ኮሮናቫይረስ፡ በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ሊደረግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ክትባት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊካሄድ እንደሆነ ይፋ ተደረገ። ደቡብ አፍሪካ ለዚህ የክትባት ሙከራ የተመረጠችው በዘርፉ ባሏት ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያሉባትና ወረርሽኙም በፍጥነት እየተስፋፋባት በመሆኑ ነው።
ይህ የክትባት ሙከራ ኦኤክስ1ኮቪድ-19 ክትባት የሚባል ሲሆን የኮሮናቫይረስን የሚያስከትለውን ሳርስ-ኮቪ-2 የተባለውን ቫይረስ ሰዎች እንዳይያዙ ለመከላከል የታለመ ነው።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተደረገ ምርመራ እስካሁን ቢያንስ 80 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወረርሽኙ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ 1,674 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለሞት ተዳርገዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ይህ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ የዊትስ ዩኒቨርስቲ ከዩናይትድ ኪንግደሙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እና ኦክስፎርድ ጀነር ኢነስቲቲዩት ከተባሉ ተቋማት ጋር የሚካሄድ መሆኑ ተግለጿል።
በሽታው ወሳኝ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ የሚደረገው ይህ የክትባት ሙከራ ለደቡብ አፍሪካ ም ሆነ ለአፍሪካ ከፍያለ ጥቅም የጠቀሱት በዊትስ ዩኒቨርስቲ የክትባት አጥኚ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳቢር ማድሂ፤ በሽታው እየተባባሰ ህሙማን ከመበርከታቸው በፊት ክትባቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል። '
የክትባቱ ሙከራ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የሚደረግ ሲሆን ለዚህም ባለፈው ሳምንት በሙከራው የሚሳተፉ ሰዎች ባለፈው ሳምንት የተመረጡ ሲሆን ሙከራው በዚህ ሳምንት ይደረጋል ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው የክትባት ሙከራ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጥልቅ ፍተሻ ተደርጎበት በደቡብ አፍሪካ መንግሥት የጤና ምርቶች ተቋጣጣሪ ተቋምና በዊትስ ዩኒቨርስቲ ፈቃድ ተሰጥቶታል ተብሏል።
ይህ ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከአራት ሺህ ሰዎች በላይ የተሳተፉበት ክሊኒካል ሙከራ የተደረገበት ሲሆን በደቡብ አፍረካ ከሚደረገው ሙከራ ጋር ተመሳሳይና ተዛማጅ የሆነ ሙከራ ብራዚል ውስጥ ሊጀመር እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሁሉም የላቀ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚሳተፉበት የዚህ ክትባት ሙከራ አሜሪካ ውስጥ በ30 ሺህ ሰዎች ላይ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል።
በደቡብ አፍረካው የክትባት ሙከራ ላይ ጥቅም ላይ የሚውለው ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም እና በብራዚል ውስጥ የተሞከረው እንደሆነ ተገልጿል።
ክትባቱ የሚሰጣቸው ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ሰውነታቸው የኮሮናቫይረስን እንዲያውቀው በማድረግ ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም እንዲያዳብር በማድረግ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ይችላሉ ብለው ተመራማሪዎቹ አዎንታዊ ውጤትን ይጠብቃሉ።


















