ክትባት በማዘጋጀት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ የሚነገርለት ዓለም የዘነጋችው ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, WELLCOME TRUST
ዋልደማር ሃፍኪን ሞርዴካይ ከፓሪስ ሕንድ እየተመላለሰ በዓለም ቀዳሚ የተባለውን ክትባት ለኮሌራ መከላከያነት ፈበረከ።
ነገር ግን በድንገተኛ መርዝ ሕይወቱ እንዳይሆን ሆነች።
በፈረንጆቹ 1984 ዋልደማር ወደ ሕንዷ ካልካታ አመራ። ለኮሌራ ክትባት ፍለጋ።
ወቅቱ የፀደይ ወራት ነበር። ኮሌራ በሕንድ የሚፈላበት።
ተመራማሪው ወደ ሕንድ ይዞ ያቀናው ክትባት ኮሌራን ከዚህች ምድር ያጠፋል ብሎ አስቦ ነበር። ነገር ግን ተስፋው ከቀን ቀን እየጨለመ መጣ።
በወቅቱ ሕንድ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች። እንግሊዛውያን ቅኝ ገዢዎች ተመራማሪውን ሊያሰሩት አልቻሉም።
ዋልደማር የዱር እንስሳት ተመራማሪ ነበር። ዶክተር አልነበረም። ሩስያዊ አይደሁድ ነው። ብዙ ዘመኑን ያሳለፈው ግን ፓሪስ ነበር።
ዋልደማር የሕድን አፈር ሲረግጥ 33 ዓመቱ ነበር። ያመረተው ክትባት በሁለት ዙር የሚሰጥ ነው።
ለዋልደማርና የሥራ አጋሮቹ ተሳታፊዎችን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነበር። በዚያ ላይ የመጀመሪያውን ዙር ተከትበው ለሁለተኛው ዱካቸው የማይገኝ በርካታ ተሳታፊዎች ነበሩ።
መጋቢት 1984 ላይ የካልካታ ጤና ቢሮ እስቲ ብቅ ብለህ እዚህ አካባቢ ኮሌራ አለ ወይስ የለም የሚለውን አጣራ ብሎ ጋበዘው።
ይህ ለተመራማሪው ምቹ አጋጣሚ ነበር። በሄደበት ሥፍራ ያሉ በርካታ ሰዎች በየቤታቸው ተኝተዋል። የህመም ምልክታቸውም ተመሳሳይ ነበር።
ዋልደማር በሽታው የዘለቀበት ቤት ገብቶ ግማሾቹን ከትቦ ግማሾቹን ሳይከትብ ከወጣ ውጤቱን በግልፅ ማየት ያስችለዋል።
ሰውዬው ያደረገው ይህን ነው። ከ200 ታማሚዎች መካከል 116 ሰዎችን ከተበ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ በበሽታው 10 ሰዎች መሞታቸው ተሰማ። ሁሉም ሟቾች ካልተከተቡት መካከል ነበሩ።
ይህ ውጤት ለግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች ፅኑ ማስተማመኛ ነበሩ። ክትባቱን በርከት አድርገው ማዘዝ ይችሉም ነበር። ነገር ግን ስለ ክትባቱ ሰዎችን ማሳመን ራሱን የቻለ ሥራ ነበር።
ዋልደማር ከእንግሊዛውያን ሐኪሞች ይልቅ ከህንዳዊያን ዶክተሮች ጋር ተባብሮ መሥራት አዋጭ መሆኑን ተረድቶታል። ሰዎች እምነት እንዲጥሉበት በማለትም አደባባይ ላይ ቆሞ ክትባቱን ተወግቷል።
ዋልደማር ካልካታ ውስጥ ቀደምት የተባለ ክትባት ይሞክር፤ ብዙዎችን ያድን እንጂ ስሙ በሕንድም ሆነ በአውሮፓ እንዲሁም በተቀረው ዓለም እምብዛም አይነሳም።
ግሰለቡ ዩክሬን ከሚገኘው የኦዴሳ ዩኒቨርሲቲ በዱር እንስሳት ጥናት የተመረቀው በፈረንጆቹ 1884 ነበር። ፕሮፌሰር ለመሆን ቢያመለክትም አይሁድ በመሆኑ ምክንያት ተከልክሏል።
የሩስያ ጦር የአንድ አይሁድ ቤተሰብን ቤት ሲያወድሙ ተመልክቶ ሊያስቆም በመሞከሩ ምክንያት ድብደባና እሥር ደርሶበታል።
ይሄኔ ነው የትውልድ አገሩን ትቶ ወደ ጄኔቫ ከዚያም ወደ ፓሪስ ያቀናው። እዚያም በዓለም ታዋቂ በሆነ አንድ የባክቴሪያ አጥኚ ተቋም ውስጥ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ መሥራት ጀመረ።
በወቅቱ ኮሌራ በነፋስ አማካይነት የሚተላለፍ ተደርጎ ነበር የሚቆጠረው።
በኮሌራ ምርምር ላይ ጥናቱን አጠናክሮ የቀጠለው ዋልደማር ሙከራውን በጊኒ ፒግ ጀምሮ። ከዚያም ወደ ጥንቸል። ቀጥሎ ወደ ሰው ማምራት ጀመረ።
ሐምሌ 1892 ላይ ዋልደማር ራሱን አውቆ በኮሌራ በከለ። ለቀናት በትኩሳት ተሰቃየ። ነገር ግን ዳነ። ቀጥሎ በርካታ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ላይ መሞከር ጀመረ።
አንዱም ተሳታፊ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰበትም። ይሄኔ ተመራማሪው ለሰፊው ሕዝብ የሚሆን ክትባት እንደሰራ አመነ።
ነገር ግን በርካታ ፈቃደኛ ሰዎች ያሉበት አገር ማግኘት ነበረበት። ይሄኔ በወቅቱ በፓሪስ የእንግሊዝ የነበሩት ግለሰብ ወደ ቤንጋል እንዲሄድ መከሩት።
ሰውዬው ካልካታ ሄዶ ምርምሩ በተሳካላት ጊዜ አሳም ውስጥ ያሉ ሻይ ቅጠል አምራቾች መጥቶ ሠራተኞቻቸውን እንዲመረምርላቸው ጋዘቡት።
በደስታ እየፈነደቀ ወደ ሥፍራው ያመራው ዋልደማር በርካታ ሺህ ሰዎችን ከተበ። ነገር ግን በወቅቱ የወባ በሽታ ስለያዘው ወደ እንግሊዝ ተመልሶ እንዲያገገም ተገደደ።
የዋልደማር ማሕደር እንደሚያሳየው በወቅቱ ቢያንስ 42 ሺህ ሰዎችን ከትቦ ነበር።
ዋልደማር ስለ ክትባቱ ያስተዋለው ነገር ቢኖር መድኃኒቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ቢቀንስም በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ከሞት መታደግ አልቻለም።
1984 ላይ በቻይናዋ ዩናን ግዛት አንድ ወረርሽኝ ተነሳ። ከዚያም ወደ ሆንግ ኮንግ ተዛመተ። እያለም በብሪቲሽ ግዛት ወደ ነበረችው ቦምቤይ ደረሰ።
በወቅቱ የብሪቲሽ አገዛዝ ወረርሽኙ እምብዛም አደገኛ አይደለም ሲል አጣጣለው። ነገር ግን በሽታው ጥቅጥቅ ያለችውን ሞምቤይ እየሰረሰረ መዝለቅ ጀመረ።
ይህ ወረርሽኝ ገዳይነቱ ከኮሌራ ሁለት እጥፍ ነው። ይሄኔ ዋልደማር ተፈለገ። ዋልደማርም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ቦምቤይ አመራ።
