በተስፋ መቁረጥና በስጋት ውስጥ የሚገኙት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር አርሶ አደሮች

በምዕራብ ጎንደር ዞን በተለይም መተማና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች የሱዳን ወታደሮች ዘልቀው በመግባት በአርሶ አደር ማሳዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና ሰዎች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናትና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለቢበሲ እንደተናገሩት 200 የሚደርሱ አርሶ አደሮች ንብረት የወደመባቸው ሲሆን ከ1700 በላይ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር ፋይሳል ሳሊህ የአገራቸው ወታደሮች በሁለቱ አገራት አዋሳኝ የድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ተይዞ የቆየ ነው ካሉት መሬት ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠራቸውን ባለፈው ቅዳሜ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህ የድንበር ላይ ፍጥጫ ሳቢያ ጉዳት ከደረሰባቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል የተወሰኑትን ስለገጠማቸው ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በመተማ ወረዳ 400 ሄክታር የሚሆን የእርሻ መሬትን በመውሰድ ሲያለሙ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ከሰተ ውበቱ፤ በስፍራው ከ12 ዓመት በላይ የግብርና ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ይናገራሉ።
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ግን "የሱዳን ወታደሮች ወደ እኔ እርሻ አካባቢ እየመጡ አልፎ አልፎ ጥቃት ያደርሱ ነበር" የሚሉት አቶ ከሰተ፤ በዚሁ ምክንያትም ከእርሻ ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ወጥተው ነበር።
ነገር ግን ሥራቸውን ማቆማቸውን የተገነዘበው የአካባቢው አስተዳደር ወደ እርሻ ልማታቸው መመለስ እንዳለባቸው ማሳሰቡን ተከትሎ "ወደ ቦታዬ ተመልሼ በመግባት ማረስ ጀምሬ ነበር" ይላሉ።
ይሁንና በተለያዩ ጊዜያት የሱዳን ወታደሮች በአካባቢው የሚሰማሩ የቀን ሠራተኞችን እያባረሩ በማስቸገራቸው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በስፍራው እንዲሰፍር ተደርጎ የግብርና ሥራቸውን ማከናወን እንደቻሉ ገልጸዋል።
ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም ጠዋት ግን፣ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ ማታ እነሱ [የሱዳን ወታደሮች] መምጣታቸውንና እርሳቸው "ወረራ" ያሉት ክስተት መጀመሩን አስረድተዋል።
"በዘጠኝ መኪና ነው ተጭነው የመጡት" የሚሉት አቶ ከሰተ፣ "መትረየስ የጫኑ መኪኖች፣ ከኋላ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን [ሱዳናውያን] በማስከተል በእርሻ ቦታችን ላይ ወረራ ፈጸሙብን" ይላሉ።
አቶ ከሰተ በማሳቸው ላይ ሱፍ፣ ጥጥ እና ሰሊጥ ዘርተው እንደነበርና ሁሉም ለመሰብሰብ ደረሰው እንደነበር በመጥቀስ ለጥቃቱ የተሰማሩት "የቻሉትን እየሰበሰቡ ጭነው በመውሰድ ቀሪውን በማቃጠል አውድመውታል" ብለዋል።
"በማሳ ላይ እየሰራን እንዳለ እየተኮሱ መጡብን። ከዚያ የተወሰነ ለመከላከል ብንሞክርም አቅም ስላጣን ሁሉንም ነገር ጥለን ወጣን" ብለዋል።
