የትኞቹ ሃገራት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነት አላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮሪያ ከተቀረው ዓለም ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሌላት ተደርጎ ቢሳልም 50 ከሚደርሱ ሃገራት ጋር ግንኙነት መፍጠር ችላለች። እነዚህ ሃገራት ትኞቹ ናቸው? ግንኙነታቸውስ ምን ይመስላል?
ሰሜን ኮሪያ ከሃገራት ጋር ያላት ግንኙነት መሻከር በየቀኑ እየጨመረ ይገኛል።
ከሃገራት ጋር ያላት መራራቅ ግልጽ ቢሆንም በሚገርም መልኩ ሰፋ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላት።
ሰሜን ኮሪያ ከተመሰረተችበት እ.አ.አ 1948 ወዲህ ከ160 ከሚበልጡ ሃገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረች ሲሆን በ 55 ሃገራት ኤምባሲዎች ሲኖሯት በ48 ሃገራት ደግሞ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች አሏት።
ከእነዚህ መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ አዲስ አበባ ውስጥ ቢኖራትም ኢትዮጵያ ግን ፒዮንግያንግ ውስጥ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ የላትም። በዚህም ሰሜን ኮሪያ አፍሪካ ውስጥ ካሏት ጥቂት ኤምባሲዎች መካከል የአዲስ አበባው አንዱ ነው።
እንደ ሎውይ ኢንስቲትዩት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚያሳየው ካርታ ከሆነ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና ስዊዲንን ጨምሮ አነስተኛ ቢሆኑም በአጠቃላይ 25 የሚደርሱ ሃገራት ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያደርጉበት ጽህፈት ቤት አላቸው።
በይፋ የኮሪያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያ ሪፐብሊክ ተብላ ከምትታወቀው ሃገር ተለይታ ስትመሰረት ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፈጠሩ ሃገራት መካከል ኮሙኒስት የሆኑት ጎረቤቶቿ ቻይና እና ሩሲያ ይገኙበታል።
አሜሪካ ከፒዮንግያንግ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይዋ ኒኪ ሃሊ በኩል "ሁሉም ሃገራት ግንኙነታቸው ያቋርጡ" ስትል ግፊት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ከእነዚህ መካከልም ስፔን፣ ኩዌት፣ ፔሩ፣ ሜክሲኮ፣ ጣሊያን እና ምያንማር አምባሳደሮቻቸውን ወይንም ዲፕሎማቶቻቸውን አስወጥተዋል።

ፖርቹጋል፣ ኡጋንዳ፣ ሲንጋፖር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ፊሊፒንስ ደግሞ ግንኙነታቸውን ያገዱ ወይም ያቆሙ ሃገራት ናቸው።
ሆኖም በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙዎቹ የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ መልዕክተኞች እና ያስተናገዷቸው ሃገራት ለሥራ ክፍት ናቸው።
እንደውም አንዳንድ ሃገራት ያላቸውን ግንኙነት በማሳደግ ላይ ናቸው። በተለይም ደግሞ ፒዮንግያንግ የግንባታ ፕሮጀክት በምታካሂድባቸው የአፍሪካ ሃገራት እና በሃይል እና ግብርና ዙሪያ ንግግር በማድረግ ላይ ከምትገኝባቸው ሃገራት ጋር።
ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግን በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል።
ወቀሳና ጥርጣሬ
ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለቤት ሃገራት ስብስብ የሆነው ኢኮኖሚክ ኮኦፕሬሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት የተባለ ድርጅት ካቀፋቸው 35 ሃገራት መካከል 6ቱ ብቻ ናቸው ከፒዮንግያንግ ጋር ግንኙነት ያላቸው።
አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፈጥራ የማታውቅ ሲሆን ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያም ተመሳሳይ ናቸው።
ስለዚህ አሜሪካ እና ሌሎች የኤስያ ቅርብ አጋሮቿ ከፒዮንግያንግ መረጃ ለማግኘት በሌሎች ሃገራት ላይ መመርኮዝ ግድ ይላቸዋል።
ከእነዚህ ሃገራት መካከል ደግሞ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ስዊዲን ሲገኙበት በሀገሪቱ የሚገኙ አምባሳደሮቻቸውን ለመጥራትም ሆነ በዋና ከተማቸው የሚገኘውን የሰሜን ኮሪያ መልዕክተኛ ቢሮ ለመዝጋት ምንም እንቅስቀሴ አላደረጉም።
