ሰሜን ኮሪያ ያለ ኪም ጆንግ ኡን ማን አላት?

የፎቶው ባለመብት, BRENDAN SMIALOWSKI
የሰሜን ኮሪያው ጠቅላይ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጤናቸው እንደተቃወሰ መነገር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ቢሆንም ጉዳዩ ከወሬ የዘለለ አይደለም ሲሉ የሃገሪቱ ባለሥልጣናትና የጎረቤት ሃገር ደቡብ ኮሪያ መሪዎች አሳውቀዋል።
ወሬው ውሃ የሚያነሳም ሆነ አልሆነ ኪም ጆንግ-ኡንን ማን ነው የሚተካቸው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማፈላለግ ተጀምሯል። ቢቢሲ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ሰዎች አነጋግሯል።
የኪም ቤተሰብ ሰሜን ኮሪያን መምራት ከጀመረበት 1940 ጀምሮ ሃገሪቱን የገዙ ሁሉም ግለሰቦች ወንዶች ናቸው። የኪም ቤተሰብ ዝና በሕብረተሰቡ ውስጥ የናኘ ነው።
የቤተሰብ ታላቅነት ከልጅነት ጀምሮ ይሰበካል። ሕፃናት 'መሪያችን ኪም ጆንግ-ኡንን ማየት እፈልጋለሁ' እያሉ ይዘምራሉ።
ታድያ እንዴት ሆኖ ሰሜን ኮሪያና ካለዚህ ምስሉ ጎልቶ ከሚታይ ቤተሰብ ውጭ ማሰብ ይቻላል?
ሁሌም ኪም አለ
ኪም ጆንግ-ኡን ሥልጣል ሊጨብጡ ሲዘጋጁ በእንግሊዝኛው 'ፓየክቱ ብለድላይን' [የፓየክቱ ዘር ግንድ] የሚል ቃል አብዝቶ መሰማት ተጀመረ። ይህ የሆነው የኪምን ወደ ሥልጣን መምጣት ሕጋዊነት ለማስጠበቅ ነው።
ፓየክቱ የተቀደሰ የሚባል ተራራ ነው። ኪም ሱንግ ሁለተኛ እዚህ ተራራ ላይ የጎሪላ ውጊያ እንዳደረጉ ይታመናል። ኪም ጆንግ ኢልም እዚህ ነው የተወለዱት ተብሎ ነው የሚነገረው። የአሁኑ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን አስፈላጊ የፖሊሲ ውሳኔ መስጠት ሲሹ ወደዚህ ተራራ ይሄዳሉ።
በሰሜን ኮሪያ ታሪክ ሁሌም ኪም አለ። ኪም የሃገሪቱ ልብ ትርታ ናቸው ማለት ይቻላል።
ሰሜን ኮሪያ ያለ ኪም ጁንግ-ኡን ማን አላት? የ36 ዓመቱ ኪም ልጆች እንዳላቸው ይታመናል፤ ሥልጣን ለመረከብ ግን ገና ለጋ ናቸው። የኪም ልጆች ሶስት እንደሆኑ ጭምጭምታ አለ። ትልቁ የ10 ዓመት ታዳጊ፤ ትንሹ ደግሞ የ3 ዓመት ጨቅላ። ኪም ጆንግ-ኡን ራሳቸው ሥልጣን ሲረከቡ የ27 ዓመት ወጣት ነበሩ።
የሰሜን ኮሪያን ውሎ የሚከታተሉ ማን ምን ሥልጣን እንዳለው ያውቃሉ። ትዕዛዝ ከየት እንደሚመነጭ ግን ቁርጡን መናገር ይከብዳል። አንዳንድ ጊዜ ምክትሎች ከዋና ኃላፊዎች የላቀ ኃይል አላቸው። ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ወዴት አቅጣጫ እንደምትሄድ ለመገመት እጅግ አዳጋች ያደርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
የቀሩት ሶስቱ ኪሞች
አሁን ሶስት ኪሞች ቀርተዋል። ኪም ጆንግ-ኡን ወደ ሥልጣን መመለስ ባይችሉ ሊተኳቸው ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ። የቤተሰቡን ሌጋሲ ማስቀጠል ግን ቀላል አይደለም።
የመጀመሪያዋ ኪም ዮ-ጆንግ ናት። የኪም ጆንግ-ኡን ታናሽ እህት። የአባቷ ተወዳጅ ልጅ እንደሆነች ይነግርላታል። ገና ከልጅነቷ ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ታሳይ ነበር ይባላል። ታዛቢና መልካም ፀባይ ያላት እንደሆነች ብዙዎች ይመሰክራሉ። ከወንድሟ ጋር ቅርብ እንደሆነችም ነው የሚታመነው። ትራምፕና ኪም ሲንጋፖር ሲገናኙ እስኪርፕቶ ያቀበለችው እሷ ናት። ሃኖይ በነረበው ስብሰባ ላይም ታይታለች።
