የናይጄሪያ ወጣቶች ሶስት ፖሊስ ጣቢያዎችን አቃጠሉ

የተቃጠሉ ፖሊስ ጣቢያዎች

በናይጄሪያ ደቡብ ምስራቅ የምትገኘው አናምብራ ግዛት የሚገኙ የተቆጡ ወጣቶች ሶስት ፖሊስ ጣቢያዎችን አቃጠሉ።

ለቁጣቸው ምክንያት አንድ በሞተር ሳይክል ታክሲ የሚተዳደር ግለሰብ በፖሊስ ተገድሏል መባሉን ተከትሎ ነው።

ኤበሬ ንዎግባ የተባለው ግለሰብ የኮሮናቫይረስ የሰዓት እላፊ መመሪያን ጥሰሃል በሚልም ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አውለውት ነበር።

ፖሊሶቹ ከበውትም እያለ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታውን ሲከታተሉ የነበረ ሲሆን ይህንንም ለመበተን ፖሊሶች ሽጉጥ እንደተኮሱም የአይን እማኞች ተናግረዋል።

ከተተኮሱትም ሽጉጦች መካከል የሟቹን ሆድ እንደመታውም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

"ፖሊሶቹ በሽጉጥ ከመቱት በኋላ መንገድ ላይ ትተውት በሞተር ሳይክላቸው ሄደዋል። በዚህም ምክንያት ሞቷል" በማለት ኦካፎዙ ኡጎቹክው የሚባል ነዋሪ ተናግረዋል።

ግለሰቡ የተገደለው ማክሰኞ እለት ሲሆን በቁጣ የነደዱ ወጣቶችም በትናንትናው ዕለት ወደ ከተማው ፖሊስ ጣቢያዎች በመሄድ በእሳት አጋይተዋቸዋል።

ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ወደ አቅራቢያዋ ባሉ ኤክውሎቢያና ኦኮ ወደተባሉ ከተሞች በመሄድም ነው ፖሊስ ጣቢያዎቹን ያቃጠሏቸው።

የግዛቲቷ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ጆን አባንጋ በበኩላቸው ከግለሰቡ ግድያ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ፖሊሶች ክስ ይመሰረታል ብለዋል።