ፍትህ፡ የአቶ ልደቱ አያሌውና ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የፍርድ ቤት ውሎ

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፖለቲካኛው አቶ ልደቱ አያሌው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተሰማው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነበር።
አቶ ልደቱን ፖሊስ የያዛቸው በቅርቡ በቢሾፍቱ ከተማ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው ነው።
በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የአዴፓ አባሉ አቶ ልደቱ አያሌው ተጨማሪ የ7 ቀናት ቀጠሮ እንደተሰጣቸው የፓርቲው ፕሬዝደንት አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ፍርድ ቤቱ ፖሊሶች የደረሰቡትን መረጃ ጠይቆ ፖሊሶች ከ14 ቀናት ጊዜ በኋላ ከቃል አቤቱታ ውጭ ማቅረብ አልቻንም ተጨማሪ 14 ቀናት ይሰጠን ብለው ጠይቀዋል። ይህን የተመለከተው ፍርድ ቤት ለመጨረሻ ጊዜ የ7 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ሰጥቷል።"
የአቶ ልደቱ አያሌውን የጤና ሁኔታ በተመለከተ የፓርቲው ሊቀ-መንበር ይህን ብለዋል።
"አቶ ልደቱ የልብ ህመምተኛ እንደሆኑና የሕክምና ሰርቲፌኬት እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተው እስካሁን ግን ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ የወሰነው ውሳኔ ተፈፃሚ አለመሆኑን ገልፀው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በጠየቁት መሠረት ፍርደ ቤቱ በአቅራቢያው ከሚገኘው ሆስፒታል ለሚቀጥለው ቀጠሮ የሕክምና ማስረጃ ይዘው እንዲቀርቡ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል።"
አቶ ልደቱ አያሌው ነሐሴ 11/2012 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አቶ ልደቱ ነዋሪነታቸው ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ ስልካቸው ላይ በመደወል እንደሚፈለጉ በመግለፁ፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ቢሮ በመሄድ እዚያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ፌደራል ፖሊስም ለሚፈልጋቸው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ እንዳስረከባቸው አይዘነጋም።
አቶ ልደቱ የኢዴፓ መስራችና አባል አመራር ሆነው ለረጅም ዓመታት የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ የብሔራዊ ምክር ቤት አባልና አብሮነት በሚባለው የፓርቲዎች ጥምረት ውስጥ የኢዴፓ አስተባባሪ ተወካይ ናቸው።
ይልቃል ጌትነት [ኢንጂነር]
በሌላ በኩል ይልቃል ጌትነት [ኢንጂነር] ትላንት [ሰኞ] ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የ9 ቀናት ጊዜ መፍቀዱን ጠበቃቸው አዲሱ ጌታነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ፖሊስ ድጋሚ ተጨማሪ 14 ቀናት ጠየቀ። አቶ ይልቃል ከታሰሩ ከሰኔ 25 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለው ሲቆጠር 40 ቀናት ናቸው። እነዚህ 40 ቀናት ከተጠየቁትና እስካሁን ከተሰራው ሥራ አንፃር በጣም ረጅም ናቸው ብለን ከዚህ በላይ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ ገልፀን ተከራክረናል።"
ጠበቃው አክለው አሁን ፍርድ ቤቱ የፈቀደው የምርመራ ጊዜ የመጨረሻው ነው ብለዋል።
"ፍርድ ቤቱም ክርክሩን ከሰማ በኋላ የተጠየቀው ጊዜ አስፈላጊ እንደሆነ አምኛለሁ፤ ሆንም ግን አሁን ለምርመራ የምንሰጠው ጊዜ የመጨረሻ ነው በማለት 14 ቀናት የተጠየቀውን ጊዜ ወደ 9 ዝቅ አድርጎ ለነሃሴ 14/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።"
ይልቃል ጌትነት [ኢንጂነር] በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከሰኔ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በሞቱ ሰዎችና በወደመ የመንግሥትና የግል ንብረት ጉዳይ እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው ነው።












