ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ፡ የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃቱ 75ኛ ዓመት ሲታወስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 3 ዓለም በአሰቃቂነቱ የሚያወሳው የጃፓኖቹ ሂሮሺማና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የአሜሪካ የአውቶሚክ ቦምቦች የዘነቡበት፣ የሰው ልጅ እንደ ቅጠል የረገፈበት 75ኛ ዓመት ነው።
በእነዚህ የቦምብ ጥቃቶች ምን ያህል ሰዎች እንዳለቁ ትክክለኛ ቁጥር ባይኖርም ከሂሮሺማ 350 ሺህ ሕዝብ ውስጥ 140 ሺህዎቹ ሞተዋል። በናጋሳኪም እንዲሁ 74 ሺህዎች ተፈጅተዋል።
በአውቶሚክ ቦምቡ ጥቃቱ ምክንያት ጃፓን በ1937 እጅ ሰጥታለች። እንዲሁም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ክፍል የሆነውና በእስያ የነበረውን ጦርነት ማብቂያን ያበሰረ ነው ቢሉም አንዳንዶች በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።
ጃፓን እጅ ለመስጠት ዳር ዳር እያለች የነበረች ከመሆኑ አንፃር ሽንፈቷን ከአውቶሚክ ቦምብ ጥቃቱ ጋር ማያያዝ ትርጉም አልባ ነው ይላሉ።
ማን ያውራ የነበረ? ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ ከዚህ እልቂት የተረፉት ስለማይሽር ጠባሳቸውና ህመማቸው ይናገራሉ።
የእልቂቱ ተራፊዎችም በጃፓናውያን ዘንድ ስም ተሰጥቷቸዋል፤ 'ሂባኩሻ' ይባላሉ።
ተራፊዎቹም ከሞቱት በላይ ሆኑ እንጂ ያጋጠማቸው ችግርና ስቃይ እንዲሁ ዝም ብሎ በቃላት የሚነገር አይደለም።
በጨረር በመመረዛቸው ለዘመናት የሚወልዷቸው ልጆች የአካል ጉዳት ያለባቸው እንዲሆኑ እንዲሁም ለሥነ ልቦና ጉዳት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።
የእንግሊዟ ፎቶ ጋዜጠኛ ሊ ካረን ስቶው የእልቂቱን የተረፈውን በፎቶ አስቀርታለች፤ እንዲሁም ትናንት የተፈጠረ በሚመስል ሁኔታ ከ75 ዓመታት በፊት የተፈጠረውንም ስቃይ ከሦስት ሴቶች አንደበት ሰምታለች።

የፎቶው ባለመብት, Lee Karen Stow
ቴሩኮ ኡኖ
ዕለቱ ሐምሌ 30/1937 ዓ.ም ነበር፤ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በሂሮሺማ ላይ የአውቶሚክ ቦምብ የጣሉት።
በህይወት የተረፉት ቴሩኮ የ15 አመት ታዳጊ ነበሩ።
በጥቃቱ ወቅት ቴሩኮ የሁለተኛ ዓመት የነርስ ተማሪ ነበሩ። ትምህርታቸውንም ይከታተሉ የነበረው ሂሮሺማ ሬድ ክሮስ በሚባል ሆስፒታል ውስጥ ነበር።
በጥቃቱም የተማሪዎቹ ማደሪያ በእሳት ጋየ፤ ቴሪኮ እሳቱን ለማጥፋት ቢታገሉም የበርካታ ተማሪዎች ህይወት በእሳት አደጋው ተቀጠፈ።
አንዳንድ ነገሮች እንደ ሩቅ ህልም ትዝ ቢሏቸውም፤ በዚያ ሳምንት በእሳት የተቃጠሉ ሰዎችንና አሰቃቂ አደጋዎችን በህይወት እያሉ አይረረሷቸውም። በሞትም ቢሆን የሚከተላቸው ይመስላቸዋል።
እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ነርሶች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ህይወት ለማትረፍ ቀን ከሌት እየለፉ ነበር። ምግብም ውሃም ለሁሉም በቂም አልነበረም።
ቴሩኮ ተመርቀውም በዚያው ሆስፒታል ሥራቸውን ቀጠሉ። በቃጠሎው ወቅት በሚደርስ አደጋ የሰውነት ቆዳቸው ለተለበለበ ግለሰቦች የሚደረገውን የቀዶ ህክምና ድጋፍም ማድረግ ጀመሩ።