በተለምዶ የሁለቱ አገራት ድንበር ጓንግ ወንዝ ቢሆንም አሁን ግን ያንን ተሻግረው ወረራ መፈጸሙን ገልጸዋል። "ቢያንስ የ3 ሰዓት የእግር ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ተጉዘው ነው ወረራ የፈጸሙብንም" ብለዋል። አቶ ከሰተ በተወሰነው የማሳቸው ክፍል ላይ በአማካይ እስከ 500 ኩንታል ሰሊጥና እስከ 200 ኩንታል ማሽላ ያመርቱበት እንደነበር ገልጸዋል።
የእርሻ ሥራውን "ተበድሬ ነበር የምሰራው፣ አሁን ግን ይህ አደጋ በመከሰቱ እንኳን ለማትረፍ ብድሬንም ለመክፈል ተቸግሬያለሁ፣ በዛሬው ዕለት ራሱ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድርህን የማትመልስ ከሆነ ቤትህ ይሸጣል የሚል ማስታወቂያ ቤቴ ላይ ለጥፈው ሂደዋል" በማለት ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
አክለውም "አሁን ባደረግኩት ማጣራት 89 ኩንታል ሰሊጥ፣ በርካታ የሱፍና ጥጥ ምርት ወስደውብኛል" ብለዋል። በአሁኑ ገበያ የአንድ ኩንታል ሰሊጥ ዋጋ 5 ሺህ ብር አካባቢ ደርሷል ያሉት አቶ ከሰተ፣ ይህም 450 ሺህ ብር አካባቢ እንደሚገመት ገልጸዋል።
በተጨማሪም "ማሳውን ስናሰራው የነበረው በቀን ሰራተኛ ነበር፤ ነገር ግን ደመወዛቸውን መክፈል ባለመቻላችን እስከ 250 የሚደርሱ ሠራተኞችን አሰርተን አሁን እየከሰሱን ነው" ብለዋል።
ሌላኛው በዚሁ ወረዳ [መተማ] ደለሎ በሚባል የእርሻ ቦታ ጉዳት ከደረሰባቸው አርሶ አደሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ይበይን ይባላሉ።
በክረምቱ ወቅት የጸጥታ አካል አብሮን በመኖሩ ምንም ጉዳት አልደረሰብንም፤ "ነገር ግን ጦሩ አካባቢውን ለቅቆ ወደ ትግራይ መሄዱን ተከትሎ የሱዳን ወታደር ተከታትሎ መጥቷል" ብለዋል። ወታደሩን ተከትለው ደግሞ በቅርብ የሚገኙ ሁለት የሱዳን ከተማ ነዋሪዎች በመምጣት ዘረፋና ውድመት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
የሱዳን ወታደሮች ወደ አካባቢው ሲገቡ ጥቃት እየፈጸሙ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ይበይን፣ በዚሁ የተኩስ ልውውጥም "ሁለት የጉልበት ሠራተኞች ተገድለውብኛል፣ ሌሎች ሁለት ሠራተኞች ደግሞ በከባድ ተጎድተውብኛል" ብለዋል።
ከእዚህም በተጨማሪ በርካታ የካምፕ ቁሳቁስ አውድመዋል የሚሉት አቶ ይበይን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ጭነው ሲወስዱ ቀሪውን ደግሞ አውድመውታል ብለዋል።
አርሶ አደሩ አቶ ይበይን በዘንድሮው የእርሻ ዘመን ሙሉውን ማሳቸውን የማሽላ ሰብል ዘርተው እንደነበርና ከእዚህ ውስጥም አብዛኛው እንደተወሰደ ቀሪውም እንደወደመ በመግለጽ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብና ንበረት ኪሳራ እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን አካባቢው ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የሱዳን ወታደሮች በሁሉም ቦታዎች በቋሚነት ሰፍረው አይቀመጡም የሚሉት አቶ ይበይን፤ ሰሞኑን ድጋሚ ወደ ማሳቸው በመሄድ 400 ኩንታል ያህል ማሽላ ለመሰብሰብ መቻላቸውን ይገልጻሉ።
ይህንን ማሳ ከ15 ዓመት በላይ እንዳረሱት የተናገሩት አቶ ይበይን፣ በአማካይ በዓመት በብር ደረጃ ሲተመን ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ብር ከወጭ ቀሪ ያገኙበት እንደነበር ገልፀው፤ በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ በዚህ ዓመት ከባድ ኪሳራ እንደገጠማቸው አመልክተዋል።

ሙላት ነጋሽ ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ በምትገኘው ምድረ ገነት ውስጥ ሲሆን በግብርናው ዘርፍ ተሠማርተው ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል።
