በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ቢያንስ 55 ዜጎቿ መገደላቸውን ጋና አረጋገጠች

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ እና የጋና አቻቸው ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ በጦርነቱ ለተገደሉት ሰዎች ያላቸውን ክብር ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Ghana's Foreign Affairs Ministry/Facebook

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ እና የጋና አቻቸው ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ በጦርነቱ ለተገደሉት ሰዎች ያላቸውን ክብር ሲገልጹ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ቢያንስ 55 ጋናውያን መገደላቸውን እና በአሁኑ ወቅት ሁለት ጋናውያን የጦር እስረኛ ሆነው መያዛቸውን የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ ወደ ኪየቭ ተጉዘው የዩክሬን ባለሥልጣናትን ማናገራቸውን በመጥቀስ ከ2022 ጀምሮ ወደ 272 የሚጠጉ ጋናውያን ወደ ጦርነቱ መግባታቸው ይታመናል ብለዋል።

አብላክዋ ቁጥሮቹን "አሳዛኝ እና አስፈሪ" ሲሉ የገለፁት ሲሆን፣ ጋና "እነዚህን ልብ የሚሰብሩ መረጃዎች እንዳላየች ማለፍ አትችልም" ብለዋል።

ጋናውያን በማን ወገን ተሰልፈው እየተዋጉ እንደሆነ ባይገልጹም፣ ረቡዕ ዕለት የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ከ36 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ1,700 በላይ ሰዎች ለሩሲያ እንዲዋጉ ተመልምለዋል።

በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ከተሳተፉ አፍሪካውያን መካከል 55 ጋናውያን መሞታቸው በይፋ የተረጋገጠ ከፍተኛ ቁጥር ነው።

በካሜሩን የሚገኙ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በግጭቱ 94 የሚሆኑ ዜጎች መሞታቸውን ቢዘግቡም፤ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።

ሁለት ደቡብ አፍሪካውያን እና ቢያንስ አንድ ኬንያዊ በጦርነቱ ሞተዋል።

የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሟቾች አሃዝ "ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን ሕይወት፣ የብዙ የጋና ቤተሰቦችን እና የአገራችንን ተስፋ የሚወክል ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጋና መንግሥት "ሁሉንም በስውር እና በሕገወጥ የሚካሄዱ የቅጥር ሁኔታዎችን ለመከታተልና ለማስወገድ" እንዲሁም የአገሪቱ ወጣቶች ወደ ጦርነቱ እንዳይሳቡ ለመከላከል የተጠናከረ የሕዝብ ግንዛቤ መስጫ ዘመቻዎችን ለመጀመር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

"ይህ የእኛ ጦርነት አይደለም፤ ወጣቶቻችንም ለሌሎች ደጀን እንዲሆኑ መፍቀድ አንችልም" ሲሉ ተናግረዋል።

ሐሙስ ዕለት አንድ የኬንያ ዜጋ ወጣቶችን በስራ ዕድል ስም ወደ ሩሲያ እንዲሄዱ አግባብቶ በዩክሬን ውጊያ ውስጥ እንዲሳተፉ ምክንያት ሆኗል በሚል ተከሷል። ፌስተስ አራሳ ኦምዋምባ ግን ክሱን ውድቅ አድርጓል።

ባለፈው ሳምንት የኬንያ ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ላለፉት አራት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በአጠቃላይ 1,000 ኬንያውያን ሩሲያን ወግነው እንዲዋጉ ተመልምለዋል።

በኬንያ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በጦርነቱ ውስጥ እንዲዋጉ ሰዎችን በመመልመል ላይ ተሳትፏል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጓል።

ይሁን እንጂ የሩሲያ ሕግ በአገሪቱ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚገኙ የውጭ ዜጎች በፈቃደኝነት በጦሩ ውስጥ ተመልምለው እንዲሳተፉ እንደሚፈቅድ ገልጿል።

ረቡዕ ዕለት የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ለሩሲያ ሲዋጉ የተያዙ ሁለት የጋና ዜጎችን እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

"የማጭበርበር፣ የተዛባ መረጃ፣ የተሳሳተ መረጃ፣ የወንጀል ዝውውር መረብ ሰለባዎች ናቸው" ብለዋል።

እስረኞቹን አያያዝ ላይ ዓለም አቀፍ ሕግ መከበሩን በመጥቀስ ዩክሬንን አመስግነዋል።

"በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የሚገልጹ መረጃዎች ደርሰውናል" ብለዋል። "ማሰቃየት አልተፈፀመባቸውም። ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ኢሰብአዊ ድርጊት አልተፈጸመባቸውም።"

የአንደኛው እስረኛ ቤተሰብ በቅርቡ እንደሚፈታ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

እንደ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ የ35 ዓመቱ ጆሹዋ ንክሩማህ ነፍሰ ጡር ሚስቱን በሐምሌ 2024 በዱባይ ትቶ የግል የደኅንነት ሥራ እንዳገኘ በማመን ወደ ሩሲያ ተጉዟል።

በመስከረም 2024 ከድሮን ጥቃት ተርፎ በዩክሬን ጦር ተይዟል። ንክሩማህ አሁንም በእስር ላይ ሲሆን፣ ቤተሰቡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእርሱ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም።

የጆሹዋ አባት አልበርት ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ዘወትር ልጃቸው በሕይወት ስለመኖሩ አልያም ስለመሞቱ ያስቡ ነበር።

"እንደ አባት፣ በየቀኑ ሐዘን ተሸክሜ እኖራለሁ። ከእንቅልፌ ስነቃ መጀመሪያው የማስበው ነገር ልጄን ነው - በልቶ እንደሆነ፣ ደህና እንደሆነ፣ አሁንም ተስፋ ይኖረው እንደሆነ" በማለት ተናግረዋል።

"ልጄ በሕይወት ወደ ቤቱ እንዲመመለስ ብቻ ነው የምፈልገው። አንድ አባት የሚጠይቀው ይህን ብቻ ነው።"

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢጋ እንዳሉት ሁለቱም ወገኖች እስረኞቹን ወደ ጋና የመመለስ ዕድል ስለመኖሩ "በግልጽ" ተወያይተዋል።

ደቡብ አፍሪካ ሐሙስ ዕለት ሁለት ዜጎቿ በዩክሬን መገደላቸውን፣ ሌሎች 15 ደግሞ ባለፈው ሳምንት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስታውቃለች።

ሁለት ተጨማሪ ዜጎቿ ሩሲያ ውስጥ "በጣም ከባድ" ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ ተናግረዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ለሩሲያ የሚዋጋ ማንኛውም ሰው እንደ ጠላት ተዋጊ እንደሚቆጠር እና ብቸኛው አስተማማኝ መንገድ እጅ መስጠት እና እንደ ጦር ምርኮኛ መቆጠር እንደሆነ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

ዩክሬን ከዚህ በፊት አፍሪካውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጎችን ከጎኗ እንዲሰለፉ ለመመልመል በመሞከር ትችት ደርሶባታል።