የፎቶው ባለመብት, Lee Karen Stow
በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ህይወት ትቀጥላለችና ቴሩኮ ከአውቶሚክ ቦምም ፍንዳታ የተረፈውን ታትሱዩኪም ጋር በትዳር ተጣመሩ።
የመጀመሪያ ልጃቸውንም ፀነሱ፤ አይናቸውን በአይናቸው ለማት ቢጓጉም ልጃቸው በጤና ትወለድ ይሆን? የሚለውም ሌላ ጭንቀት ነበር። በህይወትስ ትኖራለች? የሚለውም አሳሳቢ ሆነ።
ልጃቸው ቶሞኮም ተወለደች፤ ለቴሩኮም ተስፋን ፈነጠቀችላቸው፤ ለቤተሰቡም የአዲስ ህይወት መመስረትን አበሰረች።
"ሲዖልን ባላየውም በህይወታችን ያሳለፍነው ስቃይ ግን ሲዖል ተብሎ ሲነገር እንደሰማሁት ነው። መቼም ቢሆን ሊደገም የማይገባ ሰቆቃ ነው" ይላሉ ቴሩኮ።
"የኒውክሊየር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ አንዳንድ ሰዎች ጥረት ቢያደርጉም የመጀመሪያ ደረጃ ቁርጠኝነት የሚያስፈልገው ከመንግሥታት ነው። እነሱ ይህ ሊወገድ ይገባል ማለት አለባቸው" የሚሉት ቴሬኮ "የዓለም መንግሥታት ሁሉ በአንድነት የኒውክሊየር መሳሪያዎችን በመቃወም ትብብራቸውን ሊያሳዩ ይገባል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Lee Karen Stow

"ለሰባ አምስት ዓመታት ያህልም ዛፍ፣ ሳርም አይበቅልም የተባለባት ሂሮሺማ በአሁኑ ጊዜ አረንጓዴ ሆናለች። የከተማዋ ወንዞች ከእጸዋቱ ጋር ውብ አድርገዋታል" ትላለች የቴሩኮ ልጅ ቶሞኮ።
ምንም እንኳን ከተማዋ ተመልሳ ውበቷን ብትጎናፀፍም "ሂባኩሻ" [ከቦምቡ ጥቃት የተረፉት] በጨረሩ መርዛማነት እየተሰቃዩ ነው።
ሰቆቃቸውም ለልጅ ልጅ ተርፏል።
"የሂሮሺማና ናጋሳኪ ቦምብ ጥቃት ትዝታዎች ከአዕምሯችን ቢደበዝዝም አሁንም መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን።"
"የወደፊቱ ዕጣ ፈንታችን በእጃችን ነው። ሰላም እውን የሚሆነው እሳቤያችንን ሰፋ ስናደርገው ነው። ለሌሎች ማሰብ ስንጀምር፤ እሱንም እውን ለማድረግ የሚጠበቅብንን ስንተገብር ነው። ሰላምን ለመገንባት የማያሰልስ ጥረት ያስፈልጋል" በማለት የቴሩኮ የልጅ ልጅ ኩኒኮም ታስረዳለች።
"የአውቶሚክ ቦምቡ ገፈት ቀማሽ አይደለሁም፤ ሂሮሺማን የማውቃት እንደገና ከተገነባች በኋላ ነው። ግን ምን አይነት ዘግናኝና አሰቃቂ እልቂት እንደነበር መገመት እችላለሁ" ትላለች።
ከእልቂቱ የተረፉትን ታዳምጣለች። በዚያች ቀን ከተማዋ እንዴት እንደጋየች፣ ሰዎች፣ ወፎች፣ ዛፍ፣ ሳርና ቅጠሉ ሳይቀር እንደተቃጠለም ነግረዋታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፤ ለእርዳታ የመጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሞተዋል። ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመድ፣ ጓደኛ ፍለጋ ከሌላ ከተሞች የመጡ እንዲሁ አልቀዋል። የተረፉትም ለማይድን ህመም ተጋልጠዋል።
ኩኒኮ ከሂሮሺማና ናጋሳኪ የተረፉትን ብቻ ሳይሆን በዩራኒየም ማዕድን ቁፋሮ የሚሰሩ፣ በማዕድን ማበልፀጊያ አካባቢ የሚኖሩ፣ የኒውክሊየር መሳሪያዎችን የሚሞክሩና፣ በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰቃዩ ሰዎችም ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ከመሆኑ አንፃር ከእነሱም ጋር ያላት ግንኙነት ጠበቅ ያለ ነው።
ኤሚኮ ኦካዳ