ሰሜን ኮሪያ በኤስያ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ያሏት መልዕክተኞች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሁለትዮሽ ማዕቀብን በማለፍ ገቢ በማስገኘት በኩል ወሳኝ ናቸው።
ኤምባሲዎቹ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ሲሆን ስውር ለሆነ ተግባርም ይውላሉ የሚለው ክስም በስፋት ይሰማል።
የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲዎች ያሉባቸው አውሮፓ ሃገራት የኤምባሲውን ህንጻ ለንግድ ሥራ በህገ-ወጥ መንገድ ይከራያሉ ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ።
በታሪክ ለፒዮንግያንግ ጥሩ ናት የምትባለው ፓኪስታን ውስጥ የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት መኖሪያ ቤት መዘረፉ የታቀደበት ሊሆን ይችላል ተብሎ ብዙ ጥርጣሬዎችን ፈጥሮ ነበር።
በሁለቱም ሃገራት መካከል ያሉ ደህንነቶች የሃገራቱን ባለስልጣናት በጥርጣሬ ነው የሚመለከቷቸው።
ዲፕሎማቶችን በቁራኛ የሚከታተሉ ሲሆን በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ላይም ከፍተኛ የጉዞ እገዳ ይደረግባቸዋል።
ሊሸሹ ይችላሉ በሚል ሰሜን ኮሪያ በራሷ ዲፕሎማቶች ላይም ተጨማሪ ከፍተኛ ስለላ ታከናውናለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የርዕዮተ-ዓለም ወዳጅነት
ይህ ሁሉ ችግር መኖሩ ሲታይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ምን ያስገኛል የሚለው ጥያቄ ይነሳል።
እንደ ኩባ፣ ቬንዙዌላ እና ላኦስ ላሉት ኮሚኒስት ወይም ሶሻሊስት ሃገራት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሁለትዮሽ የርዕዮተ-ዓለም ድጋፍ እንዲኖራቸው ያግዛል።
አሁን አሁን ግን ይህን መሠሉ ግንኙነት የርዕዮተ-ዓለም ድጋፍ ከመለዋወጥ ባለፈ እንደሶሪያ እና ኢራን ላሉ ሃገራት ደግሞ በጋራ ባላቸው ጸረ-አሜሪካ ሃሳብ ላይ የተመሠረተ ነው።
በየትም ሃገር ቢመደቡ የፒዮንግያንግ ዲፕሎማቶች ለመንግሥታቸው ድጋፍ መጨመር እና 'የጠላትን' ሃሳብ ማክሸፍ ሥራቸው ነው።
እንደ ጀርመን ያሉና ከፒዮንግያንግ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲቀጥል የሚፈልጉ ምዕራባዊ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ለንግግር መንገድ የሚከፍት እንደሆነ እና ለኮሪያ ችግር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው።
ከዚህ የበለጠም አገልግሎት ይሰጣሉ። ለምሳሌ የስዊዲን ዲፕሎማቶች እ.አ.አ በ2016 ፒዮንግያንግ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረውን እና ወደ ሃገሩ እንደተመለሰ ህይወቱ ያለፈውን አሜሪካዊ ተማሪ ኦቶ ዋርምቢርን ለመጎብኘት ፈቃድ አግኝተው ነበር።
የሌሎች ዓይንና ጆሮ
በፒዮንግያንግ የቀድሞ የእንግሊዝ አምባሳደር፤ በሃገሪቱ ያለው ኤምባሲ ዋጋው ከፍተኛ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ትንሽ ዋጋ የሚያስወጣ ሲሆን "የዓለም ማህበረሰብ ጆሮና ዓይን ማረፊያ በሆነው አካባቢ መሆን ጥሩ ነው" ይላሉ።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ "ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለመመለስ ፍላጎት ካላት" አሜሪካ ንግግር ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ፍንጭ ሰጥተዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ምንም ዓይነት አላማ ይኑረው የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተለየ ነው።
የሎውይ ኢንስቲትዩት የዲፕሎማሲያዊ ካርታ እንደሚያሳየው የተወሰኑ ሃገራት ግንኙነት እየቀነሰ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከኢኮኖሚክ ኮኦፕሬሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት 43 ሃገራት መካከል ስምንቱ እንዲሁም የጂ20 ሃገራት ደግሞ ከዓለም አቀፉ ፋይናንስ ቀውስ በኋላ ያላቸውን ግንኙነት ቀንሰዋል።
ሃንጋሪ፣ ቱርክ እና አውስትራሊያን ጨምሮ 20 ሃገራት ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።
ኤምባሲ መክፈት ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙት መግቢያ መሆኑ አሁንም እንደዘለቀ ነው።
ይህ ደግሞ በብዙዎች ለተገለለችው ሃገርም ይሰራል።
በፒዮንግያንግ እና በተቀረው ዓለም መካከል ግንኙነት ያለ ሲሆን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱም ገና ተሟጦ ያበቃለት ነገር አይደለም።












