በነቀምቴ አንድ ቤተክርስቲያን በተፈጠረ መገፋፋት ህይወት ሲያልፍ ሰዎች ተጎዱ

የቤተክርስቲኗ መስራች ነብይ መሰረት ታዬ

የፎቶው ባለመብት, ARAARAA CHURCH/FACEBOOK

የምስሉ መግለጫ, የቤተክርስቲኗ መስራች ነብይ መሰረት ታዬ

በምዕራብ ኦሮሚያ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ነቀምቴ ውስጥ ትናንት ቅዳሜ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይደረጋል በተባለ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ በተገኙ ምዕመናን መካከል በተፈጠረ መረጋገጥ የአንድ ሰው ህይወት ሲጠፋ ሌሎች ላይ ጉዳት ደረሰ።

በጸሎት ፕሮግራሙ ላይ ለመሳተፍ ከአርብ ሌሊት ጀምሮ በነቀምቴ ከተማ በሚገኘው በእግዚአብሔር ምህረት ዓለም አቀፍ ቤተክረስቲያን መግቢያ በር ላይ ተሰልፈው ሲጠባበቁ በነበሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎችና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

አራራ ተብሎ በሚታወቀው በዚህ ቤተክርስቲያን በሚካሄደው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ ቦታዎች በመምጣት ሲጠባበቁ ከነበሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረው ግርግር የአንዲት ሴት ህይወት ሲያልፍ 8 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ምን ተፈጠረ?

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ቤተክርስቲያኒቱ በርካታ ሰዎች የሚያሳተፉበት የጸሎት ፕሮግራም ለቅዳሜ ታኅሣስ 24/2013 ዓ.ም አዘጋጅታ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚሁ ፕሮግራም ላይ ለመገኘትም በርካታ ሰዎች ቀድመው ቦታ ለመግኘት ከአርብ ማታ ጀምረው በቤተክርስቲያኒቱ በር ላይ ተሰልፈው ሲጠባበቁ እንደነበርና ሌሊት ላይ ወደ ውስጥ ለመግባት በሚሞክሩበት ጊዜ ግርግር ተፈጥሮ ነበር ብለዋል።

በወቅቱም የተፈጠረውን ግርግር ለማረጋጋት ፖሊሶች ወደ ሰማይ ጥይት መተኮሳቸውን እንደሰሙ ገልጸው፤ በዚህ ምክንያትም ሰዉ ተደናግጦ ሲሮጥ መገፋፋትና መረጋጋጥ ተፈጥሮ ጉዳት ሊደርስ እንደቻለ ጠቅሰዋል።

በጸሎት ፕሮግራሙ ላይ ከአርብ ጀምሮ በስፍራው የነበሩትና ቢቢሲ ቅዳሜ ከሰዓት ያናገራቸው ወ/ሮ አስቴር በላቸውም አርብ ሌሊት የተፈጠረው ችግር ፕሮግራሙን ለመሳተፍ ከመጣው ሕዝብ ብዛት ምክንያት በተከሰተ መገፋፋት የተነሳ ነው ይላሉ።

በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ የተወሰዱበት የነቀምቴ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሐኪም ዶክተር ምሬሳ በንቲ ሰዎች በግርግሩ ተጎድተው ለህክምና መምጣታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ዶከተር ምሬሳ ጨምረውም ሆስፒታላቸው ተጎዱ ሰዎችን ከአርብ ሌሊት 10 ሰዓት ጀምሮ መቀበሉን ገልጸው፤ ለህክምና የመጡት 8 ሰዎች በተለያየ ደረጃ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ለሁለቱ ቀዶ ህክምና መደረጉን ተናግረዋል።

አንዲት ሴት ግን ሆስፒታል ከመድረሷ በፊት ህይወቷ ማለፉን አመልክተው በአጠቃላይ በክስተቱ 8 ሰው ሲጎዳ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን እንደሚያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወደ ሆስፒታሉ የመጡ አብዛኞቹ ሰዎች የጉዳታቸው ምክንያት በተፈጠረው መገፋፋት ድንጋይ ላይ በመውደቅና በመረጋገጥ እንደሆነ መናገራቸውን ዶክትር ምሬሳ ገልጸው፤ አንዳንዶቹ ግን ምን እንደተፈጠረ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ይህንን ክስተት ተከትሎ አንድንድ ወገኖች የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ እንደከፈቱ ቢገልጹም፤ ቢቢሲ ያናገራቸው የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ተፈሪ ታደሰ ግን ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

ጨምረውም ጉዳቱ በርካታ ሰው የጸሎት ፕሮግራሙ ላይ ለመሳተፍ በተሰበሰበበት ጊዜ በተፈጠረ መገፋፋት መድረሱን ገልጸው፤ ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ ለማረጋጋት በቦታው መገኘቱንና ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ የማጣራት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው ሰዎች ተጎዱ የተባለው ፍጹም ውሸት መሆኑን ተናግረው "ይህንንም በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችንና የቤተክርስቲያኒቱን ኃላፊዎች በመጠየቀ ማወቅ ይቻላል" ብለዋል።

ቢቢሲ አርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ በነቀምቴው የእግዚአብሔር ምህረት ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን (አራራ) ስለተፈጠረው ነገር ዝርዝር ለመጠየቅ የቤተክረስቲያኒቱን ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።