"የ13 ዓመት ልጄን በነጭ ፖሊስ ልትገደል ትችላለህ ማለት ልብን ይሰብራል" ሶማሊያዊቷ እናት በአሜሪካ

ባለፈው ሳምንት በሚኒያፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ ተጣብቆ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ለአስር ደቂቃ ተጭኖት ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ በአሜሪካ እንዲሁም በተለያዩ በርካታ አገራት ተቃውሞዎችን አቀጣጥሏል።
ከተቃውሞዎቹ ባሻገር ለጥቁር፣ ቀደምት አሜሪካውያንና ከነጭ ውጭ ላለው ማህበረሰብ ደግሞ ንዴትን ብቻ ሳይሆን ፍራቻንም አንግሷል።
በተለይም በነጭ ፖሊሶች እጅ የሚገደሉት ታዳጊዎች ጭምር መሆናቸው ቤተሰቦች ላይ የሚፈጥረው ጭንቀትና ፍራቻ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይከብዳል።
በማያቋርጥ ፍራቻ ከሚኖሩት መካከል ሶማሊያዊቷ ኢፍራህ ኡድጉን ትገኝበታለች። በኦሃዮ የሳይንስ መምህር ስትሆን ወደ አሜሪካም የሄደችው ገና በአስራ ሁለት አመቷ ነው። የሶማሊያን እርስ በርስ ጦርነት ሽሽት ወደ አሜሪካ ቢያቀኑም ሌላ መከራ ዘረኝነት ተቀብሏቸዋል።
በአሁኑ ሰአት የ13 አመት ታዳጊ ልጅ ያላት ሲሆን የዘር ክፍፍል በነገሰበት፣ የነጭ የበላይነት በሚቀነቀንበትና ጥቁሩ ማህበረሰብ መዋቅራዊና የፖሊስ የጭካኔ በትር በሚያርፍበት ሃገር ልጅ ማሳደግ ልብ እንደሚሰብር አልደበቀችም።
ቀደምት አሜሪካውያንን ከሃገራቸው በማፈናቀልና በመጨፍጨፍ የተመሰረተችው አሜሪካ ለበርካታ ስደተኞች ህልምም ቅዠትም ትሆንባቸዋለች።
ኢፍራህና ቤተሰቦቿ የእርስ በርስ ጦርነቱን ሸሽተው ወደ አሜሪካ ሲመጡ ቢያንስ ደህና እንሆናለን፣ በጦርነት ከመታመስም እንተርፋለን በሚል ነበር።
ቢያንስ ልጆቻችንን በተሻለና ደህንነቱ በተጠበቀ ከባቢም እናሳድጋለን የሚል ተስፋን ሰንቀው የነገንም አልመው ነበር፤ ሆኖም በእንዲህ አይነት ስር በሰደደ ዘረኝነት ውስጥ ማሳደግም ቀላል አይደለም።
ለኢፍራንም በአሁኑ ወቅት የሰፈነው ዘረኝነት ከዘመናት ሲንከባለል የመጣና የአሜሪካ ታሪክም ዋና አካል መሆኑን ታስረዳለች።
"አሁን እየተፈፀሙ ያሉት የፖሊስ ግድያዎች ዝም ብለው በአንዳንድ መጥፎ ፖሊሶች የሚፈፀሙ ሳይሆን ከአገሪቱ ህግ፣ ምስረታ፣ ፖሊሲዎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው ናቸው። ይህንን ሁኔታ መረዳት ለወላጅም ልብ የሚሰብር ነገር ነው። ልጄን መጠበቅ እንደማልችና ከኔ ቁጥጥር ውጭ ባሉ ሁኔታዎች ጉዳት እንደሚደርስበት ማሰብም ሆነ ህይወቱ ሊቀጠፍ እንደሚችል ማሰብ ከጭንቅላት በላይ ነው" ትላለች።
በአሜሪካ ውስጥ በባለፉት በርካታ አመታት እንደ ትሬይቮን ማርቲን የመሳሰሉት ታዳጊ ጥቁሮች በነጭ ፖሊሶች መገደል የነጭና የጥቁር ህፃናት አለም የተለያየ ስለመሆኑ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ለኢፍራንም ይህ ሁኔታ በጣም ያስፈራታል፤ ህፃናት ልጆች ወይም ታዳጊዎች እንደ ህፃን በማይታዩበት ሁኔታ ልጅ ማሳደግ ሌላ ገፅታ አለው።
"ልጄ ህፃን እንደመሆኑ መጠን ሌሎችም እንደ ህፃን ያዩታል የሚለው ነገር አይሰራም። እያደገ ነው። ቁመቱም እየረዘመ ነው፤ ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታም ያስፈራኛል። እና ጎረምሳ መምሰሉ ባለው ስርአት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለኔ እንደ ጥቁር እናት የጥቁር ታዳጊዎች ህይወት ከቁብ በማይቆጠርበት አገር ማሳደግም አስፈሪ ነው" ትላለች።
ለታዳጊ ልጇም አሜሪካ እንደ ስርአት ጥቁር ሰዎችን እንደማትወድ፤ ምንም ያላጠፋ ልጅ አንተንም ሊገድሉህ ይችላሉ ብሎ ማስረዳትም ከባድ ነው። ኢፍራን ግን ከልጇ ጋር ይህ ቀላል የማይባለውን ውይይት ማድረግ ይጠበቅባታል።
"ይሄ ደግሞ ሌላ ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነው። ዘረኝነትን መጋፈጥ እንዲሁም ስለ ዘረኝነትም ሆነ የፖሊስ ጭካኔ ከህፃናት ጋር ማውራት በጣም አሳዛኝ ነው። እንደ ወላጅ እነሱን ለመጠበቅ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አለመቻላችንን ስረዳ የካድናቸው ያህል ይሰማኛል። ልጅነታቸውንም ሆነ የልጅነታቸውን ንፅህና መስረቅ ነው። ሌላ ምን አማራጭ አለ ? ለልጄ ስለ ፖሊስ ጭካኔም ሆነ ዘረኝነት ማስረዳት አለብኝ። የ13 ዓመት ልጄን በነጭ ፖሊስ ልትገደል ትችላለህ ማለት ልብን ይሰብራል ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰል አልችልም" በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ልጇ የሚኖርበትን አለም እውነታ ገና በህፃንነቱ መረዳትና ለሚመጣው ነገርም ዝግጁ መሆን ስላለበትም ሁኔታው ቢያስከፋትም ማስረዳት አለባት። ሆኖም ልጇ ጨለምተኛ ሆኖ እንዳያድግና እንዳይገደብም እንደ ወላጅ ሃላፊነት አለባት።
"ልጄ በአለም ላይም ሆነ በሰው ልጅ ላይ ተስፋ እንዲኖረው እፈልጋለሁ። ተስፋ እንዳይቆርጥም ሆነ ያለበትን የዘረኝነት አለም እንዲረዳ አመጣጥኜ ማስረዳት አለብኝ።" ትላለች።
የሰው ልጅ ምንም እንኳን ምርጫ ቢኖረውም ለሷ ግን ስለ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ስለ አሜሪካ አመሰራረት፣ ታሪክ ማስረዳትን መርጣለች።
"በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ያሉ ማህበራዊ ተቋማት እንዲህ አይነት ዘረኝነት እንዲፈፀም ቦታ አላቸው። አንዳንዶች ዘረኝነትን ሲያስቡ እንዲህ የተነጠለ አድርጎ የመቅረፅ ወይም ግለሰቦች መጥፎ ሲሆኑ የሚፈፅሙት አድርጎ የማሰብ ነገር አለ። በአሜሪካ ውስጥ ግን መዋቅራዊ የሆነ ዘረኝነት የሰፈነበት ስርአት ነው። ዘረኝነት ከኃይል ጋር በፅኑ የተቆራኘ ነው። ይሄንን ለ13 አመት ልጅ እንዲረዳ አድርጎ መንገር ቀላል አይደለም። ለአስራ ሶስት አመት ልጅም ጉዳዩ መሆን አልነበረበትም" በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች ።
ልጇም የምትለውን ያዳምጣል " እነዚህ ውይይቶች አሳዛኝ ናቸው። ልጆች ቤተሰቦቻቸው ሲሸበሩ ማየትም እነሱም ላይ ሊጋባ ይችላል፤ ስለዚህ በተቻለ መጠን ሳልጨናነቅ በትንሹ በትንሹ እነግረዋለሁ። ሚዲያ ላይ ስላለው የጥቁር ሰዎች ውክልና፣ የትምህርት ስርአቱ ምን ያህል የጥቁሮችን ታሪክ አካቷል የሚለውን እናወራለን። በተቻለ መጠን በአለም ላይ ተስፋን ማድረግን እንዴት ሰውነታችን፣ አዕምሯችንና መንፈሳችንን እንዴት መንከባከብ እንዳለብን እነግረዋለሁ። በተቻለ መጠን ባንተ ቁጥጥር ውስጥ ያለው ላይ አተኩር እለዋለሁ። በዚህ በዘረኛ ስርአትም ውስጥ ደስተኛ መሆን በራሱ የመቋቋሚያ መንገድ ነው" ብላለች ኢፍራን ለቢቢሲ።












