ኮቪድ-19 ፡ ስለ ክትባቱ እየተሰራጩ የሚገኙ አራት ሐሰተኛ ወሬዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተስፋ ሰጪ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች መገኘታቸው ዓለምን ቢያስደስትም ስለ ክትባቶች የሚሰራጩ አሉባልታዎች መሰናክል መሆናቸው ግን አልቀረም።
ቢቢሲ ክትባቶችን በተመለከተ እየተሰራጩ ያሉ አራት ሐሰተኛ ወሬዎችን ለይቷል።
‘ክትባቱ የዘረ መል መዋቅር ያዛባል’
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ክትባቱ የሰዎችን ዘረ መል መዋቅር እንደሚያቃውስ ተነግሯል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ገለልተኛ ሳይንቲስቶች ግን ይህ ሐሰት ነው ብለዋል።
ፋይዘርና ባዮቴክ የሠሩትን ክትባት ጨምሮ ብዙ ክትባቶች የተዘጋጁት ከቫይረሱ የዘረ መል ቅንጣት በመውሰድ ነው።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው ፕ/ር ጀፍሪ አልመንድ ክትባቶቹ የሰዎች ዘረ መል ላይ ምንም አይነት ጉዳት አያስከትሉም ይላሉ።
ክትባት የሰው ሰውነት ቫይረሱ የተሸፈነበትን ፕሮቲን እንዲያመነጭ በማነቃቃት በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳብራል።
የኮሮናቫይረስ ክትባት የዘረ መል መዋቅር ያዛባል የሚለው አሉባልታ መሰራጨት የጀመረው ከግንቦት ወዲህ ነው።
አርኤንኤ የሚባለው የክትባት ሂደት ከዚህ ቀደም እንዳልተሞከረ ያጣቅሳል።
በእርግጥ አርኤንኤ የተባለው ሂደት ከዚህ ቀደም ፍቃድ ባያገኝም፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰዎች ላይ ተሞክሯል።
ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የክትባት ሙከራ ተደርጓል።
አስተማማኝነቱ የሚረጋገጠው ከጥብቅ ፍተሻ በኋላ ነው።
በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሙከራ ክትባቶች በጥቂት በጎ ፍቃደኛ ሰዎች ላይ ይሞከራሉ። ሂደቱ ስለክትባቱ አስተማማኝነት እና በምን ያህል መጠን መሰጠት እንደሚገባው መረጃ ይሰጣል።
በሦስተኛው የሙከራ ደረጃ ክትባቱ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማነቱ ይፈተሻል። የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትል እንደሆነም ሙከራው ጠቋሚ ነው።
‘ቢል ጌትስ ማይክሮቺፕ ሊቀብሩብን ነው’
የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰውነት የሚገባ የመረጃ መሣሪያ (ማይክሮቺፕ) ለመቅበር የተፈጠረ ሽፋን ነው የሚለው የሴራ ትንተና መሰራጨት ከጀመረ ሰነባብቷል።
ከዚህ አጀንዳ ጀርባ ያሉት የማይክሮሶፍት ፈጣሪው ቢልጌትስ እንደሆኑም በስፋት ሲወራ ነበር።
ሆኖም ግን ይህንን ወሬ የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ የለም። የቢል እና መሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የተወራው ነገር “ሐሰት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሚያዝያ ላይ ቢል ጌትስ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው “ከወረርሽኙ ያገገሙ ሰዎችን ለመለየት ዲጂታል የምስክር ወረቀት ይኖራል” ማለታቸውን ተከትሎ ነው ወሬው የተሰራጨው።
በእርግጥ በቃለ ምልልሱ ወቅት ስለ ማይክሮቺፕ ምንም አልተናገሩም።
የጌትስ ፋውንዴሽን ክትባት ሲሰጥ የሰዎችን የክትባት መረጃ የሚመዘግብ ስውር ቀለም ያለው ቴክኖሎጂን በገንዘብ ይደግፋል። ቴክኖሎጂው ገና ሥራ ላይ አልዋለም።
ይህ ቴክኖሎጂ የሰዎችን የግል መረጃ አያሾልክም። ሰዎችን በስውር ለመከታተል እንደማይውልም በጥናቱ የተሳተፉት ሳይንቲስት አና ጃክሊንስ ተናግረዋል።
አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ 28 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን ቢል ጌትስ በክትባት ሰበብ ማይክሮቺፕ ሊቀብሩ እንደወጠኑ ያምናሉ። ከነዚህ ሰዎች 44 በመቶው ሪፐብሊካን ናቸው።
‘ክትባቱ የጽንስ ህዋስ ይዟል’
ሌላኛው ሐሰተኛ ወሬ ክትባቱ የጽንስ ሳንባ ህዋስ አለበት የሚለው ነው።
የሳውዝሀምተን ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ማይክል ሄድ “በየትኛውም ክትባት ውስጥ የጽንስ ህዋስ የለም” ይላሉ።
ጸረ ክትባት መረጃ ከሚያሰራጩ የፌስቡክ ገጾች አንዱላይ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል ጥናት አጣቅሶ የአስትራዜኒካ እና የኦክስፎርድ ክትባት ይዘትን ይተነትናል።
ሆኖም ግን በቪድዮው የሚጠቀሰው ጥናት ያተኮረው ቤተ ሙከራ ውስጥ ክትባቱ በሰዎች ህዋስ ላይ ሲሞከርምን ውጤት እንደሚያሳይ ነው።
ክትባት ሲዘጋጅ በቤተ ሙከራ የተሠራ ህዋስ ጥቅምላይ መዋሉ ትክክለኛ የሂደቱ አካል ቢሆንም ቪድዮው ላይ የተገለጸበት መንገድ ግን ስህተት ነው።
የብሪስትል ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ዴቪድ ማቲውስ ክትባቶች በዚህ መንገድ እንደሚሠሩና ለሂደቱ ጽንስ እንዲወርድ ተደርጓል መባሉ ስህተት መሆኑን አስምረውበታል።
‘ሰው ከበሽታው የሚያገግም ከሆነ ክትባት አያስፈልግም’
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ አሉባልታዎች፤ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ የመሞት እድላቸው ጠባብ ከሆነክትባት ምን ይጠቅማል? ይላሉ።
ከበሽታው የማገገም እድል 99.97% ነው ሲሉም ይከራከራሉ። ስለዚህም ክትባት ከመውሰድ ይልቅ በኮቪድ-19 መያዝ እንደሚመረጥ ይጠቁማሉ።
በተቃራኒው ተመራማሪዎች እንደ ማስረጃ የተጠቀሰው አሐዝ ትክክል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ጄሰን ኢኬ፤ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች 99.0% ያህሉ የመትረፍ እድል አላቸው ይላሉ።
ይህ ማለት ደግሞ ከ10,000 ሰዎች 100 ያህሉ ይሞታሉማለት ነው።
ከሚሞቱ ሰዎች በተጨማሪ በቫይረሱ ተይዘው ከፍተኛ የጤና ቀውስ የሚገጥማቸው፣ ለዓመታት ጤናቸው ላይ ጠባሳ የሚያድርባቸውም ብዙ ናቸው።
በሌላ በኩል በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የጤና ዘርፉ እየደረሰበት ካለው ጫና በቀላሉ ለማገገም መቸገሩ አይቀርም። ይህ ማለት ደግሞ ሌላ ህመም ያለባቸው ሰዎች ተገቢውን እንክብካቤ ለማግኘት ይቸገራሉ ማለት ነው።
ፕ/ር ሊያም ስሚዝ፤ ክትባት በማኅበረሰብ ደረጃ ካልተወሰደ በግለሰቦች ብቻ ተወስኖ የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣም በማለት የክትባትን አስፈላጊነት ያስረግጣሉ።