የሃኖይ ስብሰባ ባለመሳካቱ ምክንያት በጊዜያዊነት ከእርከናቸው ከተቀነሱ ባለሥልጣናት መካከል ነበረች የሚባል ወሬ ተሰምቷል። ማረጋገጥ ግን አልተቻለም። የፖሊት ቢሮ አባል ብትሆንም ውሳኔ በመስጠየት የሚታወቀው የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽን አባል ግን አይደለችም። የኮሪያ ሠራተኞች ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ ክፍልን በምክትልነት የምትመራው እሷ ናት። ፓርቲው በሃገሪቱ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው።
ሴት መሆኗ ግን ከፍተኛ ሥልጣን ለመያዝ ያከብድባታል። ሰሜን ኮሪያ ጥብቅ የሆነ አባታዊ ሥርዓት ያላት ሃገር ናት። ጠቅላይ መሪ መሆንም ሆነ ወታደራዊ ሥርዓቱንም መምራት ለሴቶች የሚታሰብ ቦታ አይደለም።
ሁለተኛው ኪም ጆንግ-ቹል ነው። የኪም ጆንግ-ኡን ታላቅ ወንድም። በፖለቲካ ጨዋታው ሜዳ የማይታይ። ከፖለቲካ ይልቅ የኤሪክ ክላፕተን [እንግሊዛዊ የሮክ ሙዚቃ ተጫዋች] ጊታር ድምፆች የሚመሰጡት እንደሆነ ይነገርለታል።
የመጨረሻው ኪም ፒዮንግ-ሁለተኛ - የኪም ጆንግ ኡን ግማሽ ወንድም። እናቱ የኪም ጆንግ ኡን እንጀራ እናት ነበሩ። ሥልጣን እንዲይዝ አብዝተው ይሹ ነበር ይባላል። ኪም ፒዮንግ-ሁለተኛ በ1971 ወደ አውሮፓ ተልኮ በተለያዩ ሃገራት አምባሳደር ሆኖ ካገለገለ በኋላ ባለፈው ዓመት ነው ወደ ሃገሩ የተመለሰው። በፒዮንግያንግ ፖለቲካ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቀም።
በኪም ጁንግ አስተዳደር ትልቅ ሚና ያላቸው ሌሎች ሰዎች ቢኖሩም ለሥልጣን ዕድል ይኑራቸው አይኑራቸው የሚታወቅ ነገር የለም።
አንደኛው ኮዊ ሪዮንግ-ሄ ናቸው። ሰውዬው የፖሊት ቢሮ ፕሬዝዳንትና የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ተቀዳሚ ሊቀ-መንበር ናቸው። ባለፈው ዓመት ደግሞ ከ20 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝደንት ሆነው ተሹመዋል።
ኪም ዮንግ-ቾል የተባሉት የውጭ ጉዳዮች ዲፕሎማት፣ የካቢኔ መሪው ኪም ጄ-ሪዪንግ፣ የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊው ጆንግ ኪዮንግ-ታየክ እና ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጣን ያላቸው ህዋንግ ፒዮንግ-ሶ በኪም አመራር ከፍተኛ የሚባል ቦታ ያላቸው ናቸው።
ማን ለሥልጣን ይጋደላል? የኪም ወዳጆችና ተቀናቃኞች የሚባል ነገር ይኖር ይሆን? ሃገሪቱ እንዳትፈራርስ በመስጋት ተቀናቃኞች ድምፃቸውን ከማሰማት ይቆጠቡ ይሆን? ሰሜን ኮሪያ እንዳይሆን ሆና በደቡብ ኮሪያ አልያም በቻይና እጅ ስትወድቅ ማየት የሚሻ ሰሜን ኮሪያዊ ይኖራል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው።
እውነት ለመናገር አሁን ኪምን ማን ይተካቸዋል የሚለው ጥያቄ ጥርት ያለ ምላሽ የለውም። እህቱ አባታዊ ሥርዓቱን ሰንጥቃ ማለፍ ይጠበቅባታል። ሌሎች ደግሞ የፓየክቱ ዘር ግንድ የላቸውም። ወጣም ወረደ ሰሜን ኮሪያውያን ሃገራቸውን ከዓለም አቀፍ ጫና ለመጠበቅ ሁሉን እንደሚያደርጉ ይታመናል።













