ራሷን ጎዳና ላይ ያዋለደችው እናት በአዳማ

ይህ የሆነው አዳማ ከተማ ነው። ታሪኩ ደግሞ የአንዲት ወጣት። ወጣቷ ኑሮዋን መስርታ የነበረው ጎዳና ላይ ነው።
የጎዳና ላይ ኑሮ ደግሞ በችግሮች የተሞላ ነውየምትለው ጠይባ እርሷና ጨቅላ ልጇ ወደሚኖሩባት አዳማ የመጣችው የእለት ጉርስ ለማግኘት፣ ሰርቶ ለማደር በመሻት ነበር።
ጠይባ በሥራ ምክንያት ከጭሮ ወደ አዳማ የመጣችው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው።
"አባትና እናት የለኝም። ትምህርት ስለጨረስኩ ሥራ ይገኛል መባሉን በመስማቴ ነው ወደ አዳማ የመጣሁት" ስትል ለቢቢሲ ቃሏን ሰጥታለች።
ጠይባ አዳማ ላይ ሥራ ስትፈልግ በሌላ በኩል ፍቅር የልቧን ደጃፍ አንኳኳ እናም የወንድ ጓደኛ ይዛ አብረው መኖር ጀመሩ።
በዚህ መካከል ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች።
ጓደኛዋ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ያለ ወጣት እንደነበር የምትናገረው ጠይባ የተለያዩ ጥቃቶች ያደርስባት እንደነበር ትናገራለች።
በየዕለቱ የሚደርስባት ድብደባ ስለበዛባት የሰባት ወር ነፍሰጡት ሆና ወደ ጎዳና ወጣች።
"እዚሁ አዳማ ኃይለማርያም ሆስፒታል አጠገብ ሳድር ነበር፤ ሲገኝ በልቼ ሳጣ እንዲሁ ጦሜን እያደርኩ ከረምኩ። የሰባት ወር ነፍሰጡር ሆኜ እስክወልድ ድረስ እዚያው ነው የኖርኩት።"
ደራሽ ምጥ ጎዳና ላይ
ጠይባ ሕይወቷን የአዳማ ጎዳናዎች ላይ ከማድረጓ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ የእርግዝና ክትትል ለማድረግ ወደ ሕክምና ተቋም ሔዳ እንደማታውቅ ለቢቢሲ ተናግራለች።
በተወለደችበት አካባቢ እናቶች ሲወልዱ ምን እንደሚያስፈልጋቸውና ምን ማድረግ እንዳለባት ስትሰማ ስለነበር ይህንኑ እራሷ ላይ ለመተግበር እንደወሰነች ታስረዳለች።
ድንገት ምጧ መጥቶ የሚያዋልዳት በዙሪያዋ ባይኖር፣ የጤና ተቋም የሚያደርሳት ቢጠፋ፣ የልጇን እትብት የምትቆርጥበት ምላጭ ማዘጋጀቷን ገልጻለች።
" እናቶቻችን ነፍሰጡር ሴት ምላጭ ከእጇ ማጣት እንደሌለባት ሲናገሩ እሰማ ነበር። እኔም ቀድሜ ምላጭ ገዝቼ ቦርሳዬ ውስጥ አስቀመጥኩኝ"
ጠይባ የገመተችው ከመሆን ያገደው አንዳች ነገር የለም። የመውለጃዋ ቀን በተቃረበበት ሰሞን ልብስ ለማጠብ ውሃ ወዳለበት ሰፈር እየሄደች ሳለች ሕመም ጀመራት፤ ምጧ መምጣቱን አልተጠራጠረችም።
" . . .የሕመም ስሜት ሲሰማኝ፣ በአቅራቢያዬ ወደነበረው የመኪና ማጠብዬ ተጠግቼ፣ መኪና የሚያጥቡ ሰዎች የሚያርፉበት ክፍል ገባሁኝ" በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
እርሷ እንደምትለው ከሆነ፣ በክፍሉ ውስጥ የነበሩ ሰዎች፣ እርሷ ምጥ ላይ መሆኗን ሲያውቁ፣ ክፍሉን ለቅቀው የሄዱ ሲሆን እርሷም ብቻዋን ልጇን በሰላም ተገላግላለች።
" ምጥ መሆኑን እንዳወቅኩኝ ቶሎ ብዬ ምላጩን ከቦርሳ ውስጥ አወጣሁኝ፤ ትንሽ ቆይቼ ልጁ ልክ እንደተወለደ ራሴን ሳልስት እትብቱን በጣቶቼ ሰፍሬ ቆረጥኩኝ። ከልብሴ ላይም ክር ቆርጬ የልጄን እትብት አበትኩኝ። ከዚያ በኋላ የማስታውሰው ከላይ የለበስኩትን ለልጄ ማልበሴን ብቻነው፤ ወዲያው ራሴን ሳትኩ"
ከአንድ ሰዓት በኋላ ሰዎች መጥተው ከስፍራው እንዳነሷት እና የሕክምና ተቋም እንደወሰዷት የምትናገረው ጠይባ፣ በአሁኑ ሰዓት እዚያው አዳማ ከተማ የተወሰኑ ሰዎች ባደረጉላት ድጋፍ ቤት ተከራይታ መኖር ጀምራለች።
"ያኔ የነበረውን ነገር ሳስታውስ እንቀጠቀጣለሁ፤ ነገር ግን እንኳንም ሁለት ሆንን በልጄ ደስተኛ ነኝ። ካሁን በኋላ ምንም ብቸገር ልጄን አሳድገዋለሁ። የልጄ ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። እርሱም ከጠነከረ ስራ እጀምራለሁ" በማለት ያላትን ተስፋ ትገልጻለች።
የአዳማ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከሚበዙባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ ናት። በአዳማ ከተማ አስተዳደር የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባለሙያ የሆኑት አቶ ኢደኦ ደዋኖ በአዳማ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕጻናትና እናቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል።
በተለያየ ችግር ከአጎራባች ዞኖች የሚመጡ ሰዎች ወደ ጎዳና ኑሮ ይገባሉ ሲሉም ይናገራሉ።
ምን ያህል ሰዎች በጎዳና ላይ እንደሚኖሩ ግን የከተማ አስተዳደሩ በቁጥር የተደገፈ መረጃ እንደሌለው በመግለጽ አዳማ ጎዳና ላይ ሁሌም አዳዳስ ፊቶች ኑሮ ጀምረው እነደሚታዩ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በከተማይቱ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎችን የማንሳት ስራ የተጀመረ ቢሆንም፣ አዳዲስ ሰዎች በሚነሱ ሰዎች በመተካት እንዲሁም የተነሱ ሰዎች ቦታ በመቀየር ወደ ጎዳና በመመለሳቸው፣ ችግሩ መፍትሔ እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል።
የጎዳና ተዳዳሪዎችን በዘላቂነት በመደገፍ እና መልሶ በማቋቋም ላይ በቋሚነት የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ባለመኖራቸውም ችግሩ እንዳይፈታ ምክንኣት ሆኗል ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናቅቀዋል።












