ተቃውሞ የገጠማቸው በአሜሪካ ስደተኞችን የሚያሳድዱት እነማን ናቸው? ምን ሥልጣን አላቸው?

የአሜሪካ የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት (አይስ) ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት (አይስ) መኮንኖች

በሚኒያፖሊስ የ37 ዓመቷ ሬኒ ኒኮል ጉድ በአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ተቋም መኮንን በተተኮሰባት ጥይት መገደሏ ተቃውሞዎችን ቀስቅሷል፤ እንዲሁም ተቋሙ (ኤይሲኢ/አይስ) ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግበት ተወስኗል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ አይስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስሯል። አብዛኞቹ እስሮች የተፈጸሙት ሰዎች በተሰበሰቡበት ስፍራ ነው።

እነዚህ እርምጃዎች ደግሞ የኤጀንሲው ሠራተኞች በመላ አገሪቱ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተቃውሞ እንዲገጥማቸው አድርጓል።

አይስ ማነው? መቼ ነው የተመሠረተው?

አይስ የትራምፕን አስተዳደር በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ ስደተኞችን በጅምላ ለማባረር ያሳለፈውን ውሳኔ በማስፈጸም ግንባር ቀደም ሆኖ እየሠራ ነው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ የአይስን በጀት እና ተልዕኮ በከፍተኛ ሁኔታ አስፍተዋል።

ኤጀንሲው የኢሚግሬሽን ሕጎችን ያስፈጽማል እና በሰነድ አልባ ስደተኞች የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ምርመራ ያካሂዳል። እንዲሁም ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን ከአሜሪካ በማስወጣት ውስጥ የራሱን ሚና ይጫወታል።

አይስ የተቋቋመው በአውሮፓውያኑ መስከረም 11/2001 ለተፈጸመው የሽብር ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በ2002 የአገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ አካል ሆኖ ነው።

ሕግ አውጪዎች የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴርን (ዲኤችኤስ) ሲያቋቁሙ አይስ ደግሞ ከንዑስ ኤጀንሲዎቹ አንዱ በመሆንተቋቁሟል።

 በአይስ መኮንን በተተኮሰ ጥይት የተመታ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአይስ መኮንን መኪናዋ ውስጥ ሳለች ተተኩሶባት የተገደለችው ሴት መኪና

የአይስ መኮንኖች ሰዎችን ለማሰር ሥልጣን አላቸው?

ተቋሙ ተልዕኮው የሕዝብ ደኅንነትን እና ብሔራዊ ደኅንነትን እንደሚያካትት አድርጎ ይመለከተዋል። ሆኖም ግን ያላቸው ሥልጣን በአሜሪካ ውስጥ ካሉት አማካይ የአካባቢ ፖሊስ ተቋማት የተለየ ነው።

የተቋሙ መኮንኖች በሕገ ወጥ መንገድ በአሜሪካ ውስጥ እንደሚኖሩ የሚጠረጥሩ ሰዎችን የማስቆም፣ የማሰር እና ማቆያ የማስገባት ሥልጣን አላቸው።

ነገር ግን በተወሰነ ማዕቀፍ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር መኮንኖቹ ላይ ጥቃት ከፈጸመ ወይም በሥራቸው ጣልቃ ካልገባ በስተቀር አሜሪካዊ ዜግነት ያለውን ግለሰብ የማሰር ሥልጣን የላቸውም።

ይህ ሆኖ ግን እንደ 'ፕሮፐብሊካ' የዜና ድርጅት ገለጻ፣ በትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ የፌዴራል መኮንኖች የአሜሪካ ዜጎችን ያለፍላጎታቸው በቁጥጥር ሥር ያዋሉባቸው ከ170 በላይ ሁኔታዎች ተከስተዋል።

እነዚህ ጉዳዮች ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች እንደሆኑ የጠረጠሯቸውን አሜሪካውያንን ያካትታሉ።

አይስ ኃይል ለመጠቀም ምን ሥልጣን አለው?

የአይስ የኃይል እርምጃዎች አጠቃቀም የሚመራው በአሜሪካ ሕገ መንግሥት፣ በአሜሪካ ሕግ እና የአገር ውስጥ ደኅንነት መምሪያ ባሉት የፖሊሲ መመሪያዎች ጥምረት ነው።

በቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የወንጀል ፍትሕ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክሪስ ስሎቦጊን በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ የሕግ አስከባሪ አካላት "ግለሰቡ እነርሱ ወይም ሌላ ሰው ላይ አደጋን የሚጥል ከሆነ ወይም ግለሰቡ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመ ከሆነ ብቻ ከባድ ኃይልን መጠቀም ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቅጽበት በተላለፈ ውሳኔ የሰው ሕይወት ላጠፉ የኤጀንሲው መኮንኖች ሰፊ ምህረት ሰጥቷል።

በ2023 የወጣው የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የፖሊሲ ማስታወሻ እንደሚያሳየው የፌዴራል ሕግ አስከባሪዎች "ከባድ ኃይልን መጠቀም የሚችሉት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው" ይለል።

እንዲሁም አንድ ፖሊስ "በራሱ ወይም በሌላ ሰው ላይ የሞት ወይም ከባድ የአካል ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት ምክንያታዊ እምነት ካለው ከባድ ኃይልን" ሊጠቀም እንደሚችል አስፍሯል።

የአይስ አባላት አንድ ተቃዋሚ ሰልፈኛን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአይስ አባላት አንድ ተቃዋሚ ሰልፈኛን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ

አይስ የት ነው የሚንቀሳቀሰው?

የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቋም (አይስ) ባልደረቦቹን በአብዛኛው በአሜሪካ ውስጥ የሚያሰማራ ሲሆን፣ አንዳንድ ሠራተኞቹን ከአገር ውጪ መድቦ ነገር ግን ሥራቸው በአሜሪካ ውስጥ ይሆናል።

አይስ የአሜሪካን ድንበርን የሚቆጣጠረው የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ተቋም እህት ኤጀንሲ ነው።

ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር ከተለያዩ የፌዴራል የሕግ አስከባሪ ተቋማት የተወጣጡ መኮንኖችን በኢሚግሬሽን አስከባሪነት እንዲሳተፉ ስላደረገ እነዚህ ሚናዎች እየደበዘዙ መጥተዋል።

የድንበር ተቆጣጣሪ መኮንኖች በአሜሪካ ውስጥ እየሠሩ ሲሆን፣ ከአይስ ጋር በሚደረጉ ዘመቻዎች ውስጥ ይሳተፋሉ።

አይስ እና ሌሎች ኤጀንሲዎች ከሌሎች የፌዴራል የሕግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደ ሎስ አንጀለስ፣ ቺካጎ እና አሁን ደግሞ ሚኒያፖሊስ ባሉ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ መኮንኖችን አሰማርተዋል።

አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው እስከ 2,000 የሚደርሱ የፌዴራል መኮንኖች ወደ ሚኒያፖሊስ እንደሚሰማሩ ዘግቧል።

አይስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ምን ይገጥማቸዋል?

በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ከአገር የተባረሩት ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ነው። አስተዳደሩ እንደ አውሮፓውያኑ ከጥር 20 እስከ ታኅሣሥ 10/2025 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ብቻ 605,000 ሰዎችን ከአሜሪካ ማስወጣቱን ገልጿል።

በተጨማሪም 1.9 ሚሊዮን ስደተኞች እስራትን ለማስቀረት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ለማበረታታት ከተካሄደው ጠንከር ያለ ዘመቻ በኋላ "በፈቃደኝነት ራሳቸውን አባርረዋል" ብሏል።

በአይስ ባልደረቦች ቁጥጥር ሥር የሚውል አንድ ስደተኛ የተለያዩ ነገሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

አንዳንድ ጊዜ ግለሰቡ ለጊዜው ታስሮ ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ይለቀቃል። በሌሎች ሁኔታዎች ግን አይስ ያንን ሰው አስሮ በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች በሚገኙ ከፍ ወዳሉ እስር ቤቶች ይተላለፋሉ።

ብዙ ስደተኞች በእስር ላይ እያሉ ሕጋዊ ለመሆን ጥረታቸውን የሚቀጥሉ ቢሆንም፤ ካልተሳካላቸው ግን ይባረራሉ።

የስደተኞችን መረጃ ከሚያጠናቅር ተቋም የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ከአውሮፓውያኑ እስከ ኅዳር 30/2025 ድረስ ወደ 65,000 የሚጠጉ ሰዎች በአይስ እስር ቤት ውስጥ ነበሩ።

የኢሚግሬሽን ጠበቆች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አንድ ግለሰብ በአይስ ቁጥጥር ሥር አንዴ ከገባ በኋላ ቤተሰቦች ወይም ጠበቆች የት እንዳለ ለማወቅ አንዳንድ ጊዜ ቀናት ሊወስድባቸው ይችላል።

ሬኔ ጉድ ከተገደለች በኋላ አይስን የተቃወሙ ሰዎች ሠልፍ ሲያካሄዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሬኔ ጉድ ከተገደለች በኋላ አይስን የተቃወሙ ሰዎች ሠልፍ ሲያካሄዱ

አይስ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ምንድን ናቸው?

ብዙ ማኅበረሰቦች አይስ እና እንደ የድንበር ተቆጣጣሪ ያሉ አጋር ኤጀንሲዎች ሥራዎችን ሲያከናውኑ እንዳይጠጉ የሚከለክል እርምጃን ይከለከላሉ እርምጃ ወስዳሉ።

ነዋሪዎች የአይስ መኮንኖች እስራት ሲፈጽሙ ቪዲዮ መቅረጻቸው የተለመደ ነው። በአይስ እና በሕዝቡ መካከል በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ጠበኛ ወይም ኃይል የተቀላቀለባቸው ሆነዋል።

በቺካጎ፣ ኢሊኖይ የአይስ ዘመቻዎች ወቅት የሚዲያ ተቋማት ቡድን የድንበር ተቆጣጣሪን ከስሰዋል።

የድንበር ተቆጣጣሪ መኮንኖች በጋዜጠኞች፣ በሃይማኖት መሪዎች እና በተቃዋሚዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ኃይል ተጠቅመዋል ተብለዋል።

የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ከመሻሩ በፊት የፌዴራል ዳኛ ከከሳሾቹ ጎን ቆሞ ነበር።

በኢሚግሬሽን አስከባሪ አካላት ዘመቻ ወቅት አንድ ግለሰብ በተኩስ ሲጎዳ የሚኒያፖሊሱ የመጀመሪያው አይደለም።

በጥቅምት ወር በሎስ አንጀለስ ውስጥ የአይስ መኮንኖች ሁለት ጊዜ በአሽከርካሪዎች ላይ መተኮሳቸውን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል።

በሁለቱም አጋጣሚዎች አሽከርካሪዎች የአይስ መኮንኖችን በተሽከርካሪዎቻቸው ጉዳት ለማድረስ እንዳስፈራሩ ተነግሯል።

የአይስ ኃላፊዎች እና ሌሎች የኢሚግሬሽን መኮንኖች ሥራቸውን ሲያከናውኑ ጭምብል በማድረጋቸውም ተተችተዋል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ይህ አሠራር መኮንኖች ምሥላቸው ያለፈቃዳቸው እንዳይሠራጭ ለመከላከል ወይም ከትንኮሳ ለመጠበቅ እንደሆነ በመግለጽ ተከላክለዋል።

አይስን እና ስደተኞችን በተመለከተ አሜሪካውያን ምን ያስባሉ?

አሜሪካውያን የፕሬዝዳንት ትራምፕን የስደተኞች ቁጥጥር ማስፈጸሚያ ዕቅዶች በተመለከተ የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው የሕዝብ አስተያየት መስጫዎች ያሳያሉ።

በጥቅምት 2025 ፒው የምርምር ማዕከል የሠራው ጥናት እንደሚያመለክተው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አሜሪካውያን በተወሰነ ደረጃ ሕገወጥ ስደተኞችን ማባረር አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ። ይህ ቁጥር ፒው ባለፈው መጋቢት ወር ካገኘው ጋር ተመሳሳይ ነው።

ነገር ግን ተመሳሳይ የሕዝብ አስተያየት ጥናት እንደሚያሳየው አሜሪካውያን ስለ ትራምፕ እርምጃ ማስፈጸሚያዎች ስጋት አላቸው።

የሕዝብ አስተያየት መስጫው እንደሚያሳየው አብዛኞቹ የአሜሪካ ጎልማሶች (53 በመቶ) የትራምፕ አስተዳደር ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን ለማስወጣት "በጣም ብዙ" እያደረገ ነው ብለው ያምናሉ። ወደ 36 በመቶ የሚሆኑት ይህንን አካሄድ ደግፈዋል።