በአሜሪካ እየተበራከተ የመጣው የፖሊስ ጭካኔ እና የተገደሉ ጥቁሮች

George Floyd

የፎቶው ባለመብት, Twitter/Ruth Richardson

የምስሉ መግለጫ, ጆርጅ ፍሎይድ

ባሳለፍነው ሰኞ አንድ ነጭ የፖሊስ መኮንን አንድ ጥቁር አሜሪካዊን በጉልበቱ አንገቱ ላይ ቆሞ ሲያሰቃየው ከቆየ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ በአሜሪካ ዘርን መሰረት ያደረገ የፖሊስ ጭካኔ ጉዳይ ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል።

ሟች የ46 ዓመት ጎልማሳ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ሲሆን በሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ጥርጣሬ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሊያውለው እንደመጣ ተጠቅሷል።

ለአስር ደቂቃ በሚዘልቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ፣ ነጭ ፖሊስ የዚህን ጥቁር አሜሪካዊ አንገት በጉልበቱ ተጭኖት እያለ በጉልህ የሚታይ ሲሆን ተጠርጣሪው በበኩሉ ‹‹መተንፈስ አልቻልኩም እባክህን አትግደለኝ›› እያለ ሲማጸነው ይሰማል፡፡

በዛኑ ቀን ደግሞ አንዲት ነጭ ሴት ኒው ዮርክ በሚገኝ ፓርክ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ለምን ውሻሽን አታስሪውም አለኝ በማለት ለፖሊስ ደውላ ነበር።

"አንድ ጥቁር ሰው እኔ እና ውሻዬ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየዛተ ነው ድረሱልኝ" በማለት ለፖሊስ ደውላለች። ጉዳዩ ሲጣራ ግን ሴትዮዋ የፓርኩን ህግ በመተላለፍ ውሻዋን በመልቀቋ ነበር ጥቁር አሜሪካዊው ውሻሽን እሰሪው ያላት።

አሜሪካ ውስጥ በጎርጎሳውያኑ 2019 ብቻ ከ1 ሺ በላይ ሰዎች በፖሊስ ተተኩሶባቸው ሕይታቸው አልፏል።

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በአሜሪካ ላለው አስፈሪ የፖሊስ ጭካኔ ማሳያ ነው ተብሏል።

ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ይዞት በወጣው መረጃ መሰረት በ2019፣ 1014 ሰዎች በፖሊስ ተተኩሶባቸው የሞቱ ሲሆን ከነዚህ መካከል ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው።

አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት በሰራው ጥናት መሰረት ደግሞ ጥቁር አሜሪካውያን ከነጭ አሜሪካውያን ጋር ሲነጻጸር በፖሊስ የመገደል እድላቸው በሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።

የፖሊስ ጭካኔ እንደ ‘ብላክላይቭስማተር’ የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ አድርጓል። ታዋቂዋ ዘፋኝ ቢዮንሴ እና ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሌብሮን ጄምስ ይህንን እንቅስቃሴ በይፋ ደግፈዋል።

እስካሁን ድረስ በአሜሪካ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሱ ተመሳሳይ የፖሊስ ጭካኔዎችን እንመልከት።

ትሬይቮን ማርቲን፡ የካቲት 2012

የ 17 ዓመቱ ትሬይቮን ማርቲን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነበር። ሳንፎርድ ፍሎሪዳ ውስጥ ነበር ጆርጅ ዚምርማን በተባለ የጥበቃ አባል ተተኩሶበት ሕይወቱ ያለፈችው።

ማርቲን ዘመዶቹን ለመጠየቅ ጥበቃ ወደሚደረግለት አንድ መንደር ያቀናል፤ በዚህም ወቅት ነበር የስፓኒሽ ዘር ያለው ፈቃደኛ የአካባቢው ጠባቂ ጋር የተገናኘው።

በወቅቱ ጆርጅ ዚመርማን በፍርድ ቤት ጥፋተኛ አይደለም ተባለ። ምንም እንኳን በአሜሪካ ሕግ መሰረት ጠባቂው የ 17 ዓመቱን ታዳጊ ራሴን ለመከላከል ነው በማለት መግደሉን እንደ ወንጀል ባያየውም የማርቲን ቤተሰቦችና ጓደኞቹ ግን የግድያ ወንጀል ነው የተፈጸመው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ነበር ‘ብላክላይቭስማተር’ የሚባለው ማህበራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው።

ኤሪክ ጋርነር፡ ሰኔ 2014

ኤሪክ ጋርነር በወቅቱ ትንባሆ በሕገ ወጥ መንገድ በመሸጥ ተጠርጥሮ ነበር በፖሊስ የተያዘው። ኤሪክ በፖሊስ አንገቱ ተቆልፎ ‹‹እባካችሁ መተንፈስ አልቻኩም›› እያለ በተመሳሳይ ሁኔታ ነበር የሞተው፡፡

ለኤሪክ ሞት ተጠያቂ የነበረው ነጭ የፖሊስ አባል ዳንኤል ፓንታልዮ ከሥራው የተባረረው ከክስተቱ አምስት ዓመታትን ቆይቶ መሆኑ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል፡፡

ጆርጅ ፍሎይድ መሬት ላይ ወድ

የፎቶው ባለመብት, Darnella Frazier

ማይክል ብራውን፡ ነሀሴ 2014

የ 18 ዓመቱ ማይክል ብራውን ዳረን ዊልስን በተባለ ፖሊስ አባል ተተኩሶበት መሞቱን ተከትሎ ደግሞ ‘ብላክላይቭስማተር’ የሚባለው እንቅስቃሴ ከአሜሪካ አልፎ ዓለማቀፍ ተቀባይነትን እንዲያገኝ አድርጓል።

ሚሱሪ ፈርጉሰን ውስጥ በተፈጠረው ይህ ክስተት ምክንያት ከባድ አመጽ ተነስቶ የነበረ ሲሆን አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

ዋልተር ስኮት፡ ሚያዝያ 2015

ዋልተር ስኮት የ 50 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን በሳውዝ ካሮላይና ከፖሊስ ለማምለጥ ሲሞክር ሶስት ጊዜ በጥይት ተመትቶ ነው ሕይወቱ ያለፈችው።

የፖሊስ አባሉ ዋልተር ስኮትን ለማስቆም የሞከረው የመኪናው ፍሬቻ መብራት በመሰበሩ ነበር። በወቅቱ ዋልተር ለልጁ የሚቆርጠውን ወርሀዊ ድጋፍ ባለመክፈሉ በፖሊስ ይፈለግም ነበር።

ስላገር የተባለው የፖሊስ አባል ዋልተር ስኮትን በመግደል ወንጀል ተከሶ 2017 ላይ የ 20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል። የዋልተር ቤተሰቦችም የ 6.5 ሚሊየን ዶላር ካሳ ተከፍሏቸዋል።

ፍሬዲ ግሬይ፡ ሚያዝያ 2015

ዋልተር ስኮት በፖሊስ ተተኩሶበት ከሞተ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ባልቲሞር ሜሪላንድ ውስጥ ደግሞ ሌላ ቁጣን የቀሰቀሰ የፖሊስ ጭካኔ ተመዝግቧል።

ፍሬዲ ግሬይ የ 25 ዓመት ወጣት ሲሆን በኪሱ ውስጥ የስለት መሳሪያ ይዞ በመገኘቱ ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው።

በቦታው የነበረ የአይን እማኝ በቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ፍሬዲ እየጮኸ ፖሊሶች ተሸክመው መኪናቸው ውስጥ ሲያስገቡት ይታያል።

ከጥቂት ሰአታት በኋላ ፍሬዲ የአከርካሪ አጥንት ችግር አጋጥሞታል ተብሎ ሆስፒታል ገባ። ከሳምንት በኋላ ግን ሕይወቱ አለፈች። ይህ ተከትሎ በተቀሰቀሰ ቁጣም ዜጎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው 20 ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።

ከፍሬዲ ሞት ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ስድስቱ የፖሊስ አባለት ግን ጥፋተኛ አይደሉም ተብለው በነጻ ተሰናብተዋል።

ፊላንዶ ካስቲል፡ ነሀሴ 2016

ፊላንዶ ካስቲል ሚኒሶታ ውስጥ ጀሮሚኖ ኣኔዝ በሚባል የፖሊስ አባል ነው ተተኩሶበት ህይወቱ ያለፈችው።

በወቅቱ የተፈጠረውን ነገር የፊላንዶ የፍቅር ጓደኛ በስልኳ አማካይነት በቀጥታ አስተላልፋው ነበር። ምንም እንኳን የፖሊስ አባሉ ፍርድ ቤት ቢቀርብም አንድ ዓመት ከፈጀ የፍርድ ሂደት በኋላ በነጻ ተሰናብቷል።

• ቦታም ጂን፡ መስከረም 2018

የ 26 ዓመቱ ቦታም ጂን፣ አምበር ጋይገር በምትባል የፖሊስ አባል ነበር በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ተተኩሶበት ህይወቱ ያለፈችው። በወቅቱ የፖሊስ አባሏ ቤቷ የገባች መስሏት በሂሳብ ስራ የሚተዳደረው ቦታም ጂን ቤት በስህተት ትገባለች።

ልክ ስመለከተው ቤቴን ሊዘርፍ የገባ መስሎኝ ተኮስኩበት ብላለች። ከአንድ ዓመት በኋላም አምበር በወንጀሉ ጥፋተኛ በመባሏ የ 10 ዓመት እስር ተፈርዶባታል።

• አትላንታ ጄፈርሰን፡ ጥቅምት 2019

የ28 ዓመቷ አትላንታ፣ የህክምና ተማሪ የነበረች ሲሆን ዳላስ ውስጥ በመኝታ ክፍሏ ሳለች ነበር አሮን ዲን በተባለ የፖሊስ አባል የተደገለቸው።

የፖሊስ አባሉ ከጎረቤት የአትላንታ የሳሎን በር ክፍት ነው የሚል ጥቆማ ደርሶት ነበር የመጣው። በመቀጠልም በመኝታ ቤቷ መስኮት በኩል ተኩሶ ገድሏታል።

በግድያ ወንጀል ክስ ቢቀርብትም እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረበም።

ብሪዮና ታይለር

የፎቶው ባለመብት, Facebook

• ብሪዮና ታይለር፡ መጋቢት 2020

የ 26 ዓመቷ ብሪዮና ታይለር የድንገተኛ ህክምና ባለሙያ ነበረች። ኬንታኪ ውስጥ ፖሊሶች ወደ መኖሪያ ቤቷ ሲገቡ በተፈጠረ ጭቅጭቅ ወቅት ስምንት ጊዜ በጥይት ተመትታ ነው ህይወቷ ያለፈው።

ፖሊሶቹ በወቅቱ ዕጽ በቤቷ አለ በማለት ነበር የሄዱት። ነገር ግን በብሪዮና ቤት ውስጥ ምንም አይነት ዕጽ አልተገኘም ነበር።

ፖሊስ በበኩሉ አንድ የፖሊስ አባል በጥይት በመመታቱ ነው ተኩስ የተከፈተው ብሏል።