ኢራናዊያን ተቋውማቸውን ማሰማት ሲቀጥሉ፤ ትራምፕ "ለመርዳት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል

የፎቶው ባለመብት, @Vahid
ኢራናዊያን የመንግሥትን አዋጅ ጥሰው ቅዳሜ ምሽት ተቃውሟቸውን ማሰማት መቀጠላቸውን ዘገባዎች አሳይተዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት ቢያንስ 100 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ እና ብዙዎች መጎዳታቸው ቢዘገብም ተቃውሞ አሁንም ጋብ አላለም።
ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ቪድዮዎች እንደሚያሳዩትና የዓይን እማኞች እንደሚሉት መንግሥት ተቃውሞን ለማርገብ ከፍተኛ ኃይል እየተጠቀመ ነው።
በሕዝባዊ ተቃውሞው የተነሳው በኢራን የኢንተርኔት አገልገሎት እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የሀገሪቱ አቃቤ ሕግ ሞሐመድ ሞቫሄዲ አዛድ ቅዳሜ ባስተላለፉት ትዕዛዝ ማንኛውም ተቃዋሚ "የፈጣሪ ጠላት ነው" ይህ ደግሞ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጀመረው ተቃውሞ ተሳትፈዋል የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።
በኑሮ ውድነት ምክንያት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ በመላ ሀገሪቱ የተስፋፋ ሲሆን ከ100 በላይ ከተማዎች ሰልፍ አስተናግደዋል።
ሰልፈኞቹ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ አገዛዝ እንዲወርድ ጠይቀዋል።
ኻሜኒ ተቃዋሚዎቹን "ምድረ አጥፊ" ብለው ካጣጣሉ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን "ለማስደሰት" ሙከራ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የኢራን መንግሥት ተቃውሞን ለማርገብ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጓል። የኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት ውሱን ሲሆን ዳታ በመንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው።
የአሁኑ ተቃውሞ ከሶስት ዓመት በፊት ከታየው "ሴቶች፣ ሕይወት፣ ነፃነት" ከተሰኘው ተቃውሞ ከበድ ያለ መሆኑን አንድ ተንታኝ ለቢቢሲ ፐርዢያ ተናግረዋል።
የኢንተርኔት ጥናት ባለሙያው አሊሬዛ ማናፊ በአሁኑ ወቅት በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት "ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል" ብለዋል።
ኢራናዊያን ከተቀረው ዓለም የሚገናኙበት ብቸኛው መንገድ ስታርሊንክ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው ይህንን የሚጠቀሙ ሰዎች በመንግሥት ክትትል ሊደረግባቸው ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ቢቢሲ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ሁኔታውን መዘገባ ባለመቻላቸው መረጃዎችን ማጣራት አስቸጋሪ ሆኗል።
ቢሆንም አንዳንድ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሾልከው ከመውጣታቸው በተጨማሪ ቢቢሲ ኢራን ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማናገር ችሏል።
ቅዳሜ ምሽት የተቀረፁና ቢቢሲ ያጣራቸው ምስሎች እንደሚያሳዩት ተቃዋሚዎች በቴህራን ጊሻ ጎዳና ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ቢቢሲ ቬሪፋይ ከሰሞኑ የተቀረፁ መሆናቸውን ያረጋገጣቸው ቪድዎች በቫኪል አባድ ጎዳና በተቃዋሚዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት መፈጠሩን ያሳያሉ።
ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ ተቃዋሚዎች እሳት አቀጣጥለው ተሽከርካሪ ጎማ ባላቸው የቆሻሻ መጣያዎች ተከልለው ድምፃቸውን ያሰማሉ። በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ደግሞ ራቅ ብለው በተጠንቀቅ ቆመዋል። አንድ አውቶቡስ በእሳት ተቀጣጥሎ ይታያል።
በርካታ የጥይት ድምፅ የሚሰማ ሲሆን ተቃዋሚዎች ድስትና መጥበሻ እያጋጩ ድምፅ ያሰማሉ። ቢቢሲ ቬሪፋይ ያጣራው አንድ ቪድዮ የተቃውሞ ማዕከል በሆነው የቴህራኑ ፑናክ አደባባይ በርካታ ተቃዋሚዎች ድምፃቸውን እያሰሙ እንደሆነ አሳይቷል።
በሰሜን ምስራቅ ቴህራን ሄራቪ አካባቢ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተው የአሊ ኻሜኒ አገዛዝ እንዲወርድ ሲጠይቁ የሚያሳይ ቪድዮም ተለቋል።
"አሜሪካ ለመርዳት ዝግጁ ናት"
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው "ኢራን ነፃነትን እየሻተች ነው። ምናልባትም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ። አሜሪካ ለመርዳታ ዝግጁ ናት!!!" ሲሉ ፅፈዋል።
ትራምፕ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ፕሬዝደንቱ በኢራን ላይ ሊወሰዱ ስለሚችሉ ወታደራዊ እርምጃዎች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል ሲሉ ዘግበዋል።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ማብላያዎች ላይ እርምጃ መውሰዷ ይታወሳል።
ከፕሬዝደንቱ በተጨማሪ ሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት በኢራን ለሚደረገው ሕዝባዊ ተቃውሞ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።
በተጨማሪም በኢራን አብዮት ከሥልጣን የተወገዱት እና መቀማቸውን አሜሪካ ያደረጉት ሬዛ ፓህላቪ ኢራናዊያን ድምፃቸውን ማሰማታቸውን እንዲቀጥሉ አበረታትተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል "የፀጥታ ኃይሎች ሕጋዊ ያልሆነና እና ከፍተኛ ኃይል እየተጠቀሙ መሆኑን የሚያሳዩ የሚረብሹ ምስሎችን" እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።
ካለፈው አርብ ጀምሮ በሶስት ሆስፒታሎች የሚገኙ ሠራተኞች በተጎጂዎች ቁጥር ምክንያት አገልግሎት መስጠት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ቢቢሲ ፐርዢያ አርብ ምሽት 70 አስከሬኖች ወደ ራሽት ሆስፒታል መምጣቱን አረጋግጧል።














