ኮሮናቫይረስ ፡ የኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ጥያቄ እንዴት ይመለሳል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በቀጣይ ወራት ቢያንስ 20 በመቶ ለሚሆኑ ዜጎች የኮሮናቫይረስ ክትባት እንድታገኝ ለማስቻል እየተሠራ እንደሆነ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለሕዝም ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ፤ የዓለም አገራት ክትባቱን እንዲያገኙ የሚያስተባብረው ኮቫክስ የተባለው ጥምረት አባል እንደመሆኗ፤ እንደሌሎች አገራት ሁሉ ክትባቱን እንዲደርሳት ይደረጋል ብለዋል ሚንስትሯ።
"በበጀት እና በክትባት ተደራሽነት ላይ እየተሠራ ስለሆነ እንደ ሌሎች አገራት ኢትዮጵያ ቢያንስ 20 በመቶ ለሚሆነው ዜጋ ክትባት እንድታገኝ ይደረጋል" ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ባላት አቅም ከምትገዛው ክትባት ባሻገር በልገሳ ተጨማሪ ጠብታ እንድታገኝ እንደሚደረግም ሚንስትሯ ተናግረዋል።
የጤና ሚንስትሯ፤ ኢትዮጵያም ለኮቫክስ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥያቄ እንዳቀረበች ከሳምንታት በፊት መናገራቸው አይዘነጋም።
ዶ/ር ሊያ ጨምረውም፤ ለአገልግሎት ብቁ ከሆኑ የክትባት አይነቶች መካከል ኢትዮጵያም እንድታገኝ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮቫክስ በኩል ክትባቱን በፍጥነት ለማግኘትና በቅድሚያ መከተብ ለሚገባቸው ወገኖች እንዲደርስ ለማድረግ እንደሚሰራም መግለጻቸው ይታወሳል።
እስካሁን በተደረጉ ምርምሮችና ሙከራዎች በርካታ ተስፋ ሰጪ ክትባቶች ተገኝተዋል። ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑና ለጤና ባለሙያዎችም እየተሰጠም ነው።
ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል የእድሜ ባለጸጎችና የቀደመ ህመም ያለባቸው በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።
እስካሁን ቀዳሚውን የተጠቃሚነት ዕድል ያገኙት ባለ ጸጋ አገራት ሲሆኑ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ ክትባቱ ለሁሉም እንዲዳረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።
አገራትም ለዜጎቻቸው ክትባቱን ለማቅረብ ባላቸው አማራጮች ሁሉ እየሞከሩ ነው።
"አላማቸው ፍትሐዊ ስርጭት እንዲኖር ነው"
በስዊድን ማላርጋለን ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም ውስጥ መምህርና የሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት በንቲ ገለታ እንደሚሉት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አቅመ ደካማ አገሮች ክትባቱን ሊያገኙ የሚችሉት በኮቫክስ አማካኝነት ነው።
ኮቫክስ ስብስብ ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ክትባት ላይ የሚሰራው ጋቪ እና የወረርሽኝ ምላሽ የሚያስተባብር ተቋምም ይገኛሉ። በጋራ የሳይንሳዊ ፈጠራና የክትባት ስርጭትን ያስተባብራሉ።
"የክትባት ክፍፍል ስሌቱ በዓለም ጤና ድርጅት ነው የሚሠራው። በእድሜ እና በጤና ባለሙያ ስብጥር የሚወሰን ይሆናል" ሲሉ ያስረዳሉ።
አቅመ ደካማ አገሮች ክትባቱን ከማግኘት እንዳይገለሉ አቅምን የማስታበባር ስራ ይኖራል ሲሉም ያክላሉ።
"ዓለም አቀፉ የአጤና ድርጅት ገንዘብ ያላቸው አገሮች ምርቱን እንዲያግዙም ያደርጋል" ይላሉ።
በክትባት ሥራው 172 አገሮች እንደተሳተፉ ጠቅሰው፤ የቀለም፣ የእድሜ እና መሠራቱን ያስረዳሉ።
"የዚህ አገር ነው የሚባል አይደለም። አላማቸው ፍትሐዊ ስርጨት እንዲኖር ነው። ኮቫክስ ይህንን ይሰራል" ሲሉም ያክላሉ።
ከዚህ ቀደም የኮቪድ-19 ቁጥር ሪፖርት ሲደረግ ቻይና እና አሜሪካ መካከል ፉክክር እንደነበር እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት አቶ በንቲ፤ "ዓለም አቀፍ ፖለቲካው የክትባት ስርጭቱን ሊጎዳ ይችላል የሚል ፍርሀት አለ። ቢሆንም ግን ፍትሐዊ ስርጭት ይኖራል የሚል እምነት አለኝ" ሲሉ ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ክትባት ተገኝቷል በሚል ማሕበረሰቡ መዘናጋት እንደሌለበት ያሳስባሉ።
"ኮልድ ቼይን ወይም የቅዝቃዜ ሰንሰለት ክትባቱ ከተመረበት አንድ ቦታ እስከሚደርስ ያለው ሰንሰለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው መብራት ይጠፋል። የትራንስፖርት ችግርም አለ። እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጥንቃቄ ነው።"
እስከሚመጣው ዓመት መጨረሻ ድረስ በዓለም ሁለት ቢሊዮን የክትባት ጠብታ የማከፋፈል እቅድ አለ። ከዚህ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሽታው በጣም ተጋላጭ ለሆኑ አረጋውያን እና የጤና ባለሙያዎች ነው።
"አገራችን የወጣት አገር ናት። የእድሜ ባለጸጋዎች ቁጥር ትንሽ መሆኑ ከሚመደበው የክትባት ስሌት ሊያጎድል ይችላል" የሚሉት ባለሙያው፤ ክትባቱ ጥሩ መረጋጋት ቢያመጣም መዘናጋት እንዳይኖር ካሁኑ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያሰምሩበታል።
እስካሁን ድረስ ውጤታማ የተባሉ ክትባቶችን ዝርዝር እንመልከት።
ፋይዘር/ባዮንቴክ
ኮሮናቫይረስን በመከላከል 90 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለው ይህ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ይፋ የሆነው በፈረንጆቹ ሕዳር 9/2020 ነበር።
በወቅቱ ክትባቱን ይፋ ያደረጉት ፋይዘር እና ባዮንቴክ ኩባንያዎች ግኝቱ ለሳይንስና ለሰው ልጅ ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
የአሜሪካ እና የጀርመን ኩባንያ የሆኑት ፋይዘር እና ባዮንቴክ በስድስት የተለያዩ አገራት 43 ሺህ 500 ሰዎች ላይ መሞከራቸውን የገለጹ ሲሆን አንድም ጊዜ አሳሳቢ የጤና ችግር አልታየም ብለዋል።
አስትራዜኒካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ
አስትራዜኒካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እያበለፀጉ ያሉት ክትባት ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው ክትባቶች መካከል ነው።
ይሄው ክትባት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሙከራ መልክ ተሰጥቷል። ደቡብ አፍሪካ ለዚህ የክትባት ሙከራ የተመረጠችው በዘርፉ ባሏት ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያሉባትና ወረርሽኙም በፍጥነት እየተስፋፋባት በመሆኑ ነው።
ይህ የክትባት ሙከራ ኦኤክስ1ኮቪድ-19 ክትባት የሚባል ሲሆን፤ ኮሮናቫይረስን የሚያስከትለው ሳርስ-ኮቪ-2 በተባለው ቫይረስ ሰዎች እንዳይያዙ ለመከላከል የታለመ ነው።
ሞደርና
የዩናይትድ ስቴትስ መድኃኒት አምራች ኩባንያ የሆነው ሞደርና ከኮሮናቫይረስ 95 በመቶ የሚከላከል አዲስ ክትባት ማግኘቱን ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል።
ሞደርና የምርምር ውጤቱን ይፋ ያደረገበትን ዕለት "ታላቅ ቀን" በማለት ሐሴቱን ገልጿል።
ስፑትኒክ-5
ይህ ሩሲያ ሰራሽ ክትባት ይፋ በተደረገ ጊዜ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአገር ውስጥ በተደረገ ምርምር አገር በቀል ክትባት አግኝተናል፤ ለሰዎች አገልግሎት እንዲውልም ይፋዊና ብሔራዊ ፍቃድ ሰጥተናል ብለው ነበር።
በዓለም የመጀመርያው የተባለው ይህ ስፑትኒክ-5 ክትባት ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲትዩት ነው ያመረተው። ክትባቱ ይፋ የተደረገውም ነሀሴ ወር ላይ ነበር።
ኢንስቲትዩቱ እንደሚለው ክትባቱ አስተማማኝ የመከላከል አቅም ይሰጣል።
ሲኖቫክ
መላው ዓለም ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ደፋ ቀና ሲል ቻይናም እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ሲኖቫክ የተባለ ክትባት መስራት ከጀመረች ሰነባብታለች። እንደውም በጎ ፈቃደኞችን መከተብ ከጀመረች ቆየት ብላለች።
በቻይና በሙከራ ላይ የሚገኘው የኮቪድ-19 ክትባት አመርቂ የሚባል ውጤት እያስገኘ ነውም ተብሏል። ሆኖም ክትባቱ አመርቂ ውጤት ያስገኘው በረዥም የሙከራ ሂደት ውስጥ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሳይሆን፤ መካከለኛ ምዕራፍ በሚባለው ክፍል ነው።
















