ሱዳን፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሱዳን ሄዱ ማይክ ፖምፒዮም ካርቱም ገብተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ሱዳን ዛሬ ማለዳ ማምራታቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካርቱም በሚኖራቸው ቆይታ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሐንና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ውይይት ያካሂዳሉ ሲል ጽህፈት ቤታቸው ገልጿል።
በተመሳሳይም አሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ታሪካዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማክሰኞ ከእስራኤል ጉዟቸው በማስከተል ሱዳን ገብተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ሱዳን ሲጓዙ ከ15 ዓመታት በኋላ በአንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው።
ለዓመታት ተበላሽቶ የቆው የአሜሪካና የሱዳን ግንኙነት ባለፈው ዓመት ኦማር ሐሰን አልብሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣናቸው ከተወደዱ በኋላ እየተሻሻለ መጥቷል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የሱዳን መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሆኑት ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሉዓላዊ ምክርቤቱ ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተነግሯል።
በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በሱዳን ባለስልጣናት መካከል የሚደረገው ውይይት ሱዳን ለምታደርገው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አሜሪካ በምትሰጠው ድጋፍ፣ ሱዳን ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ስለምትወጣበት ሁኔታና ሱዳን ከእስራኤል ጋር ስላላት ግንኙነት ላይ ያተኮረ ይሆናል ተብሏል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ቀደም ሲል እስራኤል ውስጥ ጉብኝት በማድረግ ከከፍተኛ አገሪቱ ባለስልጣናት ጋር የተወያዩ ሲሆን የሱዳኑ ጉብኝታቸውም ያንን ተከትሎ የሚከናወን ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሱዳን ባቀኑበት ዕለት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ወደ ካርቱም እንደሚገቡ መገለጹ በሁለቱ መካከል ውይይት ለማድረግ የሚያስችል እድል እንዳለ እየተነገረ ነው።
በተለይ ደግሞ ከወራት በፊት በአሜሪካ አደራዳሪነት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ሲካሄድ የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ በዚሁ አጋጣሚ ሊነሳ እንደሚችል ተገምቷል።
ኢትዮጵያ ያለባትን የኤሌክትሪክ ኃይል እግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሳ ባለፉት በርካታ ዓመታት የስትገነባው በቆየውና ወደ መጠናቀቁ በተቃረበው ግዙፍ ግድብ ዙሪያ ሦስቱ አገራት መቋጫ ያላገኘ ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በግድቡ የውሃ አሞላልና የሥራ ክንውን ዙሪያ መግባባት ያልቻሉት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ እየተጀመረ በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆረጥ የቆየ ውይይትና ድርድር ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በተለይ ከወራት በፊት ዋሽንግተን ውስጥ የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ ተሳታፊ የነበሩበት ድርድር ወደ መጠናቂያው በተቃረበበት ጊዜ ኢትዮጵያ ጥቅሜን የሚየስከብር አይደለም በማለት ከስምምነቱ እራሷን ማግለሏ ይታወሳል።
በግድቡ ድርድር ጉዳይ ላይ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉት እንደነበረ ይታወቃል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ የሱዳን ጉብኝት ከበርካታ ዓመታት በኋላ በአንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን የተደረገ ቀዳሚ ጉብት ነው።
ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ሱዳንን የመሩት ኦማር ሐሰን አልበሽር ከረዥም የስልጣን ዘመን በኋላ መነሳታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል በር ከፍቷል።
ሱዳን የአልቃኢዳ መሪ የነበረውን ኦሳማ ቢን ላደን አስጠግታ በማቆየትና የተለያዩ የሽብር ቡድኖችን በመደገፍና በአሜሪካዊያንና በአሜሪካ ጥቅሞች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ገብታ ቆይታለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፒዮ ወደ ሱዳን የሚያቀኑት በእስራኤል፣ በባህሬንና በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት የጉዞ ፕሮግራማቸው ውስጥ አንድ አካል ሆኖ ነው።















