የደቡብ ኮሪያ እና የሰሜን ኮሪያ የብሽሽቅ ፊኛዎች ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሜን ኮሪያ ሸሽተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚሻገሩ ሰዎች በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ፊኛዎችን ወደ አገራቸው ሰሜን ኮሪያ ይልካሉ። ይህንን የሚያደርጉትም ከደቡብ ኮሪያ የድንበር ከተማ ሆነው ነው።
ሰሜን ኮሪያን የሸሹት ብቻም ሳይሆን የደቡብ ኮርያ መብት ተሟጋቾች ጭምር በርካታ መልዕክት የያዙ ረዣዥም ፊኛዎችን ወደ ጎረቤታቸው ይልካሉ።
በፊኛዎቹ ውስጥ የሚጠቀለሉት መልዕክቶች በአመዛኙ ሰሜን ኮሪያ ዜጎቿን በጭቆና አረንቋ ማኖሯን እንድትተው የሚወተውቱ ናቸው። አንዳንዶቹ መልዕክቶች ደግሞ የብሽሽቅ ይዘት ያላቸው ናቸው።
"እኔ ደቡብ ኮሪያዊ ነኝ፤ የኪም ቤተሰብ አይደለሁም፤ ለኪም ባሪያ አይደለሁም፤ ነጻ ዜጋ ሆኛለሁ" የሚሉ መልዕክቶች ይገኙበታል።
ይህ በፊኛ የብሽሽቅ መልዕክት ጠቅልሎ ወደ ጎረቤት አገር በንፋስ ኃይል የማሻገሩ ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰሜን ኮሪያን እያስቆጣት መጥቷል።
በእርግጥ ድርጊቱ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ሰሜን ኮሪያ ግን እንደ አሁኑ ተበሳጭታ አታውቅም።
በእነዚህ ፊኛዎች ውስጥ ብሽሽቅ ይኑርባቸው እንጂ የፍቅር ደብዳቤዎችን ጨምሮ ቼኮሌቶችና አንዳንድ ጊዜም ዶላሮች በፊኛው ውስጥ ተደርገው ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዲበሩ ይደረጋሉ።
በተለይም መብት ላይ የሚሰሩ ደቡብ ኮሪያዊያን በየዓመቱ ይህንን ማድረግ ባሕልና አንድ የትግል መሣሪያ አድርገውት ቆይተዋል።
በ2014 እንዲያውም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እነዚህን ፊኛዎች በመሳሪያ ተኩሰው ለመጣል በመሞከራቸው በድንበር አካባቢ መጠነኛ የተኩስ ልውውጥ እንዲፈጠር አድርጓል።
አሁን ግን የሰሜን ኮሪያ ቁጣ እየገነፈለ በመምጣቱ ደቡብ ኮሪያ ነገሩን ለማጤን ተገዳለች።
ሰሜን ኮሪያም በበኩሏ ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ይሄን "ጅላጅል ድርጊት" እንድታቆም የሚጠይቅ የመልስ ፊኛ ልካ ታውቃለች።
የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት እህት ኪም ኦን ጁንግ ባለፈው ሐሙስ ከሰሜን የሚበሩ ፊኛዎች አስቆጥተዋት ረዥም መግለጫ ማውጣቷ ተሰምቷል። ይህም በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ተነቧል።

የፎቶው ባለመብት, AFP / Getty
የሴትዮዋ ቁጣ የመነጨው ከአገሯ የከዱ ዜጎች ከደቡብ ኮሪያ ድንበር ሆነው በፊኛ የላኳቸው ፖስት ካርዶችና በራሪ ወረቀቶች ናቸው።
ኪም ኦን ጁንግ "እነዚህ የሰው አይጠመጎጦች" ስትል ነው የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለማንኳሰስ የሞከረችው።
በሰሜን ኮሪያ ፓርቲ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ሥልጣን አላት የምትባለው ኪም ኦን ጁንግ "እነዚህን የሰው አይጠ መጎጦች የለቀቀብን ኃይል ደግሞ ሊጠይቅ ይገባል" ብላለች። ይህም ደቡብ ኮሪያ መንግሥትን የሚመለከት ተደርጎ ተተርጉሟል።
ይሄ ፊኛ የመላኩን ነገር ደቡብ ኮሪያዊያን ካላቆሙት የጋራ ድንበር የሰላም ስምምነቱን ጨምሮ በጋራ የተፈጠረው የካሶንግ ኢንደስትሪ ፓርክ ስምምነትን ልታፈርስ እንደምትችል ዝታለች።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ይህ የሰሜን ኮሪያ ዛቻ ያስፈራው ይመስላል። ፊኛ የመላኩንደ ድርጊት በሕግ ለማስቆም እያሰበ ይገኛል። ሆኖም በዛቻው ተደናግጦ ለዚህ ውሳኔ እንደበቃ አላመነም።
"ለነገሩ እነዚህ ፊኛዎችና የሚይዙት መልዕክት አንዳንድ ጊዜ በእኛ መሬት ላይ ስለሚቀር አካባቢን እየበከለብን ነው። እሱን ማስወገድ በራሱ ትልቅ ሥራ ነው የሆነብን" ሲል ነገሩን ለማቆም እንደሚገደድ ጠቁሟል።
ፊኛ ላኪዎቹ ግን በደቡብ ኮሪያ መንግሥት የአቋም ለውጥ ያፈሩ ይመስላል።
"የፈለገ ነገር ቢመጣ ይህንን ነገር በፍጹም አናቆምም። እንዲያውም አንድ ሚሊዮን ፖስት ካርዶችና በራሪ ወረቀቶችን አዘጋጅተናል። ፊኛዎቹን ወደ ሰሜን ኮሪያ መላኩን አጠናክረን እንቀጥልበታለን" ብለዋል።
ከሰሜን ኮሪያ ነጻ የወጡ አርበኞች ግንባር ኃላፊ ፓርክ ሳንግ ባለፈው ዓመት ብቻ ማኅበራቸው 11 ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ፊኛዎችን ወደ ሰሜን ኮሪያ መላኩን ተናግሯል።
"ይህ ሰሜን ኮሪያ አይደለም። ይህ ደቡብ ኮሪያ ነው፤ በደቡብ ኮሪያ ዜጎች ሦስት መብቶች አሏቸው። ከእነዚህ አንዱ የመናገር ነጻነት ነው" ሲል የአርበኞቹ ግንባር በድርጊቱ እንደሚገፉበት ዝቷል።
ኃላፊው "ፊኛዎችን ወደ ሰሜን ኮሪያ መላክ ከተከለከልን ቀጥሎ የምንልከው ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን ይሆናል" ሲል ዝቷል።
ፓርክ የሚመራው በደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያ አርበኞች ግንባር 40 ሺህ ከሰሜን ኮሪያ የኮበለሉ አባላትን ይዟል።