አሁን ግን የሱዳን ጦር የኢንቨስትመንት ቀጣና ወደሚባለው የምዕራብ አርማጭሆ በጣም ሰፊ ቦታ ላይ በመግባት ከማሳቸው እንዳፈናቀላቸው ይናገራሉ።
በአካባቢው የነበረው የመንግሥት ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል ለሌላ ተልዕኮ መሰማራቱን ተከትሎ፣ የድንብር አካባቢውን ለቅቆ ሲሄድ ቀጠናው ክፍት መሆኑን ተከትሎ፣ የሱዳን ኃይሎች ሰፊ የግብርና ልማት ወደሚካሄድበት ቦታ ዘልቀው መግባታቸውን አስታውቀዋል።
"አብዛኛው በአካባቢው በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ሰው ከሥራ ውጪ ሆኗል። ማሽላውንም እየጫኑት ነው። ቁጥራቸው በምዕራብ አርማጭሆ ከ200 በላይ፣ በመተማ ደግሞ ቁጥሩን [በትክክል ባላውቀውም] እስከ 50 ገበሬዎች ተፈናቅለዋል። በኢንቨስተመንት ቀጠናዎች መኪናና የእርሻ መሣሪያ የተወሰደባቸው አሉ" ብለዋል ለቢቢሲ።
"ሉግዲ አካባቢ ወደ ስምንት ኮምባይነር [ማጨጃ ማሽን] አስገብተው ነበር። ኃይላቸው ከፍ ስላለ መግባት አልቻልንም። ኮምባይነሩ ትልቅ ጉልበት ስላለው ማሳ ላይ ያለውን ማሽላ ለመውሰድ በስፋት እየሰበሰቡ ነው" ብለዋል።
በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ምድረ ገነት ከተማ አስተዳደር ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፋሲል አሻግሬም "የሱዳን ጦር ወደ ድንበር ገብቷል። እነሱ ተጠናክረው ስለመጡ በተኩስ ለመቋቋም አልተቻለም። ኮምባይነር ይዘው መጥተው ምርቱን ሰብስበው እየጫኑ ነው። ቆርጠን የከመርነውን ሁሉ እየጫኑ ሲሆን አካባቢያችንን በሙሉ ተቆጣጥረውታል" ሲሉ ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በማሳ ላይ ካለው ሰብል በተጨማሪ ለግብርና ሥራው የሚውሉ ንበረቶችንና የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎችን መውሰዳቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
"እኛ ቁጭ ብለናል። እጅ እና እግራችን ታስሮ ምን እናድርግ? ምን አቅም አለን? መንግሥት አዝመራው ተዘርፎ ሳያለቅ ይድረስልን ብንልም መልስ የለም። እኛ ከሞትን ደግሞ የምናመጣው ለውጥ የለም" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
"መንግሥት ትንሽ ትንሽ ኃይል ያቀርባል። ይህም መከላከል ብቻ ነው የሚሠራው። አገር አደጋ ላይ ነች። ለእኔ ሳይሆን አገር እንደ አገር በከፋ አደጋ ላይ ነች። ከ200 በላይ ገበሬ ተዘርፏል" ብለዋል።
የሱዳኑ የማስታወቂያ ሚንስትር ፋይሳል ሳሊህ የአገራቸው ወታደሮች በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ተይዞ ከሚገኘው መሬት ውስጥ "በአሁኑ ጊዜ ከ60 አስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሱዳን መሬትን መልሶ ይዟል" በማለት ከቀናት በፊት ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም "ማንኛውም ችግር በውይይት ይፈታል ብለን እናምናለን" ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም በአዋሳኝ የድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመቅረፍ የተጀመረውን ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ለረጅም ጊዜ ሁለቱን አገራት ሲያወዛግብ የቆየው የድንበር አካባቢን በተመለከተ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የሚያስችል ኮሚሽን ተቋቁሞ ካርቱምና አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ቢያደርግም ሁለቱንም የሚያስማማ ውጤት ላይ ሳይደረስ ቆይቷል።













