ኮሮናቫይረስ ፡ ሞዴርና የኮቪድ-19 ክትባትን ለማቅረብ ከአውሮፓና አሜሪካ ፈቃድ እየጠየቀ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞዴርና የተሰኘው የኮሮናቫይረስ ክትባት አምራች ድርጅት ከአውሮፓና አሜሪካ ፈቃድ ሰጪዎች ክትባቱን ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ ጠይቋል።
ፈቃድ ሰጪዎች ክትባቱን ያለፈበትን የሙከራ ሂደት ተመልክተው ክትባቱ ለተጠቃሚዎች መዋል አለበት ወይስ የለበትንም የሚለውን ይወስናሉ።
የቤተ ሙከራ ሂደቶች እንደሚያሳዩት ኤምአርኤንኤ የተሰኘው ክትባት 94 በመቶ ውጤታማና ሰዎች ከኮሮናቫይረስ የሚያድን ነው።
በሌላ በኩል ፋይዘር የተሰኘው ክትባት ለአሜሪካ መንግሥት ተቆጣጣሪዎች የይለፍልኝ ጥያቄ ጠይቋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ተቆጣጣሪዎችም ፋይዘር የተሰኘው ክትባት ለገበያ መዋል ይችላል ወይ የሚለውን በማጣራት ላይ ናቸው።
ከዚህም አልፎ አስትራዜኔካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እያመረቱት ያለው ክትባት ለተጠቃሚ መቅረብ ይችል እንደሁ ምርመራ እየተደረገለት ይገኛል።
ሞደርና ከዩናይት ኪንግደም መንግሥት ፈቃድ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጓል።
የሞዴርና ክትባት በ30 ሺህ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ተብሏል። በተለይ ክትባቱ ለኮሮናቫይረስ በጣም ተጎጂ ናቸው በተባሉ ከ60 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ ውጤታማ ሆኗል።
አሁን የፊት መስመሩን የያዙት ክትባቶች የራሳቸው የሆነ ጥቅምና የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው።
የአስትራዜኔካ ክትባት ዋጋው ከሌሎች ረከስ ያለ ነው።
አንድ ክትባት በአራት ዶላር [በዕለቱ ምንዛሪ 153 ብር ገደማ] ሲሆን የፋይዘር ደግሞ 20 ዶላር [765 ብር] በሌላ በኩል የሞዴርና 33 ዶላር ወይም 1262 ብር ተገምተዋል።
የአስትራዜኔካ ክትባት ብዙ ቅዝቃዜ ስለማይጠይቅ ከሌሎች በተለየ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር ቀላል ነው ተብሎለታል።
ነገር ግን ውጤታማነቱ ከ62 አስከ 90 በመቶ መሆኑ ከሌሎቹ ሁለት ክትባቶች አነስተኛ ያደርገዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ከሞዴርና ክትባት 7 ከሚሊዮን፤ ከፋይዘር 40 ሚሊዮን፤ ከአስትራዜኔካ 100 ሚሊዮን ክትባት ይድረሰኝ ስትል ቅደመ ትዕዛዝ አስቀምጣለች።
















