የኮቪድ-19 ክትባት ለድሃ አገሮች በፍጥነት እንዲደርስ የ2 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

ክትባት የምታዘጋጅ ነርስ በቻይና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ግዙፉ መድኃኒት አምራች አስትራዜኔካ ሁለት አዳዲስ ስምምነቶችን ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቶቹ ኩባንያው በአንድ ጊዜ ለኮሮናቫይረስ ክትባት 2 ቢሊዮን ጠብታዎችን ለማምረት የሚያስችለው ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው ወር አስትራዜኒካ በአንድ ጊዜ 1 ቢሊዮን ጠብታዎችን ማምረት እንደሚችል ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ለተያዘውና ተስፋ ለተጣለበት የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር የተደረገ ዝግጅት ነው፡፡

ትናንት ሐሙስ ግን ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ ስምምነቶችን የተፈራረመ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አንዱ በቢለጌትስ የሚደገፍ ነው፡፡

የእንግሊዙ አስትራዜኒካ በቅልጥፍና ያመርተዋል የተባለው ይህ የኮሮናቫይረስ ክትባት መድኃኒት በዋናነት እንዲደርስ የታሰበው ደግሞ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች ነው፡፡

አስትራዜኒካ በበኩሉ ለፍጥነት እንዲረዳው ከሌሎች ሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የመጀመርያው ሴሩም ኢንዲያ ጋር ሲሆን ይህ መድኃኒት አምራች በዓለም ላይ መድኃኒትን በከፍተኛ መጠን በማምረት አቅሙ ተስተካካይ የለውም፡፡

ሁለተኛውም ስምምነት የተደረገው ደግሞ ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ጋር በቅንጅት ከሚሰሩ ሌሎች ሁለት ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ይህም የ750 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ማዕቀፍ ነው፡፡

ሁለቱ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ የሚደገፉት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋቪ እና ሴፒ የሚባሉ ሲሆን 300 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባት የማምረት ሂደቱን እንዲያሳልጡና የምርት ግብአቶችን እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል፡፡

የክትባት መድኃኒቱ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይደርሳል ተብሎ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

የአስትራዜኔካ ሥራ አስፈጻሚ ፓስካል ሶሪዮት ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት በነሐሴ መጨረሻ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየሞከረው ያለው ክትባት ውጤታማነት ይረጋገጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሴፒ ሥራ አስፈጻሚ በበከላቸው ይህ ክትባት ላይሰራም የሚችልበት ዕድል እንዳለ መገንዘብ ያሻል ብለዋል፡፡

አስትራዜኔካ ከህንዱ ግዙፍ መድኃኒት አምራች ‹‹ሴሩም ኢንዲያ›› ጋር ያደረገው ስምምነት በአንድ ጊዜ አንድ ቢሊዮን የክትባት ብልቃጥ የማምረት ስምምነት ሲሆን ይህም በዋናነት ለመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት የሚሆን ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ማእቀፍ ውስጥ ሴሩም ኢንዲያ 400 ሚሊዮን የክትባት ጠብታ የፈረንጆቹ 2020 ከመጠናቀቁ በፊት ማድረስ ግዴታ ይኖርበታል፡፡

ቢል ጌትስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአስትራዜኒካ ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ሶሪዮት እንደተናገሩት በቅድሚያ 300 ሚሊዮን የክትባት ጠብታዎች የሚላኩት ወደ አሜሪካ ሲሆን 100 ሚሊዮን ደግሞ ለዩናይትድ ኪንግደም የተያዘ ነው፡፡ ይህም በመስከረም እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

እርሳቸው ጨምረው እንዳስገነዘቡት ድርጅታቸው አስትራዜኒካ በወረርሽኙ ወቅት ለሚፈበረኩ የክትባት ጠብታዎች ምንም ዓይነት ትርፍ የማጋበስ ዓላማ አልተያዘም፡፡ ‹‹ ይህ በመላው ዓለም የመጣ መቅሰፍት ነው፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ፈተናን የደቀነ ነው፤ በዚህ ወቅት ስለ ትርፍ ልናስብ አንችልም ብለዋል፡፡

ይህ ክትባት ፍቱንነቱ ከተረጋገጠ ለዘመናት የሰው ልጆች የሚወስዱት ክትባት ስለሚሆን ምናልባት በዚህ የመጀመርያ የወረርሽኙ ወቅት ኩባንያዎች ትርፍን ታሳቢ ላያደርጉ የሚችሉበት እድል ሰፊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በዚህ ላይ የዓለም መንግሥታት ለዚህ በጉጉት ለሚጠበቀው የኮቪድ-19 ክትባት ማግኛ እና ማምረቻ የሚሆን ቢሊዮን ዶላሮችን ለማዋጣት ቃል ገብተዋል፤ እያዋጡም ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ በርካታ ቤተ ሙከራዎች እና መድኃኒት አምራቾች ውጤታማውን ክትባት ቀድሞ ለማግኘት በከፍተኛ እሽቅድምድም ላይ ናቸው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬ ትናንት ሐሙስ ባስተላለፉት መልእክት ‹‹ እየጠበቅነው ያለነው ክትባት መታየት ያለበት ለሁሉም የሰው ልጆች በእኩል የሚደርስ የሕዝብ ክትባትን ነው›› ካሉ በኋላ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በየአቅሙ ርብርብ እንዲያደርግም ተማጽነዋል፡፡

ኮሮና
Banner