እግር ኳስ፡ ኒኮላስ አኔልካ ብዙዎች ያልተረዱት ነበር?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ ኔትፍሊክስ ላይ በአንድ ወቅት ኮከብ በነበረው እግር ኳስ ተጫዋች አኔልካ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው "ሚስአንደርስቱድ" ወጥቷል።
የቅርብ ጓደኛውና ለአመታትም አብሮት የተጫወተው ቲየሪ ሄንሪ "ለኔ ብዙዎች ኒኮ ብለው በሚያስቡትና በኒኮ መካከል የሰማይና የምድር ያህል መራራቅ አለ" በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።
በእግር ኳስ የዝና ጣራ ላይ ደርሶ የነበረው ኒኮላስ አኔልካ ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል። የአውሮፓ ሻምፒዮንሺፕ፣ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚየር ሊግን ከሁለት ክለቦች ጋርና ኤፍ ኤ ዋንጫንም አራት ጊዜ አሸንፏል።
ሆኖም የእግር ኳስ ህይወቱ አልጋ ባልጋ አልነበረም፤ ከብሄራዊ ቡድን እንዲሁም ከዌስት ብሮም ክለብ ተባሯል።
በተደጋጋሚም በበርካታ ተቃውሞች፣ ማዕቀብና ሌሎች አወዛጋቢ ጉዳዮችም በተደጋጋሚ ስሙ ሲጠራ ነበር።
የ41 አመቱ አኔልካ ታሪኩን በራሱ አንደበት ለኔትፍሊክስ ተናግሯል። ወደኋላ ዘወር ብሎ ስኬቶቹንና አወዛጋቢ ስለተባሉ ጉዳዮችም ሆነ ቀጥተኛነቱ ምን ያህል እንዳስከፈለው ተናግሯል።
ሪያል ማድሪድን ጠላሁት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አኔልካ ገና በ17 አመቱ ነበር ለታላቁ ቡድን አርሴናል የፈረመው። ወቅቱም በጎርጎሳውያኑ 1997 ነበር። አርሰናል በ1997ና በ1998 የፕሪሚየር ሊግና የኤፍ ካፕ ዋንጫዎችን እንዲያሸንፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ወደ አርሰናል የመጣውም ድንቅ ችሎታውን በተረዱት አሰልጣኙ አርሴን ቬንገር አማካይነት ነበር።
ከቬንገርም ጋር ስላላቸው ግንኙነት "አርሴን ቬንገር ከኔ ጎን ነበር። ከጎንህ ሆኖ የሚደግፍህ ሰው እንዳለ ሲሰማህ ያለ የሌለህን ትሰጣለህ" ብሏል።
ነገር ግን በጎርጎሳውያኑ 1999 አኔልካ በ29.75 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ሪያል ማድሪድ ተዛወረ።
"ሪያል ማድሪድን ስቀላቀል ኮከብነት ምን ማለት እንደሆነ ተረዳሁ እናም ጠላሁት" ይላል።
ሪያል ማድሪግ እግሩ ከረገጠባት ወቅት ጀምሮ ምን ያህል ውጥረት እንደገጠመውም ፊልም ላይ ይታያል። ይኸም ከመልበሻ ክፍል ይጀምራል።
"ተቀምጬ እያለሁ አንድ ተጫዋች ይመጣና ቦታዬ ነው ብሎ ያስነሳኛል፣ ሌላ ቦታ ስቀይርም እንዲሁ ሌላኛው እንዲሁ እያሉ አስነሱኝ" ይላል።
አኔልካ ለአምስት ወራት ያህል አንድም ግብ አላስቆጠረም፤ የሆነ ወቅትም ላይ አልለማመድም ብሎም በመቃወምም አቁሞ ነበር
"እንደ ውሻ ነው የቆጠሩኝ" በማለት ምሬቱን አጋርቷል።
በአጠቃላይ ሪያል ማድሪድ ላይ የነበረውንም ወቅት "መስዋዕትነት መከፈል የሚገባቸው ጉዳዮች ነበሩ እሱን ደግሞ ገና ታዳጊ በመሆኔ አልተረዳሁትም" ብሏል።
ለሪቨርፑል ደጋፊዎች ማወቅ ያለባችሁ መቆየት እፈልግ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጎርጎሳውያኑ 2002 አኔልካ ሊቨርፑልን ተቀላቀለ። ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ጄራል ሁልየር ጋር ግቡቡነት ነበራቸው ተብሏል። "ለኔ ምርጥ ክለብ ነውም" ይላል።
ነገር ግን በመንፈቁ ማብቂያ ወቅት አሰልጣኙ አኔልካ በሊቨርፑል እንዲቀጥል አልፈለጉም።
