዳን በዚህ ጥቁር መዝገብ ስሟ እንዲቆይ ተወሰነባት።
የአልበሽበር መንግሥት ማዕቀቡ እንደማይነሳለት ሲረዳ በድብቅ ከኢራን እና ከሐማስ ጋር መተባበር ጀመረ።
ለምሳሌ የእስራኤል አውሮፕላኖች መዳረሻቸውን ወደ ሐማስ ያደረጉ የመሣሪያ ክምችት የጫኑ ከባድ ተሸከርካሪዎችን በሱዳን የቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ አግኝተው ከጥቅም ውጭ አድርገዋል፤ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ።
አልበሽር ከሳዑዲና ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በደረሰባት ከባድ ጫና ከኢራን ጋር መሥርታው የነበረውን ግንኙነት በ2016 ቆርጣዋለች።
ይህ ውሳኔዋ ግን ማዕቀቡን እንዲላላላት አላደረገም። ምናልባት ከሳዑዲና ከኢምሬትስ የተወሰነ የኪስ ገንዘብ አግኝታበት ይሆናል ብለው የሚገምቱ አሉ።
እንዲህ እንዲያ እያለ ነው ባለፈው ዓመት በሱዳን ድንገቴ የሕዝብ አብዮት የተቀሰቀሰው። በአብዮቱ የገዛ ጄኔራሎቻቸው በአልበሽር ላይ ፊታቸውን አዞሩና ሱዳን ሌላ መልክ ያዘች። ይወድቃሉ ተብለው ያልታሰቡት አልበሽር ወደቁ።
ለሦስት ዐሥርታት ከተጫኑባት አምባገነን ገዢም ተገላገለች።
ከዚህ በኋላ ነገሮች አልጋ በአልጋ ይሆናሉ ተብሎ ነበር የታሰበው። ዋሺንግተን ግን እጅግ የማትወዳቸው መሪ ዞር ብለውላትም እምብዛምም ለመተባበር አልፈቀደችም።
የነገሮች ሁሉ ቁልፍ ያለው በአሜሪካ እጅ ነው። አሜሪካ ማዕቀቡን ስታነሳ ሱዳን ንግድ ይደራላታል። ግሽበት እየገዘገዘው የሚገኘው ኢኮኖሚዋም ያንሰራራል።
አሜሪካ ግን ይህ እንዲሆን ለጊዜው የፈቀደች አትመስልም። ለምን?
አሜሪካ ለምን እምቢ አለች?
ሱዳን ችግር ላይ ናት ሲባል ቀልድ ይመስላል። በጣም ከባድ ችግር ላይ ነው ያለችው። ቶሎ ማዕቀቡ ካልተነሳላት ያ ሁሉ የሕዝብ አብዮት ተስፋ አፈር ይበላል።
የዲሞክራሲ ሽግግሩም እክል ይገጥመዋል። እርግጥ ነው አሜሪካ ይህ እንዲሆን አትፈልግም። ለአሜሪካ መልካም የሚሆነው በሱዳን የምዕራቡን የዲሞክራሲ እሴቶች የሚያከብር መንግሥት እንዲፈጠር ነው።
ሱዳን ሽግግሩ ካልተሳካላት በድጋሚ የአሸባሪዎች መናኸሪያ እንዳትሆን ስጋት አለ።
ሱዳን የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ 72 ቢሊዮን ዶላር እዳ አለባት። ይህ ካልተቃለለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ብሎ ነገር አይኖርም።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሌለ ደግሞ ንግድ አይነቃቃም። ሥራ ፈጣሪ አይኖርም። ሕዝብ በልቶ ማደር አይችልም።
