ኮሮናቫይረስ ፡ እስራኤል የኮቪድ-119 ክትባትን ለበርካታ ሰዎች በመስጠት ቀዳሚ ሆነችነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
እስራኤል ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕዝብ የኮሮናቫይረስ ክትባትን በመስጠት ከዓለም አገራት ቀዳሚ ሆነች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የወረርሽኙ ክትባት መስጠት ከተጀመረ ወዲህ እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት ሰጥታለች።
እስራኤል ከ100 ሰዎች ከ11 በላይ ሰዎችን ስትከትብ፣ ባህሬን በ3.49 እና እንግሊዝ ደግሞ በ1.47 እንደሚከተሉ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጋር የሚሠራው ዓለም አቀፍ የክትትል ድረ-ገጽ ዘግቧል።
ለንጽጽር ያህል ፈረንሳይ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ታኅሣስ ወር ውስጥ በአጠቃላይ 138 ሰዎችን ብቻ ከትባለች።
በዓለም ዙሪያ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ 1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል።
አሜሪካ 2020 ከመጠናቀቁ በፊት 20 ሚሊዮን ሰዎችን የመከተብ ዕቅዷን ማሳካት ሳትችል 2.78 ሚሊዮን ዜጎቿን ብቻ ነው መከተብ የቻለችው።
አስካሁን የተሰጡት ክትባቶች የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ሲሆን የመጀመሪያውን የወሰዱ ሰዎች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መከተብ ይጠበቅባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕንድ በሚቀጥለው ሳምንት ብሔራዊ ተቆጣጣሪ ያፀድቀዋል ተብሎ የሚጠበቀውን ክትባት ለሕዝበወ ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገች ነው።
እስራኤል ለምን ቀዳሚ ሆነች?
እስራኤል ክትባቱን ከሳምንት በፊት መስጠት የጀመረች ሲሆን ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ፣ ለጤና ባለሙያዎችና ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት በየቀኑ 150 ሺህ ሰዎችን እየከተበች ነው።
ወረርሽኙ እንደተከሰተ የተደረጉ ስኬታማ ድርድሮችን ተከትሎእስራኤል የፋይዘር-ባዮኤንቴክ ክትባት አግኝታለች። ክትባቱን በጤና አጠባበቅ ሥርዓቷ አማካይነት እየሰጠች ነው። በእስራኤል ሕግ መሠረት ሁሉም እስራኤላውያን እውቅና ባለው የጤና ተቋም መመዝገብ አለባቸው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዩሊ ኤደልስቴይን ለኤን ቲቪ እንደገለጹት እስራኤል የፋይዘር ክትባትን ደኅንነቱ እንዲጠበቅ በማድረግ ከፋፍላ አጓጉዛለች። ይህ ማለት አነስተኛ መጠን ያላቸው ክትባቶችን ርቀት ወደላቸው አካባቢዎች መላክ ይችላል።
እንደገና ለመመረጥ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ከየካቲት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ከወረርሽኙ መውጣት እንደምትችል ተንብየዋል። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛ ጊዜ ብሔራዊ የእንቅስቃሴ እገዳ ላይ ናት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ ለምን ወደ ኋላ ቀረች?
በተጠናቀቀው ዓመት ማብቂያ ላይ በተጀመረው የክትባት ዘመቻ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ፈረንሳይ ከ100 ያነሱ ሰዎችን ብቻ ከትባለች፡፡ ለንጽጽር ያህል በተመሳሳይ ጊዜ ጀርመን ከ130 ሺህ በላይ ክትባቶችን ሰጥታለች።
የአውሮፓ ሕብረት ክትባቶቹን ለመፍቀድ ከእንግሊዝ እና ከአሜሪካ ዘግይቶ ነበር። ለሕብረቱ አባል አገራት ተቆጣጣሪ አካል የሆነው የአውሮፓ መድኃኒቶች ኤጄንሲ ለፋይዘር ክትባት እውቅና የሰጠው ከሳምንት በፊት ነበር።
በፈረንሣይ የሚታየው ሌላው ችግር ክትባቱን በተመለከተ ሰፊ ጥርጣሬ መኖሩ ነው። በአይፖስ ግሎባል አማካሪ በተካሄደው የሕዝብ አስተያየት ጥናት መሠረት 40 በመቶ የሚሆኑት ፈረንሣያዊያን ብቻ ናቸው ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹት።
ይህ ቁጥር ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር በቻይና 80 በመቶ፣ በዩናይትድ ኪንግደም 77 በመቶ እና በአሜሪካ ደግሞ 69 በመቶ ይደርሳል።
ሕንድ ምን እየሠራች ነው?
ሕንድ በክትባት መርሃ-ግብሩን ለመተግበር የሚረዳትን ብሔራዊ ልምምድ እያካሄደች ሲሆን በአዲሱ ዓመት አጋማሽ 300 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ አቅዷለች።
በመንግሥት በሚደገፈው በኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባት ላይ አደምነቷን ጥላለች። ይህም የክትባቱ ለማጓጓዝ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ስለማይፈልግ በርቀት ለሚገኙ የህክምና ተቋማት ለማሰራጨት ምቹ ያደርገዋል።
በሕንድ ውስጥ በባራት ባዮቴክ እየተሠራ የሚገኘው ክትባት እውቅናን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ኮቪድ-19 እስካሁን 150 ሺህ የሚጠጉ ሕንዳዊያንን ሕይወት ቀጥፏል። 10 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በበሽታው ተይዘውባታል፤ ይህም ከአሜሪካ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።















