ነዳጅ ወይስ ዕፅ? ትራምፕ ማዱሮን በቁጥጥር ስር ያዋሉት ለምንድነው?

ካራካስ የሚገኘው ፉዌርቴ ቲዩና የተባለው ወታደራዊ ካምፕ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Luis JAIMES / AFP via Getty Image

የምስሉ መግለጫ, በካራካስ ጥቃት ከደረሰባቸው ስፍራዎች መካከል ፉዌርቴ ቲዩና የተባለው ወታደራዊ ካምፕ አንዱ ነው

ፕሬዝደንት ትራምፕ የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ በካራካስ ከተፈፀመ መጠነ ሰፊ ጥቃት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቁት ቅዳሜ ንጋት ነው።

የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ፣ ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው በኒው ዮርክ ከተማ ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታውቀዋል።

ዐቃቤ ሕጓ ጨምረውም "ከዕጽ ምርት እና ዝውውር ጋር የተያያዘ ሴራ፣ ኮኬይን ወደ አሜሪካ በማስገባት ሴራ፣ መትረየሶች እና አውዳሚ መሳሪያዎችን በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ለመያዝ በማሴር" የሚሉ ክሶች በማዱሮ ላይ እንደቀረቡባቸው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ እና ባለቤታቸው አሜሪካ ውስጥ "በአሜሪካ ምድር፣ በአሜሪካ ፍርድ ቤት የአሜሪካንን የፍትሕ አቅም ሙሉ ለሙሉ በቅርቡ ይጋፈጡታል" ሲሉም አክለዋል።

ማዱሮ እንዴት ወደ ሥልጣን መጡ?

ማዱሮ ሰይፍ ይዘው በፓርላማ ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኒኮላስ ማዱሮ ወደ ሥልጣን የመጡት በግራ ዘመሙ ፕሬዝደንት ሁጎ ቻቬዝ አመራር ወቅት ነበር። ማዱሮ የቻቬዝ የቬንዙዌላ ዩናይትድ ሶሻሊስት ፓርቲ መሪ ናቸው።

የቀድሞው የአውቶቡስ ሹፌር፤ ቻቬዝን ተክተው የቬንዙዌላ ፕሬዝደንት የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2013 ነው።

ቻቬዝ እና ማዱሮ ቬንዙዌላን ላለፉት 26 ዓመታት መርተዋል። ፓርቲያቸው ብሔራዊውን ጉባዔ፣ አብዛኛውን ፍርድ ቤት እና የምርጫ ኮሚሽኑን ይቆጣጠራል።

በ2024 ማዱሮ የብሔራዊው ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው ታወጀ። ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲው የሰበሰበው ድምፅ የሚጠቁመው ተቀናቃኛቸው ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ምርጫን በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን ነው።

ጎንዛሌዝ ዋነኛዋ የተቃዋሚ መሪ የነበሩት ማሪና ኮሪና ማቻዶ በምርጫው እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን ተከትሎ ነው ዕጩ ሆነው የቀረቡት።

ማቻዶ ባለፈው ጥቅምት "ከአምባገነንት ወደ ዲሞክራሲ ለሚደረገው ሽግግር ሰላማዊ ትግል በማድረጋቸው" የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ማቻዶ የተጣለባቸውን የጉዞ እግድ በመጣስ ባለፈው ታኅሣሥ ከተደበቁበት ወጥተው ወደ ኦስሎ በማቅናት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ትራምፕ ቬንዙዌላን ዒላማ ያደረጉት ለምንድነው?

ትራምፕ የቬንዙዌላው መሪ ወደ አሜሪካ ለሚመጡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።

በቬንዙዌላ ያለውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ እና አፈና በመሸሽ ከ2013 በኋላ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ቬንዙላዊያን ከሀገራቸው እንደሸሹ ይገመታል።

ምንም እንኳ ትራምፕ ማስረጃ ባያቀርቡም ማዱሮ "እስር ቤት የአእምሮ በሽተኞች ማቆያዎች" ያሉ ግሰለቦች "ወደ አሜሪካ እንዲሸሹ አድርጓ" ሲሉ ይወቅሳሉ።

ትራምፕ ወደ አሜሪካ የሚገቡ በተለይ ፌንታኒል እና ኮኬይን የተባሉ አደንዛዥ ዕፆችን ለመቆጣጠር ቆርጠው መነሳታቸውን ይናገራሉ።

ትሬን ዴ አራሁዋ እና ካርቴል ዴ ሎስ ሶሌስ የተባሉ ሁለት የወንጀለኛ ቡድኖችን አሸባሪ ሲሉ ፈርጀዋል። አክለው ሁለተኛው ቡድን የሚመራው በማዱሮ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

ተንታኖች እንደሚሉት ካርቴል ዴ ሎስ ሶሌ የወንጀለኛ ቡድን ሳይሆን ኮኬይን በቬንዙዌላ በኩል እንዲያልፍ የሚፈቅዱ ሙሰኛ ፖሊሶችን ለመግለፅ የወጣ ስም ነው።

ትራምፕ ማዱሮ ያሉበትን ለሚጠቁም 50 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እንደሚከፍሉ ተናግረው የቬንዙዌላ መንግሥትን አሸባሪ ቡድን ብለው እንደሚፈርጁ አስጠንቅቀው ነበር።

ማዱሮ በተደጋጋሚ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ አለመሆናቸውን ተናገረው አሜሪካ "በዕፅ ላይ ከፈትኩት ያለችው ጦርነት" እሳቸውን ከሥልጣን ለማስወገድ እና የቬንዙዌላ የነዳጅ ክምችትን ለመቀራመት ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቬንዙዌላ አሜሪካን በዕፅ እያጥለቀለች ነው?

የአደገኛ ዕፅ ምሁራን እንደሚሉት ቬንዙዌላ በዓለማችን የዕፅ ዝውውር ውስጥ ያላት ሚና ዝቅተኛ ሲሆን በሌሎች ሀገራት የሚመረቱ ዕፆች የሚተላለፉባት ሀገር ናት።

በተቃራኒው ጎረቤቷ ኮለምቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኮኬይን አምራች ብትሆንም ይህ ዕፅ በቬንዙዌላ ሳይሆን በሌሎች ሀገራት በኩል ወደ አሜሪካ እንደሚገባ ይታመናል።

የአሜሪካ ዕፅ ቁጥጥር ቢሮ (ዲኢኤ) በ2020 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ወደ አሜሪካ ከሚመጣው ኮኬይን አንድ ሶስተኛው በፓሲፊክ በኩል የሚገባ ሲሆን አነስተኛ መጠን ያለው ደግሞ በካሬቢያን በኩል ይገባል።

ከሄሮይን 50 እጥፍ ኃይል ያለው ፌንታኒል የተባለው ዕፅ፤ በአሜሪካ ለሚከሰተው ኦፒዮይድን አብዝቶ በመውሰድ የሚመጣ ሞት ቁጥር አንድ ተጠያቂ ነው።

በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ትራምፕ ፌንታኒል "ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ" ነው ሲሉ ፈርጀው ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ካስተላለፉ "ከዕፅ ይልቅ ለኬሚካል ጦር መሣሪያ የቀረበ ነው" ብለውታል።

ዲኢኤ በ2025 ባወጣው ሪፖርት ላይ ፌንታኒል የሚመጣባቸው ሀገራት የተዘረዘሩ ሲሆን ቬንዙዌላ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም።

እዚህ እንዴት ደረስን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የማዱሮ መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር ጀምረው ነበር።

የመጀመሪያው እርምጃቸው ማዱሮ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚረዳ መረጃ ለሚያቀርብ አካል 50 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እንደሚከፍሉ ማሳወቅ ነበር።

ባለፈው መስከረም ደግሞ ከደቡብ አሜሪካ ወደ አሜሪካ ዕፅ ይዘው እየመጡ ነው የተባሉ ጀልባዎች ላይ የአሜሪካ ጦር ጥቃት መፈፀም ጀመረ።

