ኮሮናቫይረስ ፡ 95 በመቶ አስተማማኝ ነው የተባለ አዲስ የኮቪድ-19 ክትባት ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞዴርና የተባለ ድርጅት ከኮሮናቫይረስ 95 በመቶ የሚከላከል አዲስ ክትባት ማግኘቱን ይፋ አደረገ።
የዩናይትድ ስቴትስ መድኃኒት አምራች ኩባንያ የሆነው 'ሞዴርና' ያሰራጨው መረጃ ፋይዘር የተባለው ድርጅት ተመሳሳይ ይዘት ያለው መረጃ ካወጣ ከቀናት በኋላ ነው።
ሁለቱም ድርጅቶች የረቀቁ መንገዶችን ተጠቅመው ነው ክትባቶችን ያገኙት።
ሞዴርና የምርምር ውጤቱን ያደረገበትን ዕለት 'ታላቅ ቀን' በማለት ሐሴቱን የገለፀ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ክትባቱን ለመጠቀም ፈቃድ እንደሚያገኝ አስታውቋል።
ነገር ግን ድርጅቱ ያወጣው የመጀመሪያ ዙር ውጤት ስለሆነ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ እየተነገረ ነው።
የክትባቱ ሙከራ አሜሪካ ውስጥ ያሉ 30 ሺህ ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን ግማሾቹ በየአራት ሳምንቱ ክትባቱ ሲሰጣቸው ግማሾቹ ደግሞ ጥቅምና ጉዳት የሌለው መርፌ ተወግተዋል ውጤቱን ለመለየት ተሞክሯል።
ከዚህ ሙከራ በተገኘ ውጤት መሠረት 94.5 በመቶ ሰዎች በክትባቱ ምክንያት ለኮሮናቫይረስ ሳይጋለጡ ቀርተዋል ተብሏል።
ስለክትባቱ ውጤቱ የቀረበው ዘገባ ጨምሮም፤ ሙከራ ከተደረገባቸው መካከል 11 በኮቪድ-19 ክፉኛ የታመሙ ሰዎች የመከላከል አቅም አዳብረዋል ይላል።
የሞዴርና ዋና የሕክምና ኃላፊ ታል ዛክስ "በጠቅላላው የክትባቱ ውጤታማነት ድንቅ ነው. . . ታላቅ ቀን" ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስካሁን የማናውቀው
የክትባቱ ዘላቂነት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ እስካሁን አልታወቀም። ይህን ለማወቅ ተሳታፊዎች ላይ የሚደረገው ክትትል ይቀጥላል።
ክትባቱ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች የተሻለ መከላከል እንደሚሰጥ ቢጠቆምም ሙሉ መረጃ ግን ያሻል ተብሏል።
ዛክስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "እስካሁን ባለው መረጃ ክትባቱ በጊዜ ብዛት አቅሙን አያጣም።"
ሌላው የማይታወቀው ነገር ክትባቱ ሰዎች በጣም እንዳይታመሙ ከማድረግ ያግዳል ወይ የሚለውና ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳያስተላልፉስ ያደርጋል የሚለው ነው።
ደኅንነቱስ?
ክትባቱ እስካሁን በደኅንነት ጉዳይ ይህ ነው የሚባል ነገር አልተነሳበትም። ነገር ግን የትኛውም መድኃኒት 100 በመቶ እንከን አልባ ሊሆን አይችልም።
አንዳንድ ተሳታፊዎች ክትባቱ የወሰዱ ሰሞን መጠነኛ ድካም፣ ራስ ምታትና ሕመም እንደተሰማቸው አስታውቀዋል።
የሞዴርና እና የፋይዘር ክትባት ከ90 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆናቸው ተነግሯል።
ነገር ግን የሁለቱም ድርጅቶች ውጤት የመጨረሻ ደረጃ ላይ አልደረሰም። ውጤታማነቱም ሊቀየር ይችላል ተብሏል።
ቢሆንም የሞዴርና ክትባት ማቀዝቀዣ ውስጥ ለማስቀመጥ ከሌሎቹ ክትባቶች በተለየ ቀላል እንደሆነ ተነግሯል።
የሞዴርና ክትባት ማቀዝቀዣ ውስጥ እስከ አንድ ወር መቆየት ሲችል የፋይዘር ግን ለአምስት ቀናት ብቻ ነው የሚቆየው።
ሩስያ የለቀቀችው ስፑትኒክ 5 የተሰኘው ክትባትም 92 በመቶ የመከላከል አቅም እንደላው ተነግሯል።
መቼ ልናገኘው እንችላለን?
ይህ የሚወሰነው ባለንበት ቦታና በዕድሜያችን ነው ተብሏል።
ሞዴርና ክትባቱን ለአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ኃላፊዎች በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
20 ሚሊዮን ክትባቶች ለአሜሪካውያን ዝግጁ እንደሚያደርግም ድርጅቱ አስታውቋል።
ድርጅቱ በሌሎች አገራትም ፈቃድ ለማግኘት እየሞከረ እንዳለና በሚቀጥለው ዓመት 1 ቢሊዮን ክትባቶች አምርቶ ለማዘጋጀት ማቀዱን አስታውቋል።