የፎቶው ባለመብት, Yuki Tominaga
በሂሮሺማ ላይ የአውቶሚክ ቦምብ ሲጣል ኤሚኮ የስምንት ዓመት ልጅ ነበሩ።
በፍንዳታውም ታላቅ እህታቸው ሚየኮን ጨምሮ አራት የቤተሰባቸው አባላት ተገድለዋል።
እህታቸው ኤሚኮንም ሆነ ሌሎች ቤተሰባቸውን ፎቶ ዘመድ ቤት ሲያዩ ያ ጨለማ ጊዜ ድቅን ይልባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Emiko Okada

የዚያችን ዕለት እህታቸው በጠዋት ተነስታ "በኋላ እንገናኝ" ብላ እየፈነደቀች ወጣች። "ገና አስራ ሁለት ዓመቷ ነበር። ፈገግታ የማይለያት፤ ህይወትን በተስፋ የምታይ ልጅ ነበረች" ይላሉ ኤሚኮ።
ነገር ግን ከወጣችበት አልተመለሰችም፤ የት እንደደረሰችም አልታወቀም።
ቤተሰቦቿም ለዓመታትም ተስፋ ሳይቆርጡ እናገኛታልን ብለው ካሰቡበት ቦታ ሁሉ ፈለጓት። አስከሬኗንም አላገኙ።
እናም በህይወት ትኖራለች በማለትም በተስፋ መኖር ጀመሩ።
በወቅቱም የኤሚኮ እናት ነፍሰ ጡር ነበሩ፤ ነገር ግን ትንሽ ቆይቶ በሚያሳዝን ሁኔታ ፅንሱ ጨነገፈ።
"በቤታችን የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም። ስለ ጨረሩ የምናውቀው ነገርም ስላልነበረ ተመረዘ አልተመረዘ ያገኘነውን ዕቃም ሆነ ምግብ መሰብሰብ ጀመርን" ይላሉ።
በእነዚያ ተስፋ አስቆራጭ ቀናትም ሰዎች የሚበሉት ሲያጡ ምግብም ይሰርቁ ነበር፤ "ውሃማ ብርቅ ነበር" ይላሉ።
ያ አስቸጋሪ ጊዜ አሁን ተረስቷል።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Emiko Okada

ከትንሽ ጊዜያት በኋላ አስደንጋጭ ነገር መከሰት ጀመረ። የኤሚኮ ፀጉራቸው ይረግፍ ጀመ፣ ድዳቸው ያለማቋረጥ ይደማል እንዲሁም ያለ ምክንያትም መድከም አመጡ።
"በወቅቱ በጨረር መመረዝ ምን እንደሆነ አናውቅም ነበር። ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ ነው የደም ህዋሳቶቼ በትክክል ማመንጨት እንደማይችሉ የተነገረኝ" ይላሉ።
በሂሮሺማ በየዓመቱ ጥቂት ቀናት ፀሐይዋ ስትጠልቅ ደማቅ ቀይ ቀለም ሰማይ ላይ ይታያል። ከመድመቋ የተነሳ የሰዎችም ፊት ወደቀይነት ይቀየራል። ይህም ሁኔታ አስደሳች ቢመስልም ለእሳቸው ግን ወደኋላ ይወስዳቸውና፤ ከተማዋ የተቃጠለችበት ሁኔታ ድቅን ይልባቸዋል።
"ለሦስት ቀናት ያህል ከተማዋ ስትቃጠል ነበር፤ ለዚያም ነው ያንን የሚያስታውሰኝን ሁሉ የምጠላው። ፀሐይዋ ስትጠልቅ ማየት አልፈልግም፤ በከፍተኛ ሁኔታ ነው የምጠላው" ይላሉ።
ከቦምቡ ጥቃት የተረፉት በርካቶች ታሪካቸውንም ሳይነግሩ፤ እንደተማረሩ ህይወታቸው አልፏል።
"እነሱ መናገር ባይችሉም እኔ የነበረውን እናገራለሁ" ይላሉ።
"በርካቶች ዓለም ሰላም እንድትሆን ምኞታቸውን ይናገራሉ። ለእኔ ግን የሚቀድመው ድርጊት ነው። የዓለም ሕዝቦች ማድረግ የምንችለውን መፈፀም አለብን።"
"እኔም ብሆን ለልጆቼና ለልጅ ልጆቼ የተሻለ ህይወት እንዲመሩ፤ በደስታ እንዲኖሩ የምችለውን ማድረግ አለብኝ።"

