የአሜሪካ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ቬንዙዌላ "ኢንቨስት የሚደረግባት አይደለችም" ሲሉ ለትራምፕ ተናገሩ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቬንዙዌላ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ከነዳጅ ኩባንያዎች 100 ቢሊዮን ዶላር ቢጠይቁም ያገኙት ምላሽ ያልጠበቁት ሆኖባቸዋል።

በዋይት ሐውስ በነበረው ስብሰባ ላይ አንድ የግዙፍ የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቬንዙዌላ "አሁን ኢንቨስት የሚደረግባት" አይደለችም ብለዋል።

የዓለማችን ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች ከትራምፕ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ኃላፊዎቹ ቬንዙዌላ ግዙፍ የነዳጅ ክምችት እንዳላት ቢያምኑም አካባቢውን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ ብዙ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ኃይሎች ወደ ካራካስ አቅንተው የሀገሪቱን ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ ትራምፕ የቬንዙዌላን የነዳጅ ሀብት ለዓለም ገበያ አውላለሁ ማለታቸው ይታወሳል።

አርብ በዋይት ሐውስ በነበረው ውይይት "ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ የምታገኘው ጥቅም ዋጋው ዝቅ ያለ የኃይል አቅርቦት ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

ነገር ግን የነዳጅ ኩባንያ ባለቤቶቹ ሁኔታው በጥንቃቄ እንዲታይ ይሻሉ።

ከአሜሪካ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ኤክሶን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳረን ዉድስ "ሁለት ጊዜ ንብረታችን ተወርሶብናል። ሶስተኛ ጊዜ ስንገባ ትልቅ ለውጥ እንሻለን። ሀገሪቱ አሁን ባለው ሁኔታ ኢንቨስት የሚደረግባት አይደለችም" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቼቭሮን የተባለው ኩባንያ በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር አሁንም እየተንቀሳቀሰ ያለ ብቸኛው የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያ ነው።

የስፔኑ ሬፕሶል እና የጣሊያኑ ኢኒ ቬንዙዌላ ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች በዋይት ሐውስ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል።

ትራምፕ የትኛው ኩባንያ ቬንዙዌላ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችል ፈቃድ የሚሰጠው መንግሥታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"ከኛ ጋር ነው የምትሠሩት። ከቬንዙዌላ ጋር አይደለም። ከቬንዙዌላ ጋር እንድትሠሩ አንፈልግም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ዋይት ሐውስ እንዳለው ቬንዙዌላ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን "እየነቀሰ" ለማንሳት ዝግጅት ላይ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሁን ሀገሪቱን ከሚመሩት ከቀድሞዋ የማዱሮ ምክትል ዴልሲ ሮድሪጌዝ ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።

አሜሪካ በተገባደደው ሳምንት ማዕቀብ የተጣለበት ነዳጅ የጫነ መርከብ በቁጥጥር ሥር ማዋሏን አስታውቃለች። ከነዳጅ ሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ባለ የሒሳብ መዝገብ ውስጥ እንደሚገባ ተነግሯል።

ትራምፕ አርብ ዕለት የፈረሙት ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ከቬንዙዌላ ነዳጅ ሽያጭ የሚገኝ ገንዘብን እንዳይንቀሳቀስ እንዳያግዱ ያስገድዳል።

የቬንዙዌላ የነዳጅ ምርት በተለይ ባለፉት አስርታት በዝቅተኛ ኢንቨስትመንት እና በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። የዓለማችን ቁጥር አንድ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር በቀን 1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የምታመርት ሲሆን ይህም ከዓለም አቅርቦት ሲነፃፀር 1 በመቶ ብቻ ነው።

ኤክሶን እና ሼል በቬንዙዌላ ያለው የደኅንነት ሁኔታ ካልተጠበቀና ሕጋዊ ዋስትና ከሌለው "አይደለም በ10 ቢሊዮኖች አንድ ቢሊዮንም ኢንቨስት አያደርግም" ሲሉ ጎልድዊን ተናግረዋል።