የሐሰት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ውጤት የሚያሳየው የኮቪድ-19 ክትባት ውድቅ ሆነ

የሐሰት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ውጤት የሚያሳየው የኮቪድ-19 ክትባት ውድቅ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, UNIVERSITY OF OXFORD

ብዙ ተስፋ ተጥሎበት አውስትራሊያ ውስጥ ሙከራ እየተደረገለት የነበረው የኮሮናቫይረስ ክትባት ተሳታፊዎች ላይ የሐሰት የኤችአይቪ ውጤት በማሳየቱ ውድቅ ተደርጓል።

አውስትራሊያ ከዚህ ተስፋ ከተጣለበት ክትባት 51 ሚሊዮን ብልቃጦች ለመግዛት አቅዳ ነበር።

አውስትራሊያ በምትኩ እንደ አስትራዜኔካ ያሉ ውጤታማ ክትባቶችን ለመግዛት ቅድመ ትዕዛዝ አስቀምጣለች።

ሲኤስኤል እና የአውስትራሊያው ኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያበለፀጉትን ክትባት የወሰዱ ሰዎች ደም ሲመረመር ኤችአይቪ ፖዘቲቭ የሚል ውጤት ያሳያል።

ነገር ግን ተሳታፊዎቹ የኤችአይቪ ምርመራ ሲደርግላቸው ደማቸው ንፁህ ሆኖ ተገኝቷል።

የሙከራ ደረጃ ላይ የነበረው ክትባት በሽታ ተከላካይ ህዋሳትን በማመንጨት ረገድ ውጤታማ ተብሎ ነበር።

ነገር ግን ክትባቱ ከኮሮናቫይረስ ባለፈ በአንዳንድ ተሳታፊዎች ላይ ኤችአይቪ ቫይረስን የሚከላከሉ ሴሎች አምርቷል። ይህ ማለት ደግሞ ተሳታፊዎቹ የሐሰት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ውጤት ይታይባቸዋል ማለት ነው።

ነገር ግን በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ አልተገኘም።

ክትባቱን ሲያመርቱ የነበሩ ተመራማሪዎች ስህተቱን ለማረም ቢያንስ አንድ ዓመት ይፈጃል ማለታቸውን ተከትሎ ምርምሩ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል።

ፕሮጀክቱን በጣምራ ከሚመሩት ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ የሆኑት ፖል ያንግ ውሳኔው እጅግ 'ልብ ሰባሪ' ነው፤ ምክንያቱ ለ11 ወራት ምርምር ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል።

አውስትራሊያ ኮሮናቫይረስ በሕብረተሰቡ ዘንድ እንዳይሰራጭ ለማድረግ በሠራችው ሥራ ተመስግናለች።

የሃገሪቱ የጤና ሙያተኞች ምንም እንኳ ሃገሪቱ ወረርሽኙን እየተቆጣጠረች ቢሆንም በሚቀጥለው ዓመት በሚደርሱ ሁለት ክትባቶች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይቻላል ይላሉ።

የአውስትራሊያ መንግሥት ምናልባት በሃገር ውስጥ የሚመረቱ ክትባቶች ባይሳኩ በሚል ዝግጅት እንዳደረገ ተናግሯል።

ለዚህም ዝግጅት እንዲሆን ከተለያዩ ክትባት አምራች ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መድረሱን መንግሥት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን "ሕዝባችንን ሙሉ በሙሉ ለማስከተብ ከያዝነው የጊዜ ገደብ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ልናስከትብ እንችላለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

አውስትራሊያ ካዘዘችው መካከል አንዱ የሆነው በኦክስፎርድና አስታራዜኔካ ጥምረት የሚመረተው ክትባት ውጤታማነቱ ቢረጋገጥም ከፈቃድ ሰጪዎች ይሁንታ እየተጠባበቀ ይገኛል።

አውስትራሊያዊያን በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ክትባት ማግኘት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

25 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አውስትራሊያ ባለፈው ሳምንት አንድ ሰው ብቻ በቫይረሱ ተይዞብኛል ብላለች።

የኮሮናቫይረስ በዓለም ዙሪያ መሰራጨት ከጀመረ ወዲህ በሃሪቱ 28 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ሲረጋገጥ 908 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

ይህ ቁጥር ከሌሎች አደጉ ከሚባሉ ሃገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ያነሰ ነው።