መንግሥት ከምዕራብ ኦሮሚያ ለሚሰማው እሮሮ ተጠያቂው "ሸኔ ነው" አለ

በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ተገደለች ተባለችው አምሳሉ ጉደታ

የፎቶው ባለመብት, ከማህበራዊ ሚደያ

የምስሉ መግለጫ, በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ተገደለች ተባለችው አምሳሉ ጉደታ

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አራት ዞኖች በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ 'በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ግድያዎች እየተፈጸሙ ነው' የሚሉ ተደጋጋሚ እሮሮዎች ከነዋሪዎች ይሰማል።

ከእነዚህ መካከል በምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሰቢ ወረዳ ኬሌዬ ቢርቢር በምትሰኝ ቀበሌ ውስጥ ተገደሉ የተባሉት የአራት ልጆች እናት ይገኙበታል።

ወ/ሮ አምሳሉ ጉደታ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ ሐሙስ ግንቦት 13 2012 በእርሻ ሥራቸው ላይ ሳሉ በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ባለቤታቸው አቶ ሚረቴ ኢማና ይናገራሉ።

"ጥላብኝ የሄደችው ህጻናት 'እናታችን መቼ ነው የምትመጣው' እያሉ ይጨቀጭቁኛል" ይላሉ አቶ ሚረቴ ኢማና።

በተመሳሳይ መልኩ በምዕራብ ወለጋ ዞን የገንጂ ወረዳ ነዋሪ የነበረው ወጣት ለሊሳ ተፈሪ ከሁለት ሳምንት በፊት በአካባቢው ተሰማርቶ በሚገኘው የመንግሥት ኃይል በቁጥጥር ሥር ከዋለ ከሁለት ቀናት በኋላ ሞቶ መገኘቱን ቤተሰቦቻቸውን አነጋግረን መዘገባችን ይታወሳል።

የወጣቱ እናት ወ/ሮ ጫልቱ ሁንዴሳ ልጃቸው ታስሯል ወደተባለበት ስንቅ ይዘው ሄደው "የልጄ አስክሬን በሸራ ተጠቅልሎ ሜዳ ላይ ተጥሎ አገኘሁ። የልጄን ሞት እዚያው ተረዳሁ" በማለት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በአከባቢው 'የሸኔ አባላት ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም ደጋፊ ናቸው" የሚባሉ ሰዎች ለእስር እየተዳረጉም እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በጉዳዮ ዙሪያ ምላሽ እና ማብራሪያ ለማግኘት የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አጥጋቢ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን በቀደመ ዘገባችን ተጠቁሟል።

'መነሻው ሸኔ ነው'

ቢቢሲ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን በስልክ አግኝቶ ማነጋገር ችሎ ነበር።

የቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል ሞሐመድ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ላይ የሚቀርበው አቤቱታ ሐሰት ነው። ይህ ክስ መሠረተ ቢስ ነው ይላሉ።

"ጸረ-ሰላም ኃይሎች ራሳቸው ገድለው መንግሥት ላይ ማሳበባቸው የተለመደ ነው" ያሉት አቶ ጅብሪል፤ "እኛ ሰላማዊ ዜጋ ገድለን አናውቅም፤ የጸጥታ መዋቅሩም ሰላማዊ ሰው አይገድልም። ለሚሞቱ ሰዎች መነሻውም መጨረሻውም ሸኔ ነው" ይላሉ።

የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው ለግድያዎቹ ሸኔን ተጠያቂ የሚያደርጉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ "የመጀመሪያው መንግሥት እና ህዝብ የሰጣቸውን ሰላማዊ ትግል 'አንቀበልም' በማለት የደህንነት ችግር ፈጥረዋል። ሁለተኛው ደግሞ ህዝብ ወደ ሚኖርበት ገብተው፣ ህዝብ መካከል ሆነው ወደ ጸጥታ አስከባሪዎች ይተኩሳሉ" ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ንጹሃን ዜጎች እየተጎዱ መሆኑን ጨመረው ያስረዳሉ።

አቶ ጅብሪል ለግድያዎቹ ሸኔ ተጠያቂ ስለመሆኑ የሚያቀርቡት ሌላኛው መከራከሪያ፤ በዚህ ሁኔታ ንጹሃን ዜጎች ሲጎዱ የመንግሥት ኃይል ሰው ገደለ ብለው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይለጥፋሉ፤ አባላቶቻቸው ሲገደሉም 'ንጽህ ዜጋ በመንግሥት ኃይል ተገደለ' ይላሉ"።

አቶ ጅብሪል በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ንጹሃን ዜጎች እየተጎዱ እንደሆነ ያረጋገጣሉ።

"ከዚህ ቀደም እኔ በነበርኩበት ቦታ ተኩስ ከፍተው፤ የሸኔ ኃይል እየተንቀሳቀስ እያየን፤ ህጻናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶች መካከል በመግባታቸው መምታት እየቻልን፤ ተኩስ እንዲቆም አስደርጊያለሁ" ይላሉ አቶ ጅብሪል።

ባለቤታቸው የተገደለችባቸው አቶ ሚረቴ ከአራት ልጆቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ, ባለቤታቸው የተገደለችባቸው አቶ ሚረቴ ከአራት ልጆቻቸው ጋር

የአራት ልጆች እናት እንዴት ተገደሉ?

አቶ ሚረቴ እንደሚሉት ባለቤታቸው የበቆሎ ማሳ ውስጥ እያለች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ህይወታቸው አልፏል።

"የአንድ ዓመት ህጻን የእናቷ አስክሬን አጠገብ ቁጭ ብላ እንዳለች ነው የባለቤቴን አስክሬን ያነሳሁት" በማለት በሃዘን ተውጠው ይናገራሉ።

ባለቤታቸው በጥይት ተመትታ ስትገደል በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተመልክተዋል ይላሉ አቶ ሚረቴ። አቶ ሚረቴ እንደሚሉት ከሆነ ከባለቤታቸው ግድያ አንድ ሳምንት በፊት፤ እርሳቸውም በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ድብደባ ተፈጽሞባዋል።

"ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ 'ሸኔ ያለበትን ቦታ ታውቃለህ' ብለው እጄን ወደኋላ አስረው በድብደባ ሰባብረውኝ በቤት ውስጥ አስቀርተውኛል" ይላሉ።

በደረሰባቸው ድብዳበ ከቤት ወጥቶ ሥራ መስራት አዳግቷቸው እንደነበረ እና ቤተሰቡ በሙሉ በባለቤታቸው ትከሻ ላይ ወድቆ እንደነበረ ይናገራሉ።

"ትናንት በጉልበቴ ሰርቼ ቤተሰቤን አስተዳድር ነበር። አሁን ተሰብሬ ቤት ተቀምጬ ባለሁበት ወቅት የምትረዳኝን የልጆቼን እናት ነጠቁኝ" ይላሉ።ከዚህ ቀደም በአካባቢው በመንግሥት እና ታጣቂዎች መካከል ግጭት ይከሰት እንደነበረ አስታውቀው፤ ባለቤታቸው በተገደለችበት ወቅት ግን በአካባቢያቸው ምንም አይነት ግጭት እንዳልነበረ ተናግረዋል።

"እሷ ለመግደል ታስቦ ነው የተተኮሰባት" ይላሉ።

በባለቤታቸው ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘም ሆነ የባለቤታቸውን ግድያ ለመመርመር የመጣ የመንግሥት አካል እንደሌለ አቶ ሚረቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።