ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያ ነፃ የኮቪድ-19 ምርመራ መስጠት መጀመሯን አስታወቀች

በሚሊኒየም ሆስፒታል ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ነፃ ምርመራ ማድረግ እንደሚችሉ የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ በሚገኙ በተመረጡ 34 የጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ከክፍያ ነፃ ናሙና በመስጠትም ምርመራ ማድረግ ይችላሉም ተብሏል።

የጤና ማዕከላቱንም ዝርዝር የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው አውጥተዋል።

ነፃ የኮቪድ-19 ምርመራ ይሰጥባቸዋል ተብለው ከተጠቀሱትም መካከል ሚኒልክ ሆስፒታል፣ አቤት ሆስፒታል፣እንጦጦ ፋና የጤና ማዕከል፣ ህዳሴ የጤና ማዕከል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ የካቲት 12 ሆስፒታል፣የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይገኙበታል።

ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የጤና ማዕከላት የነፃ ምርመራን በተመለከተ የተባለ ነገር የለም።

በአዲስ አበባ በሚገኙ የጤና ማዕከላት ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ 1 ሺህ 250 ብር ክፍያ የሚጠየቅ ሲሆን፤ አንዳንድ የጤና ተቋማትም 1 ሺህ 500 ብር ያስከፍላሉ።

አገሪቷ ከዚህ ቀደም የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚያሳዩና፣ከህመምተኞች ጋር ንክኪ ያላቸውን ብቻ ነበር በነፃ የምትመረምረው።

በአሁኑ ወቅት አገሪቷ አስገዳጅ አድርጋው የነበረው የጭምብል ማጥለቅ መመሪያ ላላ ብሏል።

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል፣ ሲዲሲ ባወጣው መረጃ መሰረት በአፍሪካ ከፍተኛ የህሙማን ቁጥር ከተመዘገባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ነው።

ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ወደ 1.7 ሚሊዮን የላብራቶሪ ምርመራ ያከናወነች ሲሆን፣ 114 ሺህ 834 ህሙማንንም መዝግባለች። ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 769 ዜጎቿንም በኮሮናቫይረስ እንዳጣች የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ በዛሬው ዕለት እንደተናገሩት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌንየም ሜዲካል ኮሌጅ ሲኒየር አንስቴቲስት የሆኑት አቶ ገብረሥላሴ አባዲ በኮቪድ-19 መሞታቸውንም ገልፀዋል።