የፎቶው ባለመብት, Lee Karen Stow
ሬይኮ ሃዳ
የትውልድ ቀያቸው ናጋሳኪን አውቶሚክ ቦምቡ እንዳልነበረ ሲያፈራርሳት ሬይኮ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ነበሩ። ዕለቱ ነሐሴ 3/1937 ከረፋዱ አምስት ሰዓት ገደማ ነበር።
ያስታውሳሉ ዕለቱ ሐሙስ ነበር። በጠዋትም በአየር ጥቃት ዙሪያ አንዳንድ ማስጠንቀቂያዎች ይተላለፉ ስለነበር ሬይኮም ቤታቸው እድብ ብለው ተቀመጡ።
ማስጠንቀቂያው ሲቆምም አካባቢያቸው ወደሚገኝ ምኩራብ አመሩ። የአየር ጥቃት ይደርሳል የሚሉ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ በመነገሩ ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ አቁመው ነበር።
ጊዜያቸውንም በምኩራብ ውስጥ በማጥናት ያሳልፉ ነበር።
ሬይኮ ወደ ምኩራቡ ከደረሱ ከአርባ ደቂቃ በኋላ መምህራቸው አሰናበቷቸው፤ ሬይኮም ወደቤታቸው አቀኑ።
ቤት ሊገቡ ሲሉ "ደረጃውን ወጥቻለሁ መሰለኝ። ድንገት የሆነ ድብልቅልቅ ያለ ነገር ተፈጠረ። በቃላት መግለፅ የማይቻል የብርሃኑ ድምቀት አይንን የሚያጥበረብር ቀለማት ማየት ጀመርን። ቢጫ፣ ብርቱካናማ፣ . . . ሁሉም ተደባልቆ እንደ ህልም አየን።"
"ምን እንደሆነ እንኳን ለማሰብ ጊዜ ሳላገኝ ሁሉ ነገር ነጭ ሆነ።"
"ከዚያም ብቻዬን የቀረሁ መሰለኝ። ከዚያም ከፍተኛ ድምፅ አምባረቀ፤ ሁሉ ነገር ፀጥ ረጭ አለ። እኔም አቅሌን ስቼ ወደቅኩ።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚያም ድንገት ሲነቁ መምህራቸው ያላቸው ነገር ትዝ አላቸው። በአየር ጥቃት ወቅት ወደተዘጋጁት ድንገተኛ መሸሸያ ቦታዎች ማምራት። እናታቸውን ቤት ውስጥ አገኟቸውና ተያይዘውም በአቅራቢያቸውም ወዳለ መጠለያ አመሩ።
"ምንም መቧጨር እንኳን አልደረሰብኝም። የኮንፒራ ተራራ አድኖኛል። በተራራው ሌላ ክፍል የሚኖሩት ግን እንደኛ እድለኛ አልነበሩም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ደርሶባቸዋል።"
በርካቶችም ተሰደው ወደእነሱ አካባቢ መጡ። ሁኔታቸው የሚዘገንን ነበር። "አይናቸው የተጎለጎለ፣ ፀጉራቸው የተቃጠለ፤ እርቃናቸውንና ብዙዎቹም ሰውነታቸው ተቃጥሎ ቆዳቸው ተንጠልጥሎ ነበር" በማለት ያስታውሳሉ።
እናታቸውን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ እናቶች ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች አቅራቢያቸው ወደሚገኘው የንግድ ኮሌጅ አዳራሽ ወሰዷቸው። እዚያም አረፍ እንዲሉ አደረጓቸው።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Reiko Hada
"ውሃ ጠማን ይላሉ። ውሃም እንዳመጣም ታዘዝኩ። የተሰባበረ ባሊ አገኘሁና ቅርብ ወዳለ ወንዝ ሄጄ ቀድቼ መጣሁ።"
"ውሃውን እንደጠጡትም ብዙዎቹ ሞቱ። . . . አንድ በአንድ ሞቱ።"
"ወቅቱ ሞቃታማ ነበር ። አስከሬናቸው እተበላሸ ጠረን በማምጣቱ እንዲቃጠል ተደረገ። አስከሬናቸው በኮሌጁ መዋኛ ገንዳ ተከምሮ ነበር። እንጨትም ተሰብስቦ ነደደና ተቃጠ፤ አመድም ሆኑ።"
"እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ማወቅ ይከብዳል። እንደ ሰው ልጆች በክብር አልሞቱም።"
"የወደፊቱ ትውልድ መቼም ቢሆን እኛ ባለፍንበት መንገድ ማለፍ የለበትም። መቼም ቢሆን፤ በጭራሽ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መፍቀድ የለብንም።"
"ሰላምን የሚፈጥሩት ሰዎች ናቸው። ምንም እንኳን በተለያዩ አገራት ብንኖርም፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን ብንናገርም ሰላም እንዲሰፍን ያለን ምኞት ተመሳሳይ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Lee Karen Stow