በካሬቢያን እና በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ 30 ያክል ጥቃቶች ተፈፅመው 110 ሰዎች ተገድለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ዕፅ አዘዋዋሪዎች ናቸው ካላቸው ቡድኖች ጋር ዓለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት ውስጥ መግባቱን ይናገራል።

የሕግ ባለሙያዎች ጥቃቱ "ሕጋዊ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የተነጣጠረ አይደለም" ይላሉ። በተለይ በመስከረም ወር መባቻ በአንዲት ጀልባ ላይ ሁለት ጊዜ ጥቃት መፈፀሙ ሁኔታዎች እንዲካረሩ ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው ጥቅምት ትራምፕ የሀገራቸው የስለላ ድርጅት የሆነው ሲኤአይ ቬንዙዌላ ውስጥ ድብቅ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ መፍቀዳቸውን ተናግረዋል። "የዕፅ-ሽብርተኞች" የሚሏቸው ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉም ዝተዋል።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ማዱሮ "የአሜሪካ ወዳጅ አይደለም" እንዲያውም "ብልህ ከሆነ ከሥልጣን በጊዜ ቢወርድ ይሻለዋል" የሚል ዛቻ አሰምተዋል።

አክለው ከቬንዙዌላ የሚወጡ እና ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል። ነዳጅ የማዱሮ መንግሥት ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው።

አሜሪካ የኮኬይን እና ፌንታኒል ጉዞን ለመግታት በሚል በካሬቢያን ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረችው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።

የአሜሪካ 15 ሺህ ገደማ ወታደሮች፣ የተለያዩ የጦር አውሮፕላኖች፣ ፀረ-ሚሳዔል መሣሪያዎች እንዲሁም የጦር መርከቦች በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ። ዩኤስኤስ ጄራልድ ፎርድ የተባለው የዓለማችን ግዙፉ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከብም አድራሻውን በካሬቢያን አድርጓል።

በዓለማች ግዙፉ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ ጄራልድ ፎርድ

የፎቶው ባለመብት, US Navy/Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዩኤስኤስ ጄራልድ ፎርድ በዓለማች ግዙፉ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከብ ነው

ቬንዙዌላ ምን ያህል ነዳጅ ታመርታለች? የሚገዛትስ ማነው?

ማዱሮ በተደጋጋሚ አሜሪካ ከሥልጣን ልታነሳቸው እንደምትፈልግ እና የቬንዙዌላን የነዳጅ መቆጣጠር እንደምትሻ ሲወቅሱ ተሰምተዋል።

አሜሪካ ከቬንዙዌላ ጠረፍ የተነሳ የነዳጅ መርከብ በቁጥጥር ስር ባዋለችበት ወቅት ነዳጁ ምን ይሆናል ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ "ያው የኛ ይሆናላ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የማዱሮን መንግሥት ማውረድ የፈለጉት የሀገሪቱን ሰፊ ሀብት ለመቀራመት ነው የሚለውን ሐሳብ ያጣጥላሉ።

ቬንዙዌላ በዓለማችን ትልቁ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር ስትሆን ከነዳጅ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ከመንግሥት በጀት ግማሽ ያክሉን ይሸፍናል።

ነገር ግን ወደ ውጭ የምትልከው ነዳጅ መጠን በማዕቀብ ምክንያት ውሱን ሲሆን በሀገሪቱ መንግሥት የሚመራው የነዳጅ ኩባንያ ብልሹ አሰራር እንዳለበት ይታመናል።

የአሜሪካው ኢነርጂ ኢንፎርሜሽን ባለሥልጣን እንደሚለው በ2023 ቬንዙዌላ ከዓለማችን ድፍድፍ ነዳጅ 0.8 በመቶ ብቻ ነው ያመረተችው።

በአሁኑ ወቅት በቀን 900 ሺህ በርሜል ነዳጅ ወደ ውጭ የምትልክ ሲሆን ቁጥር አንድ ሸማቿ ቻይና ናት።

ኒኮላስ ማዱሮን ከስልጣን በማስወገድ በቁጥጥር ስር ያዋለው የትራምፕ አስተዳደር "ቬንዙዌላ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሽግግር እስክታደርግ ድረስ በአሜሪካ ነው የምትመራው" ብሏል።