ኮሮናቫይረስ፡ 90 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ተሰራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮሮናቫይረስን በመከላከል 90 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ይፋ ሆነ።።
ይህ በሁለት ኩባንያዎች ይፋ የተደረገው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ክትባት 90 በመቶ ሰዎችን በኮቪድ-19 ከመያዝ ታድጓል ተብሏል፡፡
ክትባቱ ይፋ ያደረጉት ፋይዘር እና ባዮኤንቴክ ኩባንያዎች ግኝቱ ለሳይንስና ለሰው ልጅ ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
ኩባንያዎች በስድስት የተለያዩ ሃገራት 43 ሺህ 500 ሰዎች ላይ መሞከራቸውን የገለፁ ሲሆን አንድም ጊዜ አሳሳቢ የጤና ችግር አልታየም ብለዋል።
ፋይዘርና ባዮኤንቴክ ክትባቱን በፈረንጆቹ የህዳር ወር መጨረሻ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በቁጥር የበዙ ክትባቶች የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን ይህ ክትባት ተስፋ ከተጣለባቸው ውስጥ ቀዳሚው ነው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም የተደረገው ሙከራ ክትባቱ ሰውነታችን ከበሽታው ጋር እንዲለማመድና አንቲቦዲዎችን እንዲያዳብር መርዳቱ የተስተዋለ ሲሆን ሌላው ደግሞ ቲ-ሴል በመባል የሚታወቀው የመከላከል አቅምን የኮሮናቫይረስን መዋጋት እንዲችል አድርጎታል ተብሏል።
ለሙከራው በሁለት ዙር በሶስት ሳምንት ልዩነት ክትባቱ መሰጠቱ ታውቋል።

ሙከራው በአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱርክ የተካሄደ ሲሆን የሁለተኛ ዙር ክትባት ከተሰጠ ወዲህ 90 በመቶ መከላከል መቻሉን መስተዋሉ ተገልጿል።
ፋይዘርበና ባዮኤንቴክ የተሰኙት ኩባንያዎች 50 ሚሊዮን መጠን ያለው ክትባት በፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ እንደሚያቀርቡ የገለጹ ሲሆን በ2021 ደግሞ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን እንደሚያመርቱ ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
መድሃኒቱ ግን ከአሁኑ ተግዳሮት እንደገጠመው እየተነገረ ነው። ክትባቱ መቀመጥ ያለበት ከዜሮ በታች 80 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚቀዘቅዝ ስፍራ ነው ተብሏል።
ሌላው የመድሃኒት አምራቾቹ መድሃኒቱ በእድሜ ተከፋፍሎ ያለውን ውጤት ያላቀረቡ ሲሆን የሚየዓዳብረው የመከላከል አቅምም ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አልታወቀም።
ዩናይትድ ኪንግደም ይህንን ክትባት 30 ሚሊየን ያህሉን ለመግዛት ትዕዛዟን ቀድማ አስገብታለች።
