አኔልካን ማኔጅ የሚያደርጉት ወንድሞቹ ሌላ ክለብም እየፈለጉ መሆናቸው አሰልጣኙን አላስደሰተም።
አኔልካ በዚህ ይፀፀታል።
"የሊቨርፑል ደጋፊዎች እኔ መቆየት እንዳልፈለግኩ ነው የተሰማቸው፤ ሁኔታው እንደዛ አይደለም። ያ ወቅት ለኔ አሳዛኝ ነው። ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን የምችልበት ክለብ ነበር" ብሏል።
ፀረ- ሴም አይደለሁም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምናልባት በአኔልካ የእግርኳሰኝነት ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ ያስከተለው በዌስት ብሮም ውስጥ የነበረው ቆይታ ነው።
ግብ ሲያስቆጥር ደስታውን ለማሳየት ቄኔሌ የተባለውን ምልክት ማሳየቱ ነበር ከፍተኛ ውግዘት ያደረሰበት።
ምልክቱን ፈረንሳያዊው ኮሜዲያን ዱዮዶን ምባላ ሲጠቀምበት ይታያል። ይህ ግለሰብ በፀረ ሴማዊነቱ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡም ፌስቡክ አግዶታል።
ይህንንም ተከትሎ አኔልካ አምስት ጨዋታዎች ታገደ፤ 80 ሺህ ፓውንድም ተቀጣ።
በወቅቱ የሰላምታ ምልክቱ ፀረ ሴማዊነት አይደለም በሚልም ተከራክሯል። አኔልካ ፀረ ስርዓት ነውም ብሏል።
በፊልሙም ላይ አኔልካ ከክለቡ ስራ አስኪያጅ ስቲቭ ክላርክ ጋር ለነበራቸው ፀብና አተካሮ ምላሽ ነው ብሏል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ አኔልካን ተቀያሪ በማድረጋቸውም አኔልካ ማዋራት አቆመ። ዌስት ብሮም ኮከብ ተጫዋቹ አኔልካ በሌለበት አምስት ጨዋታዎችን ተሸነፈ።
አሰልጣኙም ተባረረ። አኔልካም በመጀመሪያው ጨዋታ ጎል አስቆጠረ።
"ቡድኔ ጋር ተመልሸ በመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ጎል አስቆጠርኩ። እናም ደስታዬን ገለፅኩ" የሚለው አኔልካ "ብዙዎች ከስቲክ ክላርክ ጋር የነበረኝን እሰጣገባ አያውቁም። ቄኔሌውም ለሱ ነው።"
"ለኔ ፀረ ሴማዊነት አይደለም እናም በጣም ነው ያስደነቀኝ፤ ጎል ካስቆጠርኩ በኋላ ለምን ሴማዊነትን ስለመጥላት ለምን አስባለሁ?"
የሬይሞንድ ዶሜኔችን እናት አልሰደብኩም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ውዝግብ የማያጣው አኔልካ በ2010 የአለም ዋንጫም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚዲያ ቀልብን ስቦ ነበር።
ከአሰልጣኙ ሬይሞንድ ዶሜኔች ጋር በመጋጨቱም የፈረንሳይ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አኔልካ እንዲባረር ወሰነ።
ቡድኑ ግን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም ይህንንም ውሳኔ በመቃወም ስልጠና ላይ አንገኝም አሉ።
ሁኔታው በጣም ተጋግሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚም ጣልቃ ገብተው ነበር።
አኔልካ አተካሯቸውን ባይክድም የፈረንሳዩ ጋዜጣ ለኢኩፕ ፊት ገፁ ላይ ይዞት የወጣውንና የአሰልጣኙን እናት መሳደቡን በጥቅስ አድርጎ መፃፉን በጭራሽ ሲል ክዷል።
"የሚያዉቁኝ ብዙዎች በጋዜጣው ላይ የተጠቀሰውን ብዬ ከሆነ መቼም ቢሆን እንደማልክድና ሁሉን ነገር ፊት ለፊት እንደምጋፈጥ ያውቃሉ። እናቱንም አልሰደብኩም" ብሏል።
ብዙዎች ያልተረዱት? ፊልሙ እንደሚያሳየው አኔልካ ዝምተኛ፣ ቀጥተኛ ብዙ ነገሮችን በራሱ ይይዝና ከቁጥጥር ውጭ ሲሆኑ ምላሽ ይሰጣል። ብዙዎች ያልተረዱት ይሆን? ተመልካቾች የራሳቸውን ምላሽ ይስጡ።












