ሱዳን፡ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ሱዳን ሊመጡ ነው

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በሱዳን ይፋ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ጉብኝቱ ሁለቱ አገራት ወዳጅነታቸው እየታደሰ መሆኑን ማሳያ ነው ተብሏል።

ሱዳን አሁንም ቢሆን አሜሪካ በአገር ደረጃ ሽብርን ይደግፋሉ ከምትላቸው አገሮች ተርታ አልወጣችም።

ይህ ማለት ሱዳን በአሁን ሰዓት እጅግ የተጠማችውን ብደር እና የውጭ ኢንቨስትመንት ማግኘት አትችልም።

ሆኖም የሱዳን የሽግግር መንግሥት አሜሪካ አገራቸው ከዚህ የአሸባሪ አገራት ዝርዝር ትፍቀናለች ብሎ ተስፋ እያደረጉ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ተስፋው እውን ለመሆኑ እየተቃረበ መሆኑን ማሳያ ነው ይላሉ።

ፖምፔዮ ወደ ሱዳን ብቅ የሚሉት በእስራኤል ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይፋ ባደረገው መረጃ ፖምፒዮ የሱዳንን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክና የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር ውይይት ያደርጋሉ።

አሜሪካ ለሽግግር መንግሥቱ ድጋፍ ታደርጋለች፤ ሱዳንና እስራኤል የሚቀራረቡበትን መንገድም ትሻለች ብለዋል።

ባለፈው ጥቅምት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ከጄኔራል ቡርሃን ጋር በኡጋንዳ ተገናኝተው ነበር። ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን እንዲሰምር እንደሚሰሩም ቃል ተገባብተው ነበር።

ይህን ተከትሎም ይመስላል በዚህ ሳምንት ሱዳን አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የነበሩን ሰው ከሥራ ያሰናበተችው። ምክንያቱ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከእስራኤል ጋር ያደረገችውን ታሪካዊ ስምምነት በስሱም ቢሆን በመተቸታቸው ነው ተብሏል።

ይህም ሱዳን ከእስራኤልና ከአሜሪካ ጋር ለመወዳጀት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነች የሚመሰክር ነው።

አልበሽር ከረዥም የስልጣን ዘመን በኋላ መነሳታቸውና አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ በሱዳን ጉብኝት ማድረጓ ነገሮች መልካቸውን እንደሚለውጡ በቂ ማሳያዎች ተደርገው ተወስደዋል።

የአልቃኢዳ መሪ የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ለአምስት ዓመታት በሱዳን መኖሩ ይታወቃል። ያን ጊዜ ቢን ላደን የአልበሽር እንግዳ ሆኖ ነበር የቆየው።

አሜሪካ በየመን በ2000 ዓ.ም የደረሰባት ጥቃት ሱዳን እንዳቀነባበረችው ታምናለች። በዚህ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 17 የባሕር ኃይል አባላት መገደላቸው ይታወሳል።

ሱዳን ለሟች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል መስማማቷም የቅርብ ጊዜ ዜና ነበር።