ኮሮናቫይረስ፡ የድረ ገፅ የዓሣ ሽያጭ ተጧጡፏል

አሳ አጥማጅ

የፎቶው ባለመብት, MyFishman

ማሌዥያ አገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች። በዚህ ወቅት ካሜሮን በተባለች ግዛት የሚገኙ አርሶ አደሮች የዓሣ ምርታቸውን መሸጥ ስላልቻሉ ይጥሉትም ነበር። መደብሮች ተዘግተው ስለነበር አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት አርሶ አደሮች ፊታቸውን ወደ ድረ ገፅ ግብይት አዙረዋል።

በማሌዥያ ብቻ ሳይሆን በመላው ደቡብ ምሥራቅ እስያ ያሉ አርሶ አደሮችና አሣ አስጋሪዎች ድረ ገፅን ከሸማች ጋር ለመገናኘት እየተጠቀሙ ነው።

ስቲቭ ቶሽ በቆሎና አበባ ይሸጣል። ከማሌዥያ መዲና ኳላ ላምፑር በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ካሜሮን ግዛት እርሻ አለው።

“የእንቅስቃሴ ገደቡ ሲጣል አበባዎቹን እጥል ነበር። የአበባ ፍላጎት የቀነሰው በፍጥነት ነበር” ሲል የገጠመውን ይገልጻል።

‘ላዛዳ’ የተባለ የድረ ገፅ መገበያያ እንደ ስቲቭ ያሉ አርሶ አደሮችን ታድጓል። በድረ ገፅ ከአበባ ፈላጊዎች ጋር እንዲገናኝም መንገድ ከፍቶለታል።

እንደ ቀድሞ አትክልትና ፍራፍሬ ይዘው ወደ ገበያ መውጣት ያልቻሉ አርሶ አደሮችም የስቲቭን ፈለግ ተከትለዋል።

የእንቅስቃሴ ገደብ በታወጀ በመጀመሪያው ሳምንት ከ1.5 ቶን በላይ የአትክልት ምርት በድረ ገፁ ተሽጧል። ስቲቭ እንደሚለው “የድረ ገፅ ግብይት ባይጀመር ኖሮ ብዙ አበባ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ይጣል ነበር።”

የአሣ ምርቶች መደብር ባለቤቷ አውድሪ ጎ፤ በማሌዥያ ዓሣ ታከፋፍላለች። ዓሣ በየቤቱ ማከፋፈል፣ በመደብር መሸጥም ስላልቻለች በድረ ገፅ ምርቱን ማቅረብ ጀምራለች።

“ምርታችንን ለሬስቶራንቶች ማቅረብ አልቻልንም ነበር። በብዛት ዓሣ የሚገዙ ተቋሞችም ሥራ አቁመዋል። በድረ ገፅ መሸጣችን ንግዱ እንዳይቆም ረድቶናል።”

አውድሪ እንደምትለው፤ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ሰዎች ምግብ እያከማቹ ስለነበር የዓሣ ሽያጭ በ150 በመቶ ጨምሯል።

ኮሮና
Banner

ከድረ ገፁ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ዓሣ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል።

የላዝዳ ድረ ገፅ ዋና ኃላፊ ፒሬ ፖጋንት እንደሚናገሩት፤ የተጠቃሚዎች ፍላጎት እየተቀየረ በመምጣቱ አርሶ አደሮችና ሌሎች አምራቾችም የሽያጭ አካሄዳቸውን እየለወጡ ነው።

ሩማህ ሳዩር የተባለ ቡድን የኢንዶዜዥያ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ በድረ ገፅ ምርታቸውን ያሻሽጣል። ከ89 መንደሮች የተውጣጡ 2,500 አርሶ አደሮችንም አቅፏል።

ቀድሞ በጃካርታ ዙርያ ለመደብሮች፣ ለሆቴሎች፣ ለሬስቶራንቶችና ለካፌዎች ምርት ያቀርብ ነበር። ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ግን ሽያጭ 60 በመቶ አሽቆልቁሏል። ከዚያ ግን ድረ ገፅን እንደ አማራጭ ወሰዱ።

አርሶ አደሩ ፓክ ኦፒክ፤ በጃካርታ ጎመንና ሌሎችም አትክልቶች ይሸጥ ነበር።

“ይህ ወረርሽኝ ለኛ ለአርሶ አደሮች እጅግ ፈታኝ ነው። የለመድነው በባህላዊ መንገድ ገበያ ወጥቶ መሸጥ ነበር። ይህ ሲቋረጥ ምርታችንን በድረ ገፅ መሸጥ ጀመርን። አሁን ሰዎች ከቤታቸው መውጣት ስለማይችሉ በዚህ መንገድ ይሸምታሉ።”

ላዝዳ ድረ ገፅ ከታይላንድ መንግሥትም ጋር ይሠራል። ቀድሞ ምርታቸውን ከአገር ውጪ ይሸጡ የነበሩ አርሶ አደሮች የአገር ውስጥ ገበያ እንዲያገኙም ይደግፋል።

ሰኔ ላይ ወደ 50 የሚደርሱ ፍራፍሬ አምራቾችን የማቀፍ እቅድም ነድፈዋል።

የቻይናው የድረ ገፅ መገበያያ አሊባባ፤ የቀጥታ ግብይት መድረኩን ለአርሶ አደሮች ከክፍያ ነፃ አድርጓል። የቻይና አርሶ አደሮችን ከ41 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ጋር ለማገናኘትም ወጥኗል።

የቀጥታ ግብይቱ በተጀመረ በሦስት ቀናት ውስጥ 15 ሚሊዮን ኪሎ ምርት መሸጡንም ጃክ ማ የመሠረቱት አሊባባ አስታውቋል።