ሱዳናዊያን በጣም ተቸግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሱዳን 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ረሐብ እያንዣበበበት ነው የሚል አስደንጋጭ ሪፖርት አውጥቷል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነው ደግሞ ኮቪድ-19 ነው። ሌላ ጆሮ ደግፍ ደግሞ ጎርፉ ነው። የሱዳን ችግር ከዚህ በኋላ በዳቦ እደላ የሚፈታ አይደለም። በቢሊዮን ዶላሮች ብድር ማግኘት አለባት። ቢሊዮን ዶላር እዳ ሊሰረዝላት ይገባል። ኢንቨስተሮች በስፋት ወደ ሱዳን ሊገቡ ይገባል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ሱዳንን ከአሸባሪ አገራት ተርታ ካስቀመጣት ጥቁር መዝገብ ለመፋቅ አዝጋሚ ሂደት ተጀምሮ ነበር። በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ እክል ገጠመው።
ለዚህ የመጀመሪያው እርምጃ የሆነው አልቃኢዳ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት በተለይም በየመን ላደረሰው ጉዳት ለሟችና ተጎጂ ቤተሰቦች ሞቅ ያለ ካሳ መክፈል ነበር። ሱዳን ይህን ለማድረግ ዓይኗን አላሸችም።
ገንዘብ ባይኖራትም ከዚያም ከዚህም ብላ የካሳ ብር አዘጋጀች፤ 335 ሚሊዮን ዶላር አሁኑኑ እሰጣለሁ አለች።
ነገር ግን ባለፈው ወር መስከረም የአሜሪካ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ቸክ ሹመር እና ቦብ ሜናንዴዝ ሂደቱን አስቁመውታል።
ምክንያታቸው ደግሞ የመስከረም 11ዱ ጥቃት ሰለባዎችም በዚህ ካሳ ውስጥ መግባት አለባቸው የሚል ሐሳብ በመጠንሰሱ ነው።
ሱዳን ይህ አዝጋሚ ሂደት እያቆሰላት ይገኛል። ሱዳን ጊዜ የላትም። ጥምር መንግሥቱ ሊፈርስ፣ ሕዝቡም አደባባይ ተመልሶ ሊወጣ ይችላል። ነገሮች በፍጥነት መሻሻል አለባቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ ይህንን የሱዳንን መጨነቅና መጠበብ ለራሷ ፍላጎት ማዋል ትፈልጋለች።
ነሐሴ መጨረሻ ሱዳንን የጎበኙት ማይክ ፖምፔዎ አንድ ሐሳብ ይዘው ነበር የሄዱት፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላ ሐምዶክ።
"ከዚህ ሁሉ ጣጣ ብትወጡ አይሻልም?"
"መንገዱን ያመላክቱን ክቡር ሚኒስትር"
"እናንተ እስራኤልን እውቅና ስጧት፣ ትራምፕ ኮንግረሱ ያስቆመውን የማዕቀብ መነሳት ሂደት በፍጹማዊ ሥልጣኑ ይቀልብሰው።"
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለፈው ወር ለእስራኤል እውቅና መስጠቷን ተከትሎ ሱዳን ተመሳሳይ እርምጃ ከወሰደች 4ኛዋ የአረብ ሊግ አባል አገር ትሆናለች ማለት ነው።
ፖምፒዮ ይህ እንዲሆን የሚፈልጉት ትራምፕ ለምርጫ ከመቅረባቸው በፊት ነው።
ጄኔራሎቹ ምን አሉ?
ከእስራኤል ጋር ዓይንና ናጫ ሆነው መቆየት የሚፈልጉት ኢስላሚስቶች አሁን ከአልበሽር ጋር ወይ ዘብጥያ ወርደዋል ወይ ከፖለቲካው ገሸሽ ብለዋል።
አሁን በሱዳን ያለው የአደራ አስተዳደር ነው። የወታደሩና የሲቪሉ ጥምረት ይህን ትልቅ ውሳኔ ለመወሰን ሥልጣኑ አለው ወይ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐመዶክ ይህን ውሳኔ ቢወስኑ ብዙ ቀውስ ውስጥ ይገባሉ። የጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደሩም የመፍረስ አደጋ ይገጥመዋል።
ለፖምፒዮም በግልጽ የነገሯቸው ይህንኑ ነው። ይህንን ውሳኔ እልባት መስጠት የሚችለው ሕዝብ የሚመርጠው ቀጣዩ የሱዳን መንግሥት ብቻ ነው።
እርግጥ ነው አሁን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክና ሲቪል አስተዳደሩ ቢሮ ቢውልም ዋናው ሥልጣን ያለው አሁንም በወታደሮቹ እጅ ነው።
ሳዑዲ፣ ግብጽና ኢምሬቶች የሚደግፏቸው የሽግግር ካውንስሉ ሊቀመንበር ሌተናል ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና ምክትላቸው ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ ወይም በቅጽል ስማቸው ሐሜቲ ወታደሩን ብቻ ሳይሆን በሱዳን ካዝና የሚያዙ ቁልፍ ሰዎች ናቸው።
እነዚህ ጄኔራሎች ናቸው አሁን ከእስራኤል ጋር መነጋገር የጀመሩት።
ጄኔራል ቡርሃን የእስራኤልን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁን በየካቲት አግኝተዋቸው ነበር።
ናታንያሁን ለማግኘት ሲሄዱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዱክ እንኳ አላሳወቋቸውም ነበር። ጄኔራሉ ከናታኒያሁ ጋር በድጋሚ ለመገናኘትም ቀጠሮ ይዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጄኔራል ቡርሃንና ለጄኔራል ሐሜቲ ለእስራኤል እውቅና መስጠትና ከማዕቀቡ መገላገል ምርጫቸው ነው። ሁለቱ ጄኔራሎች ይህ እንዲሆን የሚፈልጉበት ሌላ ቁልፍ ምክንያት አላቸው።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ የሕዝብ አመጽ አልበሽርን በትረ መንግሥት ሲነቀንቅ ሁለቱ ጄኔራሎች ናቸው አገሪቱን የተቆጣጠሩት። ከሁለት ወራት በኋላ ወታደሮቻቸው ሰልፈኞችን ገድለዋል።
ይህንን ግድያ የፈጸሙ እንዲጠየቁ ሕዝብ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ከሲቪል አስተዳደር ጋር ሥልጣን ለመጋራት እምቢታን ይመርጣሉ ተብሎ ተሰግቶ ነበር። አሜሪካ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ሳዑዲና ኤምሬትስ ጫና ፈጥረው ነገሩ እውን አደረጉት እንጂ ሱዳን ከአንድ አምባገነን ወደ ሌላ ልትሸጋገር ጫፍ ደርሳ ነበር።
አሁን ጄኔራሎቹና የሲቪል አስተዳደሩ ሥልጣን ይጋራል። ጄኔራሎቹ በአልበሽር ጊዜ ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጥያቄ ውስጥ መግባት አይፈልጉም። ይህ እንዲሆንላቸው ግን ቶሎ ለእስራኤል እውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል።
በሌላ ቋንቋ አሁን ወታደሩ የሲቪል አስተዳደሩን እየታገሰ ያለው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና እንዳይነፈገው ስለሰጋ ብቻ ነው። እንጂ ሙሉ ሥልጣኑን ቢቆናጠጥ ይመርጣል።
ሕዝቡ ወታደሮቹ ያደረሱበትን በደል ግን አልረሳላቸውም። ተጠያቂ የማያደርጋቸው ሁሉም ሥልጣን በእጃቸው ስላለ ብቻ በአቅም ማጣት ነው። ይህ ማለት ለጄኔራሎቹ ከሥልጣን መራቅ ማለት ዘብጥያ ከመውረድ ብዙ አይለይም።
በሱዳን እድሜያቸው የገፉት የዚያኛው ትውልድ አባላት ኦፕሬሽን ሙሴን አይረሱም። በዚያ ዘመን ከእስራኤል ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያስታውሳቸዋል።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1984 በወቅቱ የነበሩት ፕሬዝዳንት ጃፋር ኒሜሪ የእስራኤል ልዩ ኃይልና ሞሳድ ሱዳን መጠለያ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን ከኢትዮጰያ የሄዱ ቤተ እስራኤላዊያንን በምስጢር እንዲወስዱ ፈቅደው ነበር።
ኒሜሪ በኋላ ላይ ከእስራኤሉ ሞሳድ ለዚህ ተግባራቸው ጠቀም ያሉ ሚሊዮን ዶላሮችን ለዚህ ትብብራቸው እንደተቀበሉ ይነገር ነበር።
አሁንም ቢሆን በሱዳን ትልቁን ቢዝነስ ከጀርባ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት የቀድሞ መኮንኖች እንደሆኑ ይታወቃል። በአልበሽር ጊዜ የጦር መኮንን የነበሩት ሁሉ ወደ ንግድ ገብተዋል። ገንዘቡ የሚዘወረው በእነርሱ ነው።
ማዕከላዊ ባንኩ ብር ሲቸግረው፣ መንግሥት ደመወዝ የሚከፍለው ሲያጣ እነዚህን የቀድሞ ጄኔራሎች ለምኖ ነው የሚበደራቸው።
ይህ ሁኔታ ሱዳን ወደፊትም በፖለቲካና ወታደራዊ ኃይል የአገሪቱን ሃብት በተቆጣጠሩ ኃያላን [ክሊፕቶክራሲ] የምትዘወር አገር እንደምትሆን የሚጠቁም ነው።
እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ግንኙነቷን ማለሳለስ ትፈልጋለች። እውቅ ማግኘት ደግሞ ቀዳሚው ፍላጎቷ ነው።
አሜሪካ ይህ የእስራኤል ህልም እንዲሳካ ትሰራለች። ትራምፕ ይህን አሳክተው ሳምንታት ብቻ በቀሩት ምርጫ ሞገስን ማግኘት ይሻሉ።
ሳዑዲና ኢምሬትስ ሱዳን ከእነሱ ፍላጎት እንዳትርቅ ፍላቶታቸው ነው። ሱዳኖች የዳቦ ጥያቄ በቶሎ እንዲመለስላቸው ይሻሉ። የሲቪል አስተዳደሩ ግን ለእነዚህ ሁሉ ፍላጎቶች ተገዢ መሆን ፈተና ሆኖበታል።
ወጣት እስራኤላዊያንና አሜሪካዊያን መንግሥታቸው ከነጄኔራል ቡርሃን ጋር አዲስ ፍቅር ለመጀመር መፈለጉ ልባቸውን ይሰብረዋል።
ምክንያቱም ጄኔራሎቹና ወታደራዊ መኮንኖቹ በአልበሽር ዘመን ለተፈጸሙ ዘግናኝ እልቂቶች በአንድም ሆነ በሌላ ተጠያቂ ናቸው። በተለይም የዛሬ 15 ዓመት በዳርፉር ለሆነው ጭካኔ የሚጠየቅ አለመኖሩ ያሳዝናቸዋል። በዳርፉር ያኔ የሞተው ሰው ከሩብ ሚሊዮን በላይ ነው።
በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ስሜት የሚሰጥ አመክንዮ እየተናገሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ናቸው።
ለእስራኤል እውቅና መስጠትና ሱዳንን ከጥቁሩ የአሸባሪ አገራት መዝገብ መፋቅ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ሁለቱን ለምን እናገናኛቸዋለን?
ሐምዶክ እያሉ ያሉት ሱዳን አሸባሪዎችን ጠራርጋ አባራለች። ሱዳን ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ገንዘብ መድባለች።
ሱዳን አሁን የዲሞክራሲ ጭላንጭል እያየች ያለች አገር ናት። ይቺን አገር ለእስራኤል እውቅና ካልሰጠሽ ብሎ ማስጨነቅ ዲሞክራሲን ማዳፈን ነው ይላሉ።
ሐምዶክ ይቀጥላሉ፣ "የእስራኤልን የዕውቅና ጉዳይ በዲሞክራሲ ምርጫ የሚመጣው መንግሥት ይጨነቅበት። አሁን ዳቧችንንና ዲሞክራሲያችንን አትንፈጉን።"
አሜሪካኖች ለጊዜው ሐምዶክን የሚሰሙበት ጊዜ ላይ አይደሉም። ሱዳን የአሜሪካንን ምርጫ ውጤት ከአገሬውም በላይ በጭንቀት የምትከታተለው ወ'ዳ አይደለም።