ከሶስት ያልሰለጠኑ ረዳቶቹና ከአንድ ፀሐፊው ጋር በመሆን አንዲት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ይኖር ጀመር። ለወረርሽኙ መድኃኒት ፍለጋ ይዳክርም ገባ።

የፎቶው ባለመብት, WELLCOME TRUST
ክትባት መሥራት ብርቁ ያልሆነው ዋልደማር ለኮሌራ የተጠቀመውን መላ ተከትሎ ለአዲሱ በሽታ መድኃኒት ይፈልግ ጀመር።
በፈረንጆቹ ጥር 10/1897 ዋልደማር ከአዲሱ ወረርሽኝ 10 ሲሲ ቀንሶ ራሱን ወጋ። ለወትሮው የሚጠቀመው 3 ሲሲ ነበር።
ለጊዜው በከባድ ትኩሳት የተሰቃየው ዋልደማር ከቀናት ሕመም በኋላ አገግሞ ተነሳ።
ከዚያም ወደ ሕዝባዊ ሙከራው ተሸጋገረ። ወረርሽኙ አንድ እሥር ቤት መግባቱን ተከትሎ ወደዚያ አቅንቶ ክትባቱን እንዲሞክር ተፈቀደለት።
በእሥር ቤት ካሉ ታራሚዎች 147 ሰዎች ክትባት ተሰጣቸው። 172 ደግሞ ያለ ክትባት ክትትል እንዲደረግላቸው ሆነ።
ክትባቱ ከተሰጣቸው መካከል ሁለት ሰዎች በሽታው ተገኘባቸው። ካልተሰጣቸው መካከል ደግሞ 12 ሰዎች ተይዘው፤ 6 ሰዎች ሞቱ።
ይሄን ስኬት የተመለከተው ዋልደማር ክትባት በብዛት እንዲመረት እና ሰዎች እንዲወጉ ከአንዲት ክፍል ቤተ ሙከራው ሆኖ አዘዘ።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ክትባቱን ወሰዱ። በዚህም በርካታ ሰዎች ከወረርሽኙ ዳኑ።
ታህሳስ 1901 በእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ የጀግና ኒሻን ሽልማት ተሰጠው። ከዚያም ቦምቤይ ውስጥ 53 ሰዎች ያሉት አንድ ቤተ ሙከራን እንዲያስተዳድር ተሾመ።
ነገር ግን ድንገት አደጋ መጣ።
መጋቢት 10 ፑንጃብ ውስጥ ባለች አንዲት ግዛት 19 ሰዎች በቲታነስ ምክንያት ሞቱ። ለቲታነሱ ምክንያት ደግሞ የዋልደማር ክትባት ነበር።
ጉዳዩ ሲጣራ 53 ኤን የሚል ስያሜ የተሰጠው ጠርሙስ መዘዘኛ ሆኖ ተገኘ። ብልቃጡ ጊዜው ያለፈበት ክትባት ይዞ ነበር።
ምርመራው ተጠናክሮ ሲቀጥል ዋልደማር ክትባት የሚሰጥበትን ሂደት መቀየሩ ታወቀ። ተመራማሪው በፊት ክትባት መስጫውን በካርቦሊክ አሲድ ነበር የሚያጥበው። ነገር ግን ፍጥነት ለመጨመር ሲል በግለት ማፅዳት መጀመሩ ለችግሩ መንስዔ መሆኑ ተደረሰበት።
በዚህ ምክንያት ተመራማሪው ከቤተ ሙከራ ኃላፊነቱ ተባረረ። ዋልደማርም ሕንድን ጥሎ ወደ እንግሊዝ ተመለሰ።
ክትባት በማግኘቱ ምክንያት የጀግና ሽልማት የተሸለመው ዋልደማር የውርደት ማቅ ይከናነብ ገባ።
በዋልደማር ሥራዎች ላይ የተመረኮዘ መጽሐፍ ያሳተሙት ዶክተር ባርባራ ሃውጉድ ተመራማሪው በማንነቱ መግለል ይደርስበት ነበር ይላሉ።
ሌሎችም ተመራማሪዎች በዚህ ይስማማሉ። ምናልባት እንግሊዛዊ ቢሆን ኖሮ ይሄ አይደርስበትም ነበር ይላሉ።
ዋልደማር ከሥራው ከታገደ ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1904 ወረርሽኙ ጣራ ላይ ደርሶ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ፈጅቷል። መድኃኒቱ የዋልደማር ክትባት ቢሆንም እሱ ግን እንግሊዝ ውስጥ ቁጭ ብሏል።
የሰውዬው ሥራ ካጠኑ መካከል አንዱ የሆኑ ግለሰብ ምናልባትም ዋልደማር ሆን ተብሎ ይሆናል ከሥራው የታገደው ይላሉ። እንደ መከራከሪያ የሚያነሱት ነጥብ ደግሞ በወቅቱ ስለ ቴታነስ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩና ጠርሙሱ ሲከፈት ምንም ዓይነት የተለየ ጠረን ያለው አለመሆኑ ነው።
ወጣም ወረደ ዋልደማር ብዙ ኢ-ፍትሐዊ መገለሎች ደርሰውበታል የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ዋልደማር በወርሃ ኅዳር 1907 ከቁም እሥሩ ተለቆ ጉዳዩ በፓርላማ ታይቶለት ወደ ሕንድ ተመልሶ ሥራውን እንዲቀጥል ተፈቀደለት።
ነገር ግን ምንም ዓይነት የክትባት ሙከራ እንዳያደርግ ታገደ። ይሄኔ ፊቱን ወደ ኮሌራ በማዞር የተሻሻለ ክትባት ለማምረት መሥራት ጀመረ። ነገር ግን ሙከራ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ በሕንድ መንግሥት ውድቅ ተደረገበት።
በ1914፤ ዋልደማር በ55 ዓመቱ ሕንድን ጥሎ ወጣ።
ከ1897 እስከ 1925 ባለው ጊዜ 26 ሚሊዮን የዋልደማር ፀረ ወረርሽኝ ክትባቶች ከሞምቤይ ወደሌላ ዓለም ተልከዋል።
ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ክትባቱ ከ50-85 በመቶ ውጤታማነት ነበረው። ነገር ግን ምን ያህል ሰው እንደታደገ የሚሳይ መረጃ የለም።
ዋልደማር ወደ ፈረንሳይ ተመልሶ ሕይወቱን ወደ ቤተ እምነት አዞረ። በምዕራብ አውሮፓ የአይሁድ ትምህርትን ለማስፋፋት ብዙ ደከመ።
ዋልደማር አላገባም። ስለመውለዱም ምንም ዓይነት መረጃ የለም።
ዋልደማር ሃፍኪን ሞርዴካይ በ70 ዓመቱ በስዊተዘርላንዷ ሎውዛን ከተማ ይህቺን ዓለም በሞት ተሰናበተ።
ሕንድ እያለ ጥናቱን ሲያካሂድባት የነበረችው ቤተ ሙከራ አሁንም ጥቅም ላይ ትውላለች። ከመቶ ዓመታት በኋላም ዘንድሮ ዓለምን ያሸበረውን ኮሮናቫይረስን በመዋጋት ላይ ትገኛለች።
ዋልደማር ሃፍኪን ከመሞቱ አምስት ዓመታት በፊት በ1925 የሕንድ መንግሥት ቤተ ሙራዋን 'የሃፍኪን ተቋም' ሲል በስሙ ሰየመለት።
በጊዜው ዜናው የደረሰው ዋልደማር ቂም አልቋጠረም ነበር። "ቤተ-ሙከራዋን በስሜ ስለሰየማችሁልኝ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው" የሚል ደብዳቤ ፅፎ ላከው።














