ኮሮናቫይረስ ፡ የኮቪድ-19 ክትባት መሰጠት ሲጀምር ዓለም ወደ መደበኛ ኑሮው ይመለሳል ተባለ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የኮሮናቫይረስ ክትባት ከፍተኛ አውንታዊ ውጤት ስለሚኖረው በበሽታው ተጽእኖ የተመሳቀለው የዓለም ሕዝብ ህይወትን ከወራት በኋላ ወደ መደበኛው መስመር እንዲመለስ ያደርጋል ተባለ።

ክትባቱን ካዳበሩት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ባዮኤንቴክ መስራች ከሆኑት አንዱ ፕሮፌሰር ኡጉር ሳሂን እንዳሉት፤ ክትባቱ የበሽታውን መስፋፋት በግማሽ እንደሚቀንሰው ተስፋ ከማድጋቸው በተጨማሪ፤ "በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል።"

ባለፈው ሳምንት ባዮኤንቴክ እና አብሮት የሚሰራው ፋይዘር የተባለው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ እንዳሉት፤ የመጀመሪያ ደረጃ የተደረገው ትንተና ክትባቱን ካገኙ ሰዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑትን ከበሽታው እንደሚከላከል አመልክቷል።

በሙከራው 43 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በክትባቱ ሙከራ ላይ መሳተፋቸውም ተገልጿል።

ፕሮፌሰር ሳሂን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከትባቱ ወረርሽኙ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ሁኔታውን እንደሚቀንሰውና በተከተቡት ላይ የበሽታው ምልክቶች እንዳይከሰት የማድረጉን ሁኔታ ለመረዳት ተጨማሪ ክትትል ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከአንድ ወር በኋላ 10 ሚሊዮን የሚደርስ የባዮኤንቴክ/ፋይዘር ክትባትን የያዙ ብልቃጦችን የምታገኝ ሲሆን፤ በተጨማሪም 30 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባትም አዛለች። በሦስት ሳምንት ልዩነት ሁለት ጊዜ የሚሰጠው ክትባት በስድስት አገራት ውስጥ ተሞክሯል።

በቀዳሚነት በአዛውንቶች መንከባከቢያዎች ውስጥ ያሉ በዕድሜ የገፉ ሰዎችና እንክብካቤ የሚሰጧቸው ሠራተኞች የሚያገኙ ሲሆን፤ በተከታይነትም የጤና ባለሙያዎችና ከ80 ዓመት በላይ የሚሆኑ ሰዎች ክትባቱን ያገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ ከዚያም ሌሎች እንደየዕድሜያቸው ክትባቱ ይሰጣቸዋል ተብለወል።

በዓለም የኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ነው የተባለው ይህ ክትባት ይፋ ከተደረገ በኋላ፤ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ታዋቂ የሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ሰር ጆን ቤል፤ ከወራት በኋላ ህይወት ወደ መደበኛ ፍሰቷ ትመለሳለች ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

"ምናልባትም ይህንን ያለ የመጀመሪያው ሰው ሳልሆን አልቀርም፤ ነገር ግን ይህንን የምለውም ባለኝ መተማመን ምክንያት ነው" ብለዋል።

ክትባቱን በማዘጋጀት ሂደት ሰፊ ተሳትፎ ያላቸው ፕሮፌሰር ሳሂን ግን ረዘም ያለ ጊዜ ሊያስፈልግ ይችላል ብለዋል።

ጨምረውም ሁሉም ነገር እንደታሰበው ከሄደ በሁለት ወራት ውስጥ ክትባቱ ለስርጭት ቀረወቦ አገልግሎት ላይ መዋል ይጀምራል።

በተያዘው ዕቅድ መሰረትም አስከ መጪው ሚያዝያ ድረስም ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ክትባት በዓለም ዙሪያ የሚሰራጭ ሲሆን "በዚህም ውጤት ማየት የሚጀመርበት ሁኔታ ይፈጠራል" ብለዋል።

በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመትም ከወራት በኋላም የክትባቱ ውጤት የሚታይበት ሲሆን ክትባቱም በስፋት ቀርቦ በርካታ ሰው ለመከተብ የሚቻል ይሆናል ተብሏል።