የኮሮናቫይረስ ክትባት ፡ የ"ቭላድሚር ፑቲንን ክትባት" እንዴት እንመነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳይንስ አቋራጭ አያውቅም። በድግግሞሽና በሙከራ የሚፈተሽ ነው። ለዚያም ነው ሳይንስ የተባለው።
ምናልባት ጀብደኝነትና ሳይንስ አብረው አይሄዱ ይሆናል።
አሁን ቭላድሚር ፑቲን እየተተቹ ያሉትም በዚሁ ነው። ብሔራዊ ኩራት ሌላ፤ ሳይንስ ሌላ እየተባሉ።
ምናልባት ይህ ትችት ምዕራቡ ለፑቲን ያለውን ጥላቻ በሳይንስ አስታኮ እየገለጠው ይሆን? ምናልባት መቀደም ያመጣው መንፈሳዊ ቅናት ይሆን?
አገራት ክትባቱን በማግኘት ረገድ ቀዳሚ ለመሆን ድምጽ አጥፍተው በሚራኮቱበት ወቅት ፑቲን 'ተቀድማችኋል' ቢሏቸው ምዕራባዊያን እንዴት ላይከፋቸው ይችላል?
ሌሎች ደግሞ መሀል ገብተው "ተው እንጂ! ይሄ የምሥራቅ የምዕራብ ጉዳይ አይደለም፤ ይሄ ሳይንስ ነው፤ ነገሩን በሳይንስ መስፈሪያ ብቻ እንስፈረው፤ ነገሩን በሳይንስ መነጽር ብቻ እንመልከተው" ይላሉ።
ለመሆኑ የፑቲን ክትባትን እንዴት እንመነው? ሳይንሳዊ ሥነ ዘዴዎችን መዝለልና ፍቱን ክትባት ማግኘትስ ይቻላል?
ይህን ለመመለስ የሳይንስ መነጽራችንን መደቀን ሳይኖርብን አይቅርም።
ክትባቱን አግኝተነዋል
የዘላለም የሩሲያ ፕሬዝዳንት የሆኑ የሚመስሉት ቭላድሚር ፑቲን ለዓለም አዲስ ብስራት አሰምተዋል።
በአገር ውስጥ በተደረገ ምርምር አገር በቀል ክትባት አግኝተናል፤ ሰዎች ላይ አገልግሎት እንዲውልም ይፋዊና ብሔራዊ ፍቃድ ሰጥተናል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የትኛውም የዓለም አገር ለየትኛውም ክትባት ሙሉ ዕውቅና ሰጥቶ ስለማያውቅ ፑቲንና አገራቸው በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ይሆናሉ።
አሁን ሳይንቲስቶችን እያነጋገረ ያለው ነጥብ የትኛውም መድኃኒት ወይም ክትባት ሲፈጠር ሦስት ጥብቅ ምዕራፎችን ማለፍ እያለበት ፑቲን በሁለት ምዕራፍ ብቻ መድኃኒቱ ተፈጠረ ማለታቸው ነው።
ክትባት ሲፈጠር ሰው ላይ ለሁለት ወራት ብቻ ተሞክሮ ውጤታማ ነው ማለት አይቻልም።
ፑቲን ግን ክትባቱ ሁሉንም የሙከራ ደረጃዎችን በአጥጋቢ ሁኔታ ማለፍ ችሏል ነው የሚሉት።
ፑቲን የሰው ልጅን የቤተ ሙከራ አይጥ አድርገዋል በሚል እንዳይወነጀሉ ሊሆን ይችላል ክትባቱ ከተሰጣቸው ዜጎች መሀል ሴት ልጃቸውን አስገብተዋታል።
አሁን ነገሩ ሁሉ ስለተጠናቀቀ በመጪው ኅዳር ክትባቱን በገፍ ማምረት እንጀምራለን ብለዋል።
በዚህ ዜና በቅድሚያ ከደነገጡት መሀል ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ይህ ዜና ገና ይፋ ከመሆኑ በፊት "ሩሲያ እባክሽን በክትባት ምርምሩ ሂደት እኛ ያስቀመጥናቸውን ሒደቶች ተከተይ" ሲል ተማጽኗታል።
ማክሰኞ ደግሞ ድርጅቱ እንዳለው ከሩሲያ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር ጀምሯል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስፑትኒክ-5
ጥድፊያ ከሳይንስ ይልቅ ለብሔራዊ ኩራት ቅድሚያ እንደሰጠ አንድ ማሳያ ሆኖ የቀረበው ለክትባቱ የተሰጠው ስም ነው።
ስፑትኒክ-5 (Sputnik-V) የሚል የቁልምጫ ስም ነው የተሰጠው። ስፑትኒክ ወደ ጨረቃ ያቀናችው በዓለም የመጀመሪያዋ የሩሲያ ሳተላይት ናት።
ስፑትኒክ በሩስኪ ቋንቋ ሳተላይት ማለት ነው።
ነገሩ የቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ በአሜሪካና በሶቭየት ኅብረት መካከል የነበረውን የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የጦር መሣሪያ ምርት ትንቅንቅና ፉክክር ለማስታወስ ይመስላል።
የሚገርመው ይህ ተሳካ የተባለው ክትባት በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዝርዝር ውስጥ ምዕራፍ ሦስት ከደረሱ ስድስት ተስፋ ሰጪ ክትባቶ አንዱ ሆኖ እንኳ አልተመዘገበም ነበር።
ምዕራፍ ሦስት የክትባት ሙከራ ማለት ክትባቱ በምዕራፍ ሁለት በተመረጡ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ከተሞከረ በኋላ አጥጋቢ ውጤት ሲያሳይ በርከት ባሉ ሰዎች ለመጨረሻ ዙር ሙከራ የሚያልፍበት ደረጃ ነው።
በክሊኒካል ደረጃ አሁን መቶ የኮቪድ-19 ሙከራዎች በመላው ዓለም ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ይገኛሉ።
የፈለገ ፈጣንና ቀልጣፋ አሰራር ቢዘረጋ አስተማማኝ የኮቪድ-19 ክትባት እስከ ሚቀጥለው የፈረንጆች 2021 አጋማሽ ድረስ እውን ሊሆን አይችልም ይላሉ እውቅ የጤና ጉዳይ አዋቂዎች።
ይህም ማለት አሁን ካለንበት ብንቆጥር ገና 10 ወራትን መጠበቅ ማለት ነው። እስከዚያ ድረስ ስንቶቻችን በሕይወት እንቆይ ይሆን?
ማነው ይህን ክትባት ያመረተው?
በዓለም የመጀመርያው የተባለው ይህ ስፑትኒክ-5 ክትባት ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲትዩት ነው ያመረተው።
ኢንስቲትዩቱ እንደሚለው ክትባቱ አስተማማኝ የመከላከል አቅም ይሰጣል።
ፑቲን በበኩላቸው ገና ቀደም ብሎ "ይህ ክትባት አስተማማኝ እንደነበር አውቅ ነበር" ብለዋል። "ሁሉንም ሳይንሳዊ ሂደቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ማለፍ ችሏል" ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል።
ፑቲን ከልጆቻቸው ለአንዷ ክትባቱ ተሰጥቷት ትንሽ አተኮሳት እንጂ ምንም አልሆነችም ብለዋል።
ፑቲን የትኛዋ ልጃቸው ክትባቱን ወስዳ እንዳተኮሳት ግን በስም አልገለጹም።
ሩሲያዊያንን ያስገረመው ታዲያ ፑቲን በታሪካቸው ስለ ሴት ልጆቻቸው ማሪያ ቮሮንዞቫ እና ካተሪና ቲኮኖቫ በሚዲያ ሪፖርት ላይ ተናግረው አለማወቃቸውና አሁን ግን ይህን ማድረጋቸው ነው።
የሩሲያ ሳይንቲስቶች የመጀመሪያ ዙር ሙከራዎች ተደርገው ሁሉም ድንቅ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል።
ሳንቲስቶቹ ሰዎች ላይ ጉንፋንን የሚያመጣው አዲኖቫይረስ የተሰኘውን የተላመደ የተህዋስ ቅንጣት ተጠቅመው ነው ክትባት ሰራን ያሉት።
ይህን ለማዳ ተህዋሲ አዳክመው ወደ ሰውነት በማስገባት ሕዋስ በማቀበል ክትባቱ ሰውነት ኮቪድ-19 ተህዋሲ ሲገባ ነቅቶ እንዲዋጋ ያደርገዋል ብለዋል።
አሁን የሩሲያ የጤና ባለሥልጣናት ለዚህ ክትባት እውቅና የሰጡት ክትባቱ በብዙ ሺህ ሰዎች ሳይሞከር መሆኑ ነው ጥያቄ ያስነሳው።
በተለመደው አሰራር ምዕራፍ ሦስት የደረሰ ክትባት ወደ ገፍ ምርት ከመገባቱ በፊት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ይሰጣል።
በዚህ ሂደት ክትባቱ የሚሰጣቸው በተለያየ የዕድሜና የጤና ሁኔታ ላሉ ሰዎች ይሆናል።
ይህም ክትባቱ የማይታወቅ አሉታዊ ጎንዮሽ ጉዳት ሰዎች ላይ እንዳያደርስ ለመቆጣጠር ነው።
ባለሙያዎች አንድ ክትባት ምዕራፍ ሦስት ላይ የሚገኘውን ሙከራ በብዙ ሺህ ሰዎች ላይ ካላደረገ እንደ ፍቱን ክትባት አይቆጠርም ይላሉ።
ገለልተኛ የጤና ባለሙያዎች ይህን ይበሉ እንጂ የሩሲያ የጤና ሚኒስትር ያገኘነው ክትባት ፍቱን ነው፤ ምንም ስጋት አይግባችሁ ብለዋል። ጨምረውም "ይህ ለሩሲያ ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር በሙሉ ትልቅ ድል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያና የሌሎች አገራት ሙከራ
ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካና ካናዳ፤ ሩሲያ የክትባት ግኝት ምስጢሮችን ልትሰርቀን ሞክራለች ሲሉ ተችተዋታል።
ሩሲያ ክትባቱን ለመፍጠር የሄደችበት ፍጥነት በሕክምና ምርምር ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። የመጀመሪያው የክሊኒካል ሙከራዋን ያደረገችው እጅግ ዘግይታ በሰኔ 17 ነበር።
በቻይና፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ከዚህ ቀን እጅግ ቀደም ብለው ነበር የጀመሩት።
ሌላው የፑቲንን ክትባት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው የጋማሊያ ኢንስቲትዩት ከክትባቱ ጋር በተያያዘ ያሉ እጅግ ጠቃሚ ዳታዎችን (መረጃዎችን) ለማንም አለማጋራቱ ነው።
ይህ ገለልተኛ ሳይንቲስቶች በክትባት ውጤቱና ስኬታማነቱ ዙርያ ምንም አስተያየት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል። ምክንያቱም ምንም መረጃ በእጃቸው ስለሌለ ነው።
ፑቲን ለዓለም አንድ ጥርት ያለ መልዕክት ማስተላለፍ የፈለጉ ይመስላል። የሩሲያ ሳንቲስቶች እጅግ የላቀ ብቃት እንዳለቸውና አገራቸው ልዕለ ኃያል እንደሆነች።
ነገር ግን ይህ አገራዊ ጀብደኝነት ለሳይንስ የሚጥም አይደለም።
እስካሁን የትኛውም የኮቪድ-19 ክትባት በሽታውን መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ አልተከላከለም። አሁን ጥያቄው የፑቲን ክትባት ይህን ያደርጋል ወይ ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ መቀመጫውን ሞስኮ ያደረገው የክሊኒካል ትራያልስ ኦርጋናይዜሽን የተባለውና በሩሲያ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎችን የሚወክለው ቡድን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምዕራፍ ሦስት የሙከራ ደረጃን ሳያጠናቅቅ የክትባቱን ስኬታማነት ይፋ እንዳያደርግ ተማጽኖ ነበር።
የቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ ስቬትላና ዛቪዶቫ እንደሚሉት አንድ መድኃኒት ምዕራፍ አንድና ሁለትን ስላለፈ ፍቱን ነው ተብሎ አይታወጅም።
የፑቲን ክትባት ደግሞ በ76 ሰዎች ላይ ነው የተሞከረው። በምንም ሁኔታ በ76 ሰዎች ላይ የተሞከረን ክትባት ፍቱን ነው አይደለም ልንል አንችልም ብለዋል።
የፑቲን የክትባት ሰበር ዜና ከሳይንስ ይልቅ ብሔራዊ ኩራትን ያስቀደመ ነበር የሚባለውም ለዚሁ ነው። ፍቱኑን ክትባት ለማግኘት አንድ 10 ወራት ያስፈልጉ ይሆናል።
እስከዚያው ግን ተስፋም ዕድሜ ነው። ፑቲን ክትባት ሳይሆን ተስፋን ይሆናል ለዓለም ያበሰሩት።
በክትባቱ ላይ የተሰነዘረው ትችት "መሰረተ ቢስ ነው"
ማክሰኞ ዕለት ሩሲያ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ካሳወቀች በኋላ በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ጉዳዩ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት በመግለጽ በክትባቱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸው ነበር።
ነገር ግን ሩሲያ በሰጠችው ምልሽ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘረ ያለው ስጋት "መሰረተ ቢስ" ነው ስትል በክትባቱ ላይ ያላትን መተማመን ገልጻለች።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ሚኻይል ሙራሽኮ እንዳሉት "በውጭ አገራት ያሉ ባልደረቦቻችን ያገኘነው ክትባት ከሌሎች አንጻር ተፎካካሪ የበላይነት እንዳለው ተገንዝበው ፍጹም መሰረት ቢስ አስተያየት ለመስጠት እየሚከሩ ነው" ሲሉ ኢንትርፋክስ ለተባለው የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጨምረውም ክትባቱ በቅርቡ ለአገልግሎት እንደሚቀርብ ጠቅሰው "የመጀመሪያው ጥቅም ላይ የሚውለውን ክትባት በሚቀጥለው ሁለት ሳምንት ውስጥ እንረከባለን. . . በቀዳሚነት ለሐኪሞች የሚሰጥ ይሆናል" ብለዋል ሚኒስትሩ።
አሁንም ክትባቱ ላይ ከተለያዩ ወገኖች ጥያቄዎች እየተነሱበት ቢሆንም የሩሲያ ባለስልጣናት እንዳሉት በመጪው ጥቅም ት ላይ ክትባቱን በስፋት ለሕዝቡ ለመስጠት ዕቅድ ይዘዋል